Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፍልሰትና የሥራ ላይ ፆታዊ ጥቃት ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸው ተገለጸ

ፍልሰትና የሥራ ላይ ፆታዊ ጥቃት ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

በየዓመቱ ከ150 ሺሕ በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን ለሕይወት አሥጊና መደበኛ ባልሆነ የፍልሰት መተላለፊያ፣ ወደ ተለያዩ አገሮች እንደሚሄዱና የሥራ ላይ ፆታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) እጅግ አሳሳቢ ባላቸው በሦስት ፈርጆች ላይ ኢትዮጵያ የዓለም የሥራ ድርጀት ስምምነቶችን  እንድትቀበል ለማድረግ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋዊ ዘመቻ መጀመሩን ባስታወቀበት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡

የፍልሰት ሠራተኞችን፣ የቤት ሠራተኞችንና የሥራ ላይ ጥቃትና ትንኮሳን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕጓ አካል ለማድረግ በይፋ በተጀመረው ዘመቻ ላይ የተገኙት የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣  ‹‹ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሠራተኞች ወደ ተለያዩ አገሮች እንደሚፈልሱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ የቤት ውስጥ ሥራ አገልግሎት የሚሰጡ የቤት ሠራተኞችና የሥራ ላይ ጥቃትና ትንኮሳ በስፋት የሚታይባት ናት፤›› ብለዋል፡፡

በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ የሠራተኞች ፍልሰት ምንጭ እንድትሆን አድርጓታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በየዓመቱ 150 ሺሕ ወጣቶች አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ይወጣሉ ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ደግሞ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 839 ሺሕ ኢትዮጵውያን ወደ ውጭ መፍለሳቸውን ይገልጻል ብለው፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ የኢትዮጵያ ትልቅ ችግር እየሆነም ነው፡፡ እንደ ሠራተኞች ፍልሰት ሁሉ የሥራ ላይ ጥቃትና ትንኮሳ ሌላው የኢትዮጵያ አሳሳቢ ችግር ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ በሥራ ቦታ የሚደርስ ጥቃትና ትንኮሳ በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ፣ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋም፣ በከተማም ሆነ በገጠር ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹ይህ አሳሳቢ ችግር ካልተፈታ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፤›› ብለዋል፡፡

በሥራ ላይ ጥቃትና ትንኮሳ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ እንደሆነ የሚያመለክተው የኢሠማኮ መረጃ፣ የዓለም ባንክ የ2019 ዓ.ም. ጥናት የሚያሳየውም 35 በመቶ ሴቶች በቅርብ አጋሮቻቸው ወይም ባልታወቁ ሰዎች አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል ይላል፡፡ ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ የከፋ የሚባል ደረጃ ላይ ስለመድረሱም አቶ ካሳሁን ጠቅሰዋል፡፡ ኢሠማኮ እነዚህን ጉዳዮች የተመለከቱ ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎችን፣ ኢትዮጵያ የሕጓ አካል ማድረግ ችግሩን ለመከላከልና የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ለማድረግ ስለሚረዳ፣ በዘመቻ ጭምር መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶቹን የሕግ አካል ሊያደርገው ይገባል ብሎ መነሳቱን አስታውቀዋል፡፡

ኢሠማኮ ሦስተኛው አድርጎ ያቀረበውና እሠራበታለሁ ያለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የቤት ሠራተኞችን የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ ጉዳይ ላይ የዓለም የሥራ ድርጅት ያስቀመጠውን ስምምነቶች ኢትዮጵያ ካልተቀበለችና የሕጓ አካል ካላደረገች፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የቤት ሠራተኞች ለሰብዓዊ መብት ረገጣና ተያያዥ ችግሮች ይጋለጣሉ ብሏል፡፡

በእነዚህ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሕጋዊ ጥበቃ በማድረግ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተደረገባቸው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያም እነዚህን ስምምነቶች የሕግ አካል ማድረግ ለእያንዳንዱ ዘርፍም ዝርዝር ሕግን ማስቀመጥ ይገባል ተብሏል፡፡

በመሆኑም በሦስቱም ጉዳዮች ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች ለማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ቀውስ ምክንያት እየሆኑ በመሄዳቸው፣ የዓለም አቀፉ ስምምነት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያስቀመጣቸውን ሕግጋቶች ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕጓ አካል በማድረግ የሕግ ከለላና ጥበቃ እንዲካሄድ አቶ ካሳሁን አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በእነዚህ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሕጓ አካል ሳታደርግ መቆየቷን የሚያመለክተው የኢሠማኮ መረጃ፣ ስምምነቱን የሕግ አካል አለማድረጉ ጉዳቱ እየሰፋ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡

የሚፈልሱ ሠራተኞችን፣ የቤት ሠራተኞችን የሥራ ላይ ጥቃትና ትንኮሳ የመሳሰሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርጉም፣ ለእነዚህ ተግዳሮቶችና አደጋዎች ፖሊሲዎችና ሕጎች ቢወሰኑም፣ ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንፃር ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

በዓለም አቀፉ ስምምነት መሠረት እነዚህ ሦስት ጉዳዮች ዝርዝር ሕግ ወጥቶላቸው የመብት ጥሰት እንዳይኖር በሕግ የተቀመጠ አሠራር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ኢሠማኮ ከዓርብ ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ስምምነቶቹ የኢትዮጵያ የሕጓ አካል እስኪሆኑ ድረስ እንደሚታገል አስታውቋል፡፡

የዓርቡ ዘመቻ ሲጀመር የዓለም ሠራተኞች የኢትዮጵያ ተወካይ የአሠሪ ፌዴሬሽኖች፣ አመራሮች፣ የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸውና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...