Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ጤናማ ያልሆነ ምግብ ቁጥጥር ሕግ እንዲወጣ እየሠራን ነው› አቶ አክሊሉ ጌትነት፣ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2019 ከተመዘገበው ሞት 43 በመቶ ያህሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው፡፡ በ2019 ለሞት ምክንያት ከሆኑት ከቀዳሚዎቹ አሥር ምክንያቶች ደግሞ ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች ከ55 በመቶ በላይ እንደነበሩ የዓለም ጤና ድርጅት የግሎባል ሔልዝ ዳሰሳ ያሳያል፡፡ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ዋና መንስዔ ከሚባሉ የሚመደብ ሲሆን፣ ይህም ከ2009 እስከ 2019  ባሉት ጊዜያት በ18 በመቶ ጨምሯል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የደም ግፊት፣ ከልክ በላይ መወፈርና ኦብሲቲ በተከታታይ በ29.8 በመቶ እና በ81.4 በመቶ ጨምረዋል፡፡ በ2019 ከስትሮክ (ምት)፣ ከልብ ሕመምና ከጉበት ጋር የተያያዙ በሽታዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከተመዘገበው ሞት ከቀዳሚዎቹ አሥር ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከአመጋገብ ችግር ጋር በተያያዘ ከተመዘገበው ሞት ውስጥ ከአሥር ስምንት ያህሉ ከልብ ሕመም ጋር ሲሆን፣ 35 በመቶው ደግሞ ከደካማ የአመጋገብ ሥርዓት ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች የተከሰቱ ነበሩ፡፡ ይህንን ችግር የአመጋገብ ሥርዓት በማበጀት፣ ምግቦች ላይ ቁጥጥር በማድረግና ቁጥጥሩን በመተግበር መፍታት ያስፈልጋል የሚለው ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ በሆነው የምግብ ቁጥጥር ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ አክሊሉ ጌትነት የማኅበሩን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ምግብ ላይ ቁጥጥር መደረግ አለበት በሚል ማኅበሩ በጀመረው ፕሮጀክት ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ፕሮጀክት ለመጀመር መነሻችሁ ምንድነው?

አቶ አክሊሉ፡- ከዚህ ቀደም ትራንስፋቲ አሲድ ላይ ስንሠራ ነበር፡፡ ይህንን የውትወታ ሥራ ስንሠራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ነበር፡፡ በግብረ ኃይሉ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ላይ የቁጥጥር ሕግ እንዲወጣ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የምግብ ቁጥጥር ሕግ ተቀባይነት አግኝቶ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ የማንቃትና የውትወታ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የትንባሆ ቁጥጥር ላይ ስንሠራ የነበረው ውጤት ያመጣ ሲሆን፣ በዚህኛውም ውጤት ለማስመዝገብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሠራለን፡፡ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ቁጥጥር ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ የመውጣትን አስፈላጊነት አስመልክቶ ግንዛቤና ተፅዕኖ ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ትራንስፋቲአሲድ ላይ ብቻ ስንሠራ እንደነበረው ሳይሆን ሁሉንም ጤናማ ያልሆነ ምግብ ያካተተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራውን ከማን ጋር ትሠራላችሁ?

አቶ አክሊሉ፡- አሜሪካ ከሚገኝ ግሎባል ሔልዝ አድቮኬሲ ኢንኪውቤተር የሚባል ጤናማ ባልሆነ ምግብ ላይ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሥራው ከመግባታችሁ በፊት በኢትዮጵያ የዳሰሳ ጥናት አድርጋችሁ ነበር፡፡ ምን ያሳያል?

አቶ አክሊሉ፡- የዓለም ጤና ድርጅት ጥናቶችና ሌሎችን ዓይተዋል፡፡ ቅርብ የሚባለው ጥናት በ2019 የተሠራ ነው፡፡ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ከሆኑ ሦስት ጉዳዮች አንዱ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለሞት ምጣኔ 43 በመቶውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ይህን የኢትዮጵያ መረጃ የዓለም ጤና ድርጅት በ2019 ያወጣው ነው፡፡ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ ያላቸው የሞት ምጣኔ እኩል እየደረሰ ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ለዚህ መንስዔ የሆኑት ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት አንዱ ምክንያት ስለሆነ፣ በዚህ ላይ ቁጥጥር የማድረጉ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ማኅበራችንም ጤናማ ያልሆነ ምግብና ሕግም ሊወጣለትና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል በሚል ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ በአሥር ዓመት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2009፣ 18 በመቶ የነበረው በ2019 29 በመቶ ደርሷል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ጤናማ ያልሆነ ምግብ የምንመገበው ከነበረበት አሥር በመቶ በላይ ነው የጨመረው፡፡ ይህም ለክብደት መጨመርና ለደም ግፊት ያጋልጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደዚህ ችግር እንዲገባ ያደረገው ምክንያት ምንድነው?

