Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከኑሮ ውድነቱ በላይ የብልፅግና አመራሮች የእርስ በርስ እሰጥ አገባ ለአገር ሥጋት መሆኑን...

ከኑሮ ውድነቱ በላይ የብልፅግና አመራሮች የእርስ በርስ እሰጥ አገባ ለአገር ሥጋት መሆኑን ኢዜማ አስታወቀ

ቀን:

ብልፅግና አገር አሻግራለሁ ቢልም ራሱ ችግር ውስጥ ገብቷል ብሏል

ለአምስት ዓመታት ሥልጣን በመረከብ ኢትዮጵያን አበለፅጋለሁ፣ ወደፊት አሻግራታለሁ፣ ያለው ብልፅግና ፓርቲ ራሱ ችግር ውስጥ መግባቱን፣ የኢትጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡ የብልፅግና ፓርቲ አካላት የእርስ በርስ እሰጥ አገባ ለአገር ሥጋት መፍጠሩንም የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው የበላይ ኃላፊዎች ሐሙስ ሚያዚያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ወቅታዊ ባሏቸው አምስት ጉዳዮች ላይ በተለይም የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ የከተማ መሬት ወረራ፣ የፀጥታ ችግር፣ ሃይማኖት ተኮር ችግሮችና በመንግሥት አካላት መካከል የሚታዩ እርስ በርስ መፋጠጦችና አለመግባባቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘመናት በተለያየ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የነበረች፣ አሁንም ያለች፣ ለወደፊትም የምትኖር አገር ናት፡፡ አገር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ችግር በሚገባበት ወቅትና ሥልጣን ላይ ያለው አካል መምራት በማይችልበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹መላ አለው›› የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በጣሊያን፣ በቱርክ፣ በሶማሊያና በሌሎች በርካታ ወረራዎችና ወረርሽኞች ወቅት አገር የቀጠለበት ታሪክ የሚታወስ መሆኑን የገለጹት አቶ የሽዋስ፣ በብልፅግና ወይም ሌሎች የሕዝብ ወኪል ነን በሚሉ አካላት የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ፣  ‹‹የአማራና የኦሮሞን ሕዝብ ማንም እየተነሳ እንደ ብርጭቆ የሚያጋጨው ሳይሆን፣ አብሮ የኖረና ለወደፊትም አብሮ የሚኖር በርካታ እሴቶች ያሉት ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሥልጣንን በአደራ የተቀበለው ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊነቱን እየተወጣ አለመሆኑን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ ገዥው ፓርቲ ኃላፊነቱን በመዘንጋት በተለይም የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመልካም አስተዳደርና መሰል ጥያቄዎችን መመለስ ሲያቅተው ሌላ የታሪክ ትርክት በመፍጠር ተከተሉኝ እያለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ያሉ ባለሥልጣናት በጭንቅ ጊዜ አገርን የማሻገር ጥበብ ሊያሳዩ የሚገባ ቢሆንም፣ በብልፅግና ፓርቲ አመራሮች መካከል እየታየ ያለው እሰጥ አገባ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካካል እንኳ መከሰት የሌለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 ‹‹በእኛ እምነት ካልቻሉ በር ዘግተውና ሥልጣናቸውን አስረክበው እንደሌላው ፓርቲ መደባደብም ሆነ መጨቃጨቅ አለባቸው እንጂ፣ ሕዝብ አናት ላይ መደባደብና ሕዝብ ትከሻ ላይ የራስን ስሜት ማገንፈል አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

 ‹‹አስቦ መናገር፣ መተግበርና በኃላፊነት መንቀሳቀስ፤›› ያስፈልጋል ያሉት አቶ የሽዋስ፣ ‹‹ይህ ጥጋብና ትዕቢት፣ አይደለም የዓመታት የወራት ዕድሜ የለውም፣ በጣም ብዙ ትዕቢተኛ ሲተነፍስበት ያየንበት ጊዜ ስለነበር፣ ትዕቢት የማያዋጣ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ መናገር እፈልጋሁ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኢዜማ በመግለጫው መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከውጭ በአፋጣኝ የሚገቡበት አማራጮችን በመጠቀም ሁሉም ዜጎችን እኩል ሊጠቀሙ የሚችሉበት ፍትሐዊ የሆነ የሥርጭት ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ ይህንን ለማስተጓጎል በሚጥሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ተጠያቂነት እንዲያሰፍን መንግሥትን ጠይቋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረቱ ሲሚንቶን የመሳሰሉ የግንባታ ዕቃዎችን በተመለከተ ፋብሪካዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን፣ በየአካባቢው በጥቅም ትስስር የተተበተቡ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመበጣጠስ በቀጥታ ተጠቃሚዎች ጋር የሚደርሱበትን ፍትሐዊ አሠራር እንዲዘረጋም ኢዜማ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ ያልሆኑ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ገደብ እንዲደረግ፣ መሠረታዊ ላልሆኑ ዕቃዎች የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቀድና ክልከላ እንዲቀመጥ፣ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣባቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለጊዜው በመግታት ምርታማነትን የሚያበረታቱ የዘመቻ ሥራዎችን በማስጀመር የአጭር ጊዜ መፍትሔ እንዲነደፍ ጠይቋል፡፡

በረዥም ጊዜ ዕቅድ የመሬት ፖሊሲውን በመለወጥ ዜጎችን ከመንግሥት ጭሰኝነት ማላቀቅ የግድ መሆኑን ገዥው ፓርቲ እንዲረዳ ኢዜማ አሳስቧል፡፡

ኢዜማ የተጀመረው የአገራዊ ምክክር መድረክ ተገቢ ትኩረት እንዲያገኝ፣ መንግሥት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጿል፡፡

መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ካደረገ በቤቶች ልማት ሥራ ከተሰማራ ኩባንያ ጋር በመንግሥት በኩል ተደርጓል የተባለው የቤቶች ግንባታ ፊርማና ስምምነት የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱን፣ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ቃል የገባውን አንድ ሚሊዮን ቤቶች ለመገንባት 1.6 ትሪሊዮን ብር የሚያስፈልገው ቢሆንም ይህንንም ማድረግ እንደማይችል የጠቀሰው ኢዜማ በዚህ ምክንያት ‹‹ሕዝቡ ባዶ ተስፋ ብቻ ታቅፎ እንዲኖር ተፈርዶበታል፤›› ብሏል፡፡

በርካታ አገራዊ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፣ ‹‹ራሱን አገራዊ ፓርቲ ነኝ ብሎ የሚያሞካሸው ብልፅግና ፓርቲ፣ ከመጋረጃ ጀርባ ያለው ትክክለኛ ማንነቱ ተገልጦ የብሔር ፓርቲ መሆኑን አደባባይ በወጣው የባለሥልጣናቱ ንትርክ በይፋ አስመስክሯል፤›› ብሏል፡፡

ክልሎችን ለመምራት በመንበሩ የተቀመጡ የብልፅግና አመራሮች ተናበውና ተቀናጅተው አገሪቱን ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ፈተና ለማውጣት በጋራ በመሥራት ከሕዝቡ አንድ ዕርምጃ ቀድመው የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ሲገባቸው፣ መሽቶ በነጋ ቁጥር እርስ በርስ እየተናከሱ፣ አለፍ ሲልም ለፀብ እየተጋበዙ ከኑሮ ውድነቱ በላይ ራሳቸው አመራሮቹ ለአገር ሥጋት መሆናቸውን ኢዜማ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በብልፅግና ቤት ውስጥ በሚፈጠር የሥልጣን ሽኩቻ ለማሸነፍ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ከችግሩ የማምለጫ ሥልት ተደርጎ በተደጋጋሚ መወሰዱ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ እውነታ እንደሆነ የገለጸው ኢዜማ፣ ‹‹ሁሉም አካላት እንዲረዱ የሚያስፈልገው በሚነድ እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ፣ ይዋል ይደር እንጂ ሁሉንም ማቃጠሉ አይቀሬ ነው፤›› ሲል ኢዜማ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...