የዓለም ባንክ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በጦርነት የተጎዶ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎችን ለማቋቋም የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ማፅደቁን፣ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን መቃወሙ ተሰማ።
የዓለም ባንክ ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈው ሚያዝያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ ባንኩ በፈቀደው የገንዘብ ድጋፍ የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራው በቅደሚያ ተጠቃሚ የሚሆኑት፣ ላለፈው አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ በጦርነት የቆዩት የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች መሆናቸው ታውቋል።
በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል፣ እንዲሁም በጦርነቱ የተጎዱ የአማራና የአፋር ክልሎች አካባቢዎች በቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የዓለም ባንክ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጎዱት አካባቢዎችና ነዋሪዎች በተጨማሪም፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በምዕራብ ኦሮሚያ በሚስተዋሉ ግጭቶች የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎችን ለማቋቋም፣ የዓለም ባንክ ያፀደቀው የገንዘብ ድጋፍ እንደሚውል ተገልጿል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጥያቄ ተቀብሎ ከማፅደቁ በተጨማሪም፣ የመልሶ ግንባታና ነዋሪዎችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክቶቹ የሚተገበሩበትን መንገድና የክትልል ሒደት አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት የቀየሳቸውን ሥልቶች ላይም መስማማቱ ታውቋል።
‹‹የመልሶ ግንባታና ነዋሪዎችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክቶቹ ትግበራ ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑን ለማረጋገጥ ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ በፌዴራል መንግሥት፣ በክልሎቹና በማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች ይተገበራል። ከፍተኛ ሥጋት ባለባቸው፣ በተለይም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በገለልተኛ ሦስተኛ ወገን አካላት ተግባራዊ ይሆናል፤›› ሲል ባንኩ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በበኩሉ የዓለም ባንክ ቦርድ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችንና ነዋሪዎችን ለመደገፍ የ300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማፅደቁ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ያለውን አሁንም ደካማ የሆነ የሰላም ሁኔታ ሊያናጋ ይችላል የሚል ቅሬታውን አሰምቷል።
ዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት መረጃዎችን በማውጣት የሚታወቀው ዴቮክስ የተሰኘው የዜና አውታር ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ያገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ ባወጣው ዘገባ፣ የዓለም ባንክ ቦርድ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ያፀደቀውን የገንዘብ ድጋፍ ሁኔታዎች እስኪጠሩ ድረስ እንዲያዘገይ ለማሳመን ኮሚሽኑ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድቷል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የዓለም ባንክ ባለድርሻ አካል ባይሆንም፣ ባንኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታን እስኪጠራና ነባራዊ ሁኔታውን ለመገምገም የገንዘብ ድጋፉን ከማፅደቅ ተቆጥቦ ጊዜ እንዲወሰድ የማግባባት ጥረት ማድረጉን፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቁት የዜና አውታሩ ዘግቧል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ለዴቮክስ ሰጡት በተባለው የኢሜይል ምላሽ፣ ‹‹ለእኛ በሰሜን ኢትዮጵያ ለማካሄድ የታቀደውን መልሶ ግንባታ በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል የተረጋጋ የሰላም ሁኔታ አለ ብለን አናምንም፣ የሰላም ሁኔታው በጣም ደካማ ነው። ከዚህ አንፃር የዓለም ባንክ በጦርነቱ ለተጎዱ አካቢቢዎች መልሶ ግንባታ ያፀደቀው የ300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ወቅቱን ያላገናዘበና አሁን ካለው የፖለቲካ አለመግባባት አንፃር ተቃራኒ ውጤት ያስከትላል የሚል ሥጋት አለን፤›› ብለዋል።