አቶ አክሊሉ፡- ፕሮሰስ የሚደረጉ ምግቦች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ጤናማ ካልሆነ ምግብ ጋር የሚያያዙት የተቀነባበሩና የታሸጉ፣ ጨውነት የበዛባቸው ምግቦች ናቸው፡፡ ዘመናዊነት ሲመጣ በተፈጥሮ ያገኘናቸውን ምግብ ከመመገብ ይልቅ በፋብሪካ የተመረቱና የታሸጉ ምግቦችን እንመገባለን፡፡ በታሸጉ ምግቦች ውስጥ ረዥም ጊዜ እንዲቆዩና እንዲጣፍጡ የሚጨመሩ ኬሚካሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ምግቡን እንዳይበላሽና እንዲጣፍጥ ቢያደርጉም፣ ለጤና ጎጂነታቸው ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘመናዊነት እየመጣ ሲሄድ፣ የታሸጉና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን የሚጨመሩት ኬሚካሎች ደግሞ ጤናማነታችን ላይ ችግር ያመጣሉ፡፡ ስለሆነም ዓይነትና መጠናቸው ላይ ቁጥጥር መደረግ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የምግብ ቁጥጥር ላይ እንዲወጣ የምትፈልጉት ሕግ ከምን ደረጃ ደርሷል?

አቶ አክሊሉ፡- አሁን ረቂቅ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ረቂቁን ከጤና ጥበቃ፣ ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና ከሌሎች የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከሌሎችም ጋር በመሆን እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ረቂቁ ገና በጅምር ላይ ነው፡፡ አርቃቂዎቹ ጋር ነው፡፡ የእኛ ሚና ሕጉ ተቀባይነት አግኝቶ ቶሎ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውትወታ ሥራውን ማን ላይ ትሠራላችሁ? በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርተው ከሚታሸጉ ምግቦች ይልቅ ከውጭ የሚገቡ ይበልጣሉ? ሥራችሁ አስመጪዎችን ማንቃትንም ያካትታል?

አቶ አክሊሉ፡- የታሸጉ ምግቦች ይዘታቸው በአግባቡ ገላጭ ጽሑፉ እንዲኖር ነው የምንወተውተው፡፡ ገላጭ ጽሑፍ በምን ዓይነትና መጠን? የሚሉና ሌሎችም ወደፊት በዝርዝር የሚወጡ ይሆናል፡፡ የውትወታ ሥራችንን ተደራሽ የምናደርገው በመገናኛ ብዙኃን አማካይነትና በሥልጠና ነው፡፡ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ላይ የታሸጉ ምግቦች ላይ ብቻ ሳይሆን ጨው አጠቃቀም ላይም ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ከጨው አጠቃቀም ጋር ያለው ችግር ምንድነው?

አቶ አክሊሉ፡- በአመጋገብ ሥርዓታችን አንዱ ከፍተኛ ችግር የጨው አጠቃቀም  ነው፡፡ 96 በመቶ የምንሆነው ኢትዮጵያውያን ጨው የምንመገበው የዓለም ጤና ድርጅት ከሚመከረው በላይ ነው፡፡ በቀን በሰው 8.3 ግራም እንጠቀማለን፡፡ የሚመከረው ግን አምስት ግራም ነው፡፡ ጨው ደግሞ ለደም ግፊት መጨመር ዋናው ምክንያት ነው፡፡ አጠቃላይ አመጋገባችንን በተመለከተ ያለን ሥርዓት ክፍተት ያለበት ስለሆነ ቁጥጥር መደረግ አለበት፡፡ በመንግሥት፣ በሕዝብና በንግድ ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ መፈጠር አለበት ነው የምንለው፡፡ አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ ይህንን ላይገነዘብ ይችላል፡፡ ስለዚህ ዋናው ትኩረታችን ግንዛቤ የመፍጠር በኋላም በሕግ እንዲደገፍ የማድረግ ነው፡፡ ሥራውን በዋናነት በመገናኛ ብዙኃን ነው የምንሠራው፡፡ ሌሎች ሁለት ድርጅቶች ከንግድ ማኅበረሰቡና ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር ይሠራሉ፡፡ ሥራውን ተከፋፍለን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደሩት ጫና ምን ይመስላል?

አቶ አክሊሉ፡- ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ 31.3 ቢሊዮን ብር ወይም የአጠቃላይ ምርቷን 1.84 በመቶ ታጣለች፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የ2017 ሪፖርት እንደሚያሳየውም፣ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከሚያወጣው ገንዘብ 30 በመቶውን የሚይዘው ለዋናዎቹ አራቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ነው፡፡ ይህም ወደ 4.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በጣም ደሃ ቤተሰቦችና ግለሰቦች በተለይም በገጠራማ አካባቢ ለሚኖሩት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመታከም አቅም የላቸውም፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኢትዮጵያ በ2030 አሳካዋለሁ ብላ እየሠራች የምትኘውን ዘላቂ የልማት ግቦችና ድህነት ቅነሳም አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሚመለከተውን አካላት በሙሉ ተባብረን ችግሩን ልናስወግድ ይገባል፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች