Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት ይብቃ!

  በየአቅጣጫው የተያዘው ኢትዮጵያን ሰላም የመንሳት እንቅስቃሴ በፍጥነት ሊቆም ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያገረሸበት ያለው የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ፍጥጫ ኢትዮጵያን ሰላም እየነሳ ነው፡፡ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሁለቱ ቅርንጫፎችና በተፎካካሪ ፓርቲነት የሚታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በመግለጫዎቻቸውና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተዋንያን በመታገዝ የገቡበት የቃላት አተካራ በፍጥነት ይገታ፡፡ የሁለቱን ክልሎች ሕዝብ የማይወክል የጠላትነት ስሜት ገለል ተደርጎ፣ በሰከነ መንገድ ከጥፋት ጎዳና ለመታቀብ ሰላማዊ አማራጮች ላይ ይተኮር፡፡ ኢትዮጵያ በየቦታው በሚነሱ ሁከቶችና ጥቃቶች ተቀስፋና ሕዝቧ የማያባራ ሥቃይ ውስጥ ሆኖ የሰላም ያለህ እያለ፣ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ መለስተኛ ችግሮችን በማጦዝ የበለጠ ቀውስ ለመፍጠር መቅበዝበዝ ተገቢ አይደለም፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚፈቱ ልዩነቶችን በማራገብ ሊገኝ የሚችለው ውድመት እንጂ ልማት እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በሴራ ፖለቲካ ምክንያት አገር ሰላም አሳጥቶ ሕዝብን መከራ ውስጥ ለመክተት እየተሄደበት ያለው ርቀት አደገኛ እየሆነ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በተለይ በሁለቱ ቅርንጫፎቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለምን መፍታት እንደማይፈልግ ግራ ያጋባል፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁከት ሰልችቶታል፡፡ አንፃራዊ ሰላሙን የሚያደፈርስበት የሴራ ፖለቲካ አስጠልቶታል፡፡ በስሙ እየነገዱ እርስ በርስ የሚያጋድሉት፣ የሚያፈናቅሉት፣ የሚዘርፉት፣ ተስፋውን የሚያጨልሙበትና ለዕድገቱ ደንታ የሌላቸው አስመሳዮችን ማየት እየቀፈፈው ነው፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ እዚህ የደረሱ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቹን የሚንዱትን እየተፀየፈ ነው፡፡ ማኅበራዊ መስተጋብሮቹን በማዛበት ሕግ የሚጥሱትን በቃችሁ እያላቸው ነው፡፡ በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በመሯቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች የተደመጡት የሕዝቡ ድምፆች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ራሳችሁ ሕግ አክብራችሁ አስከብሩ፣ ሕገወጦችን ለፍትሕ አቅርቡ፣ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ የሆኑትን ሌብነትና ምግባረ ቢስነት አስወግዱ፣ በማንነትና በእምነት ውስጥ የሚከለሉ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን አደብ አስገዙ፣ አገርን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ድርጊቶች ተቆጠቡ፣ የኑሮ ውድነቱን በደመነፍስ ሳይሆን በአዋጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ አርግቡ፣ በአጠቃላይ የአገር አንድነትና ሉዓላዊነትን የሚገዳደሩ ተግባራትን አስቁሙ በማለት ሕዝብ ጥብቅ ማሳሰቢያ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ይህ ማሳሰቢያና አደራ ተዘንግቶ በሕዝብ ስም ሌላ ዙር ጥፋት ሲደገስ በሕግ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ለማቆም አዳጋች ነው፡፡

  ኢትዮጵያውያን ከግጭትና ከውድመት የሚያተርፉት ምንም ነገር እንደሌለ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በቅርቡ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ቁሳዊ ውድመት በሚገባ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደረሰባት የገጽታ መቆሸሽ አይዘነጋም፡፡ በጦርነቱ ጦስ ሳቢያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በአሜሪካና በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚወጡባት መግለጫዎችና ሪፖርቶች አንገት የሚያስደፉ ናቸው፡፡ ሰሞኑን የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ያወጣው እ.ኤ.አ. የ2021 ሪፖርት ያካተታቸው ዝርዝር ጉዳዮች ራስ ያሳምማሉ፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ አንገትን ቀና አድርጎ ለመቆም ያሸማቅቃሉ፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተጠያቂ አካላት ይቀበሉትም አይቀበሉትም፣ ብዙዎቹን የተጠቀሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካድ አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ መግለጫዎቹ ብዙዎችን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የትውልድና የታሪክ ተጠያቂነት ከሚያስከትል መራራ ሀቅ ጋር የሚኖሩ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን፣ ልዩነቶቻቸውን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ዝግጀት በሌላቸው አካላት ምክንያት ሌላ ዙር ፍጅትና ሰቆቃ ሲደገስ ዝም ማለት የለባቸውም፡፡

  በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልሎች መካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች አሉ፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ራሳቸውን ከሕግ በላይ ለማድረግ ካልፈለጉ በስተቀር፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በሰላማዊ መንገድ ለመፈታት የሚያዳግት አንዳችም ችግር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ አሁን ከሚስተዋለው አጠቃላይ ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው ግን፣ የግለሰቦችና የቡድኖች ሥልጣንና ጥቅም ከአገር እየበለጠ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለሕጋዊና ለሰላማዊ ንግግር ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ፣ ጋሻ ጃግሬዎችን እያሠለፉ የይዋጣልን ጡንቻን ማሳየት ዋነኛው አማራጭ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በድምፁ ለሥልጣን ያበቃን ሕዝብ መናቅ ሲሆን፣ ለአገር ጭምር ደንታ ቢስነትን ነው የሚያሳየው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለም በአሁኑ ጊዜ በአማራና በኦሮሞ ፖለቲከኞች መካከል የሚስተዋለው ትከሻ መለካካት፣ ለሕዝብ ከሚኖረው ጥቅም ይልቅ ይዞት የሚመጣው ዳፋ ነው የሚያሳስበው፡፡ የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ቅርንጫፎች አመራሮች የገቡበት ፍጥጫ፣ ከእነሱ አልፎ ተርፎ ተፎካካሪዎቻቸውን አብንና ኦፌኮን ሲያካትት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ ነብይ መሆን አይገባም፡፡ የእምነት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች አገር ለማዳን ተንቀሳቀሱ፡፡

  ኢትዮጵያ በርካታ ዘመናትን ተሻግራ እዚህ ዘመን ላይ የደረሰችው በከፍተኛ መስዋዕትነት መሆኑን ታሪክ በሚገባ መዝግቦታል፡፡ በየዘመናቱ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከተስፋፊዎችና ከወራሪዎች እየተከላከሉ፣ አንዳቸው ለሌላቸው በማስተላለፍ እዚህ ትውልድ ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህ መሀል ግን የተዘነጋ አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ነፃነት ጠብቀው ማቆየት ከቻሉ፣ ለምን በልማት አሳድገው ከሀብታሞቹ ተርታ ማሠለፍ አቃታቸው የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶች የበለፀገች ስለሆነች ነው ለምን የድህነት ተምሳሌት ሆነች የሚባለው፡፡ ለዚህ መልሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላት ሲመጣ ተባብረው ለመነሳት ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡ ሰላም ሲሆን ግን ለልማት ከመነሳት ይልቅ እርስ በርስ መተናነቅ ይቀናቸዋል ነው የሚባለው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አብረው መብላት የሚወዱት ኢትዮጵያውያን አብረው መሥራት አይሆንላቸውም›› እየተባለ የሚተረተው፡፡ ይህ ሐሰት ቢሆን ኖሮ ገበያዎች በምግብ ምርቶች ተጥለቅልቀው ችግር አይኖርም ነበር፡፡ የኑሮ ውድነት እንደ ሰደድ እሳት ሕዝቡን እየለበለበው ባለበት በዚህ ጊዜ እንኳ፣ ከየአቅጣጫው የሚሰማው ቀረርቶ ግጭት መቀስቀሻ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ለማድረግ ኮሚሽን ተመሥርቶ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ምንም እንኳ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ምልመላና አሿሿም ላይ አሁንም ድረስ ጥያቄዎች እየተነሱ ቢሆንም፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እያረሙ በአንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረግ እንደሚቻል ብዙዎች እያሳሰቡ ነው፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ብልፅግና የሚመራው መንግሥትና ክልሎች አገራዊ ምክክር ለማድረግ በሚያስችል ቁመና ላይ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያስፈልገዋል፡፡ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ትርምስና ውድመት ሊከት የሚችል አደገኛ እንቅስቃሴ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አመራሮች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት መካከል እየተስተዋለ ምን ዓይነት ተስፋ መሰነቅ ይቻላል? የቃላት ጦርነቱ ወደ ሕዝብ ውስጥ እየሰረገ እየገባ ላለመሆኑ ምን ማስተማመኛ አለ? የሚስተዋለውን አገር የሚያጠፋ ችግር ለመቅረፍ አንዳችም ፍላጎት ከሌለ ምንድነው የሚፈለገው? ከአውዳሚው ጦርነትና በየቦታው በፖለቲከኞች ሴራ ከሚቀሰቀሱ ግጭቶች መላቀቅ የማይፈለገው ለምንድነው? ኢትዮጵያን ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ለማውጣት ፍላጎት ሳይኖር ስለየትኛው ልማትና ብልፅግና ነው የሚደሰኮረው? አሁንም ደግመን ደጋግመን እንላለን ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት ይብቃ! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...

  ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ቃል ሲከበር ብቻ ነው!

  እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን...