Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ላለፉት ሁለት ዓመታት ያቀረበውን ሪፖርት ገልብጦ ለፓርላማ ማቅረቡ አስወቀሰው

ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ላለፉት ሁለት ዓመታት ያቀረበውን ሪፖርት ገልብጦ ለፓርላማ ማቅረቡ አስወቀሰው

ቀን:

ሪፖርቱን አስተካክሎ እንደገና እንዲያቀርብ ተጠይቋል

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ በ2012 እና በ2013 ዓ.ም. የቀድሞው የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለፓርላማ ያቀረባቸውን የአፈጻጸም ሪፖርቶች እንደገና ገልብጦ አምጥቷል ተብሎ፣ ከምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ወቀሳ ቀረበበት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ዓርብ ሚየዚያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ገምግሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመስከረም 2014 ዓ.ም. የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀትና ለመወስን በፀደቀው አዋጅ የቀድሞውን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር  በሁለት በመክፈል ከተቋቋሙ ሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ራሱን ችሎ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ሚኒስቴሩ በቋሚ ኮሚቴው ‹‹እጅግ ነውር ተግባር›› የተባለውን በተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች ያልተገመገመ ሪፖርት፣ ለቋሚ ኮሚቴው በዘጠኝ ወራት ፈጽሜዋለሁ ብሎ መላኩ ከፍተኛ ወቀሳ አስከትሎበታል፡፡

ለአብነትም ከተጠቀሱት የተገለበጡ ከተባሉት ሪፖርቶች መካከል በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ላይ 40 ዜና መጽሔት፣ 800 በራሪ ወረቀት፣ 8 አርቲክል ተሠርተዋል ተብሎ በ2012 ዓ.ም. የቀረበ ሪፖርት ምንም ሳይቀየር የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ተብሎ መቅረቡ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ‹‹ብልሹ አሠራር ናቸው›› ተብለው ከቀረቡት 16 ጥቆማዎች መካከል 13 ተጣርተው መልስ እንደተሰጣቸውና ሦስት ጥቆማዎች በሒደት ላይ መሆናቸውን የሚያሳየና አፈጻጸሙ 97.4 በመቶ መሆኑን የሚገልጽ በ2012 ዓ.ም. የቀረበ የዘጠኝ ወራት ሪፖርት፣ አንድም ፊደል ሳይቀነስና ሳይጨመር እንዳለ ተገልብጦ ለምክር ቤቱ የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ተብሎ እንደቀረበ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ከሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ውስጥ በስድስት ወራት የነበሩ አፈጻጸሞችን በድጋሚ በዘጠኝ ወራት ሳይቀየሩ መቅረባቸውን፣ ለተቋሙ የተመደበው በጀትም ከተከናወነው ሥራ ጋር እንደማይጣጣም የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሚኒስቴሩ በተደጋጋሚ ሪፎርም ላይ ነኝ በሚል ሰበብ በርካታ ሥራዎችን ባለመሥራት አፈጻጸሙ በሚጠበቅበት ልክ አለመሆኑን መግለጹ፣  የሪፎርም ሥራ ላይ ነን በሚል ሰበብ ሥራን ማጓተቱን እንዲተው ተነግሮታል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ምልከታ በርካታ ዓመታት አስቆጥረው ለኅብረተሰቡ ምንም ዓይነት ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳይሰጡ በጅምር ላይ የቀሩ፣ ለተጠቃሚዎች ርክክብ ሳይደረግባቸው ቆመው የቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም ገልጿል፡፡

የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር) ተገልብጦ መጣ ሰለተባለው ሪፖርት እውነት መሆኑንና የሪፖርት አቀራረቡ ይዘት ብቻ ሳይሆን ግድፈት ጭምርም እንዳለው ገልጸው፣ ‹‹ለተፈጠረው ችግር እጅግ በጣም ይቅርታ እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈቲሃ አህመድ የሚኒስቴሩ የበላይ ኃላፊዎች በአዋጅ የተሰጣቸውን ሥራ ከመሥራት ይልቅ፣ የዕቅድ ትረካ ላይ እንደሚያተኩሩና ሥራው መሬት ላይ ያልወረደ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙ ሁሉም የምክር ቤት አባላት በተገኙበት መደበኛ ስብሰባ ቢቀርብ ኖሮ ጉዳችሁ ይፈላ ነበር፤››  ብለዋል፡፡

‹‹እኛ ቀድመን ስንገመግም ኃፍረት የላቸውም እንዴ ብለናል፣ ዘንድሮ ደግሞ ምን ዓይነት ተቋም ነው ያጋጠመን በሚል›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

በሚኒስቴሩ ታቅደው ያልተፈጸሙ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ትረካ የበዛበትን የዕቅድ አፈጻጸሙ በድእንደገና ተገምግሞ፣ ተከልሶና ተስተካክሎ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...