Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለካፒታል በጀት ከተፈቀደው ከ147.8 ቢሊዮን ብር ውስጥ ወጪ የተደረገው 35.9 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለበጀት ዓመቱ ከተፈቀደው 147.8 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት ውስጥ እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ወጪ ተደርጎ ጥቅም ላይ የዋለው፣ 35.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላከተ።

በጀት ዓመቱ ከጀመረበት ሐምሌ 2013 ዓ.ም. አንስቶ በነበሩት ስድስት ወራት ማለትም እስከ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ድረስ ለዓመቱ ከተፈቀደው 147.8 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ለሚመለከታቸው የካፒታል በጀቱ ባለድርሻዎች የለቀቀው 35.9 ቢሊዮን ብር ወይም 24.3 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነ መረጃው ያስረዳል።

ከተፈቀደው የካፒታል በጀት ውስጥ እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ እጅግ ዝቅተኛ በጀት የተለቀቀለት የማኅበራዊ ዘርፉ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ለማኅበራዊ ዘርፉ የተፈቀደው አጠቃላይ የካፒታል በጀት 34.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ዘርፉ ከተፈቀደለት የካፒታል በጀት በግማሽ ዓመቱ ውስጥ የተለቀቀለት 2.8 ቢሊዮን ብር ወይም 8.2 በመቶ ብቻ እንደሆነ ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል።

ለኢኮኖሚ ዘርፉ ከተፈቀደው 86.4 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት ውስጥ በግማሽ ዓመቱ የተለቀቀው 27.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ለዘርፉ ከተፈቀደው የካፒታል በጀት ውስጥ 32.1 በመቶ ብቻ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።

ለክልሎች በድጎማ መልክ እንዲተላለፍ የተፈቀደው አጠቃላይ የካፒታል በጀት መጠን 58.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ በግማሽ ዓመቱ የተከፈለው 28.04 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ለዓመቱ ለክልሎች ከተፈቀደው የካፒታል በጀት ውስጥ 47.8 በመቶ መተላለፉን ያሳያል። 

በተጨማሪም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ተብሎ ለክልሎች በካፒታል በጀት መደብ እንዲተላለፍ ከተፈቀደው 12 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ በግማሽ ዓመት ውስጥ የተላለፈው 2.5 ቢሊዮን ብር ወይም 21.5 በመቶ ብቻ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

ለአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ ከተፈቀደው 14.6 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት ውስጥ በግማሽ ዓመት የተለቀቀው፣ 2.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን በመረጃው ተመላክቷል።

በመሆኑም ለበጀት ዓመቱ ከተፈቀደው 147.8 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት ውስጥ በቀሪዎቹ ስድስት ወራት እስከ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ፣ የፌዴራል መንግሥት ማስተላለፍ የሚጠበቅበት ቀሪ የካፒታል በጀት 111.9 ቢሊዮን ብር መሆኑን መረጃው ያመለክታል። 

ለመደበኛ በጀት የተፈቀደው 308.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በግማሽ ዓመት 140.6 ቢሊዮን ብር ወይም 45.5 በመቶ የሚሆነው እንደተለቀቀ ከመረጃው መረዳት ተችሏል። 

በመጀመሪያ ለበጀት ዓመቱ የተፈቀደው አጠቃላይ በጀት 561.7 ቢሊዮን ብር የነበ ሲሆን፣ በሁለተኛው ሩብ ዓመት ላይ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በመፅደቁ አጠቃላይ የዓመቱን በጀት 683.7 ቢሊዮን ብር አድርሶታል።

የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ኢዮብ ተካለኝ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ጦርነቱ ባስከተለው ከፍተኛ ወጪ ምክንያት ለተወሰኑ የካፒታል ፕሮጀክቶች የተያዘው በጀት እንደሚታጠፍ ገልጸው ነበር።

‹‹በተለይም ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለሆነም ላቀድናቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ በጀት መልቀቅ ስለማንችል በጀቱን እንቆርጣለን፣ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን እናፋጥናለን። ለአሁን ትኩረታችን በጦርነት የተጎዱ ነዋሪዎችን እንደገና ማቋቋም ነው። በመሆኑም ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸው ፕሮጀክቶችን ብቻ በመለየት ትግበራቸው እንዲቀጥል እናደርጋለን፤›› ማለታቸው ይታወሳል። 

ለዘንድሮ በጀት ዓመት ከፀደቀው 561.7 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ የገንዘብ ሚኒስቴር የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጠይቆ፣ ባለፈው ታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል። 

የገንዘብ ሚኒስቴር የተጨማሪ በጀቱን አስፈላጊነት በተመለከተ በወቅቱ በሰጠው ማብራሪያ፣ ‹‹ተጨማሪ በጀቱን ማዘጋጀት ያስፈለገው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ፣ መንግሥት በሚሰበስበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም የተጨማሪ ወጪ ፍላጎትን በበጀት ሽግሽግ ማስተናገድ አዳጋች በመሆኑ ነው፤›› ብሎ ነበር፡፡

በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የአዲስ ወግ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና በ2014 ዓ.ም. ጎልቶ መታየት እንደሚጀምር ተናግረው ነበር።

አገሪቱ ባለፈው ዓመትም (በ2013 ዓ.ም.) በተመሳሳይ ጦርነት ውስጥ ያለፈች ቢሆንም፣ ስድስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባ እንደነበር ያስታውሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፣ በዘንድሮው 2014 ዓ.ም. ግን ጦርነቱ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጫና የከፋ እንደሚሆን ተናግረው ነበር።

በ2014 በጀት ዓመት በጦርነቱ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የኢኮኖሚያ ጫና ለማሳየትም በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት፣ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማቅረብ መንግሥት ያወጣውን ወጪ በማሳያነት አቅርበዋል። 

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ማሳያም በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ብቻ መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ አሥር ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን በማውሳት፣ ጫናውን መጠቆማቸው ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች