በኢትዮጵያ ግጭቶችና ድርቅ ባስከተሉት ችግር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀድሞ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ ለከፋ ረሃብና ለጤና መታወክ ተዳርገዋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ምስቅልቅል ሲያጋጥም ፈጥነው ተገቢውን ድጋፍ ይሰጣሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸው የዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶችና ሌሎችም አካላት የዕርዳታ እጆቻቸውን ከመዘርጋት ተቆጥበዋል፡፡ የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎችም መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አስቸግሮ ነበር፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ካልሆኑባቸው አካባቢዎች ዋናዎቹ በአፋር ክልል የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ በምዕራብ አማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎችም በሚፈለገው ደረጃ የጤና አገልግሎት መስጠት አልተቻለም፡፡
የዓለም አቀፉ ድርጅቶችና አጋር አካላት ከያዙት የተሳሳተ አቋም እንዲላቀቁ የማሳመን ሥራ እየተከናወነና ድርጅቶቹም ጉዳቱን እየተረዱና ከግትር አቋማቸው እየተላቀቁ በመምጣታቸው መሻሻሎች ቢኖሩም፣ በእነሱ በኩል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ካልቀጠለ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻውን ሊወጣው እንደማይችል ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በተወሰኑ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ቢያስቸግርም፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከሚገኙ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ተፈናቅለው በየአቅራቢያቸው በተቋቋሙ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኙና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ዜጎች መካከል ወደ 200,000 የሚጠጉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
ከተጠቀሱት ተጠቃሚዎች መካከል በአፋር ክልል በአምስት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ቀዬአቸውን የለቀቁ 294,490 ዜጎች በ16 ጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ፣ ከእነዚህም መካከል በሁለት ወረዳዎች ባሉት ሰባት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ላሉ 63,765 ዜጎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የሰብዓዊ ድጋፍና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አክለዋል፡፡
በእነዚሁ አካባቢዎች ወረርሽኞች እንዳይከሰቱ የመከላከያ ክትባቶችን መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የመጀመርያው ዙር የአፍ ጠብታ የኮሌራ ክትባት ዘመቻ በሁሉም ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ዜጎችና መጠለያ ጣቢያዎች ለተቋቋሙባቸው ቀበሌዎች ተሰጥቷል፡፡
ለመከተብ ከታቀደው 174,781 ዜጎች መካከል ውስጥም ለ120,893 (69.14 በመቶ) ዜጎች ክትባቱን በሰባት ቀናት ውስጥ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
መሠረታዊ የጤና የሥነ ልቦና፣ የሥነ አዕምሮ ጤና አገልግሎቶችና የሥርዓት ምግብ ልየታ ከክፍያ ነፃ በማድረግ በሁሉም መጠለያ ጣቢያዎች እንደተሰጠ፣ በአጠቃላይ 30 የሚሆኑ ተንቀሳቀሽ የጤናና የሥርዓተ ምግብ አገልግሎት የሚሰጡ ቡድኖች ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በእያንዳንዱ መጠለያ ጣቢያ ጊዜያዊ ክሊኒኮች ተቋቁመው ወደ ሥራ እንደገቡ፣ በክሊኒኮቹም ነርሶች፣ አዋላጅ ነርሶችና ሌሎችም የጤና ባለሙያዎች ተመድበው ተገቢውን ግልጋሎት በመስጠት ላይ እንደሆኑና በክልሎች እስከ መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት ወረርሽኝ እንዳልተከሰተ፣ ለዚህም የክትትልና የቅኝት ሥራው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው፣ በአማራ ክልል ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚጠጉ ዜጎች ከቄዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከተፈናቃዮቹም መካከል ጥቂቶቹ በየዘመዶቻቸው፣ አብዛኞቹ ደግሞ በ40 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡
ተፈናቃዮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤናና የሥርዓተ ምግብ አገልግሎት የሚሰጡ 53 ቡድኖች ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን፣ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች መካከል ከ130,256 በላይ ለሚሆኑ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች፣ የፆታ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው 10,837 ዜጎች ደግሞ የሥነ ልቦና፣ የሥነ አዕምሮ ጤና ምክር አገልግሎቶች ከክፍያ ነፃ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ብዙዎቹም እየተፈናቀሉ ወደ አማራ ክልል እየመጡ እንደሆነ፣ መንግሥት አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነቱን ለመወጣት የጤና ሚኒስቴር ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመሆን በተለይ ለወባ፣ ለቲቢና ለኤችአይቪ ቫይረስ መከላከያ የሚያገለግሉ መድኃኒቶችን በሚደረገው የአየር ትራንስፖርት እየተላከ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለክልሉ መድረስ ያለበት እንዳይስተጓጎል ተደርጎ እየተላከ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ ማኅበረሰቡ በምን አኳኃን እየደረሰ ነው? የሚለው የራሱ ችግር ቢኖርበትም ከዚህ እየተላከ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሥራ ማስኬጃም መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተላከ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
ከሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ድርቅ ያስከተለው የምግብና የውኃ እጥረት በእንስሳት ላይ ጉዳት ቢያስከትልም፣ ለረሃብና ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋጡ ሕፃናት፣ እናቶችና እርጉዝ እናቶች ቢኖሩም ሕይወቱ ያለፈው ሰው የለም፡፡ እስሁንም በተለያዩ ባለሙያዎች የተደራጁ ቡድኖችም ፈጣን የዳሰሳ ቅኝት በማካሄድ አስፈላጊው የጤና አገልግሎት መሰጠት ተጀምሯል፡፡
በሶማሌ ክልል ከ193,176 በላይ፣ በኦሮሚያ ክልል ከ424,603 ለሚበልጡ ሰዎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ እንዲሁም በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች 13 ወረዳዎች ለሚገኙና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባቶች ተሰጥቷል፡፡ 100 ቶን አጣዳፊ የአልሚ ምግብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ እንዳንዱ 3,000 ሕፃናትን ማከም የሚችል በጠቅላላው ከ200 በላይ ኪቶች ተሠራጭተዋል ብለዋል፡፡
ድርቁ በአጠቃላይ ካስከተለው ችግርና ካሳደረው ተፅዕኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመላቀቅ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ግብረ ኃይል መቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡
ግብረ ኃይሉም በየሁለት ሳምንት እየተገናኘ አጠቃላይ ግምገማ እንደሚያካሂድ ከእያንዳንዱ ክልልም ድርቁን በተመለከተ ሪፖርት እንደሚቀርብና ከሪፖርቱም በመነሳት ተገቢ ምላሽ በመስጠት አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የገቡትን ጨምሮ ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ 400,0000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ተመላሾች ወደ አገር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተመላሾቹም ወደ አገር ሲገቡ ራሳቸውን ለሌላ በሸታ እንዳያጋልጡ፣ የኮቪድ-19 ቫይረስና ሌሎችም በሽታዎች ካለባቸው ለማወቅ የሚያስችል የምርመራና የልየታ ሥራ እየተከናወነ ወደ ተዘጋጁላቸው መጠለያዎች እንዲሄዱ እየተደረገ ነው፡፡ ለተጠቀሰው ሥራና ለሌላም አገልግሎት የሚውሉ ሰባት አምቡላንሶችም ተመድበዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ የስኳር በሽታና የደም ግፊት ችግር ያባቸው ተመላሾች መድኃኒቶቻቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች ተከናውነዋል፡፡ ከተከናወኑትም ጥረቶች መካከል ተመላሾቹ ወደየተነሱባቸው ክልሎች ሲመለሱ እንዳይቸገሩ በማሰብ የጤና መረጃዎቻቸው ቀድመው ለጤና ቢሮዎች እንዲደርስ መደረጉ ይገኝበታል፡፡ ይህ ዓይነቱም አካሄድ ክትትላቸውን እንዳያቋርጡ ይረዳቸዋል፡፡