Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዓመት 15 ቢሊዮን ብር እንደሚደጉም የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ

  ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዓመት 15 ቢሊዮን ብር እንደሚደጉም የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ

  ቀን:

  የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በእጅጉ እየናጣት ላለችው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ በዘጠኝ ዘርፎች በዓመት 15 ቢሊዮን ብር ገደማ ድጎማ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ይህ የድጎማ መጠን በአጠቃላይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ የኑሮ ውድነት ለማቃለል በዋናነት ከመንግሥት ካዝናና ከግሉ ባለሀብት በቀጥታና በተዘዋዋሪ፣ እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ የገባውን እንደማይጨምር አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

  በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን እ.ኤ.አ. የ2018 የሕዝብ ቁጥር ትንበያ መረጃ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ የቋሚ ነዋሪዎች ሕዝብ ብዛት 3‚519‚000 ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚሆኑ ቤተሰቦችን ለመለየት 775,899 አባወራና እማወራዎችን መዝግቧል፡፡ ምዝገባ ከተደረገላቸው ሰዎች ውስጥ ከ347 በላይ የሚሆኑት ደሃና የደሃ ደሃ ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በዘጠኝ ዘርፎች የሚያደርገው ድጎማም በዋነኛነት የእነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና ለመቀነስ ያለመ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡ 

  ከፌዴራል መንግሥትና ከከተማ አስተዳደሩ ካዝና ይወጣል የተባለው ይህ ድጎማ የነዳጅ፣ የዳቦ አቅርቦት፣ የተዘዋዋሪ ፈንድ፣ የምገባ ማዕከል፣ የማዕድ ማጋራት፣ የትራንስፖርት፣ የመሠረታዊ ሸቀጥ አቅርቦት፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድንና ከቀረጥ ነፃ የምግብ ሸቀጥ አቅርቦት ድጎማዎችን የሚያካትት መሆኑን የንግድ ቢሮው አስታውቋል፡፡ ለከተማዋ ነዋሪዎች ይደረግባቸዋል የተባሉት እነዚህ ዘጠኝ ዘርፎች በአጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩንና የፌዴራል መንግሥትን 15 ቢሊዮን ብር ለሚጠጋ ወጪ እንደሚዳረጉ ለሪፖርተር የተናገሩት፣ የከተማዋ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ናቸው፡፡ ከዚህ ድጎማ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የነዳጅ ድጎማ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

  አቶ አደም በየቀኑ በአማካይ አንድ ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ከተማዋ እንደሚገባ አስታውቀው፣ መንግሥት ለነዳጅ ከሚያደርገው ድጎማ ትንሹ 20 ብር ተወስዶ በዓመት ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት ዘርፎች በሙሉ የከተማ አስተዳደሩ ድጎማ የሚያደርግባቸው መሆኑን አክለዋል፡፡

  በቅርቡ ዋጋው ወደ ሁለት ብር ከአሥር ሳንቲም ያደገው ሸገር ዳቦ የከተማ አስተዳደሩ ድጎማ ከሚያርፍባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑን፣ አስተዳደሩ በእያንዳንዱ ዳቦ ላይ አንድ ብር ከ14 ሳንቲም ድጎማ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ለዳቦ ፋብሪካው የሚደረገውን የስንዴ አቅርቦት ጨምሮ 818 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንደሚደረግ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

  ለተማሪዎች የሚደረገው የትምህርት ቤት ምገባና የደንብ ልብስ አቅርቦት በምገባ ማዕከል ሥር ሌላኛው የድጎማ ዘርፍ ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ ለሁለቱ ክንውኖች በ2014 ዓ.ም. ብቻ ሁለት ቢሊዮን ብር ድጎማ እንደተደረገ ያስታወቀው ቢሮው፣ በትምህርት ቤት ምገባው ከ628,000 በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እየተመገቡ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ከተማሪዎች ውጪም በስድስት የምገባ ማዕከላት በአማካይ 12 ሺሕ መመገብ የማይችሉ የከተማዋ ነዋሪዎች እየተመገቡ ነው ተብሏል፡፡

  የትራንስፖርት ዘርፉን በተመለከተ ደግሞ ለሸገር፣ ለአንበሳና ለድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች የከተማ አስተዳደሩ በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ እየደጎመ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ አደም ተናግረዋል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድንን በተመለከተም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች 181.6 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንደተደረገ ቢሮው ገልጿል፡፡

  እነዚህ ድጎማዎች እየተደረጉ ቢሆንም ከ35 በመቶ በላይ የደረሰው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የመዲናዋ ነዋሪዎችን ዋነኛ ተጋፋጭ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ኃላፊው፣ በተለያዩ ዘርፎች የሚደረገው ይህ ድጎማ ባይኖር ኖሮ የኑሮ ውድነት ጫናው ከዚህም በላይ እንደሚከፋ ጠቁመዋል፡፡

  ኃላፊው እነዚህ ድጎማዎች በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማዋ ነዋሪች ኑሮ ለማቅለል እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ አተገባበራቸው ላይ ባለ ችግር ምክንያት ግን ‹‹የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ጭምር እየተደጎሙ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሸገር ዳቦን ለዚህ እንደ ማሳያ አድርገው የገለጹት አቶ አደም፣ አሁን ዳቦው ሌላ ቦታ ለንግድ እንዳይቀርብ በሚል አንድ ቤተሰብ ከአሥር ዳቦ በላይ እንዳይወስድ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ የነዳጅ ድጎማውም ቢሆን ኢምባሲዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጭምር ሲጠቅም የነበሩ መሆኑን በማውሳት፣ መንግሥት ሊተገብር ያሰበውን የታለመ የነዳጅ ድጎማ አስታውሰዋል፡፡

  ይሁንና በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በፌዴራል መንግሥቱ የሚደረገው ድጎማ ጊዜያዊ ማስተንፈሻ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን የተናገሩት አቶ አደም፣ የነዋሪዎችን ገቢ ማሳደግ፣ ምርታማነትም መጨመር፣ የግብይት ሰንሰለቱን ማጥራትና አቅርቦትን ማስፋት መፍትሔ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...