የግሉ ዘርፍ በስፋት የተሰማራባቸው የመካካለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን አስመልክተው የወጡ ሕጎች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ፣ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አቅም ሊጎለብት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ የጀርመን የፌዴራል ኢኮኖሚ ትብብርና ዕድገት ሚኒስቴር ፈጻሚ የሆነው የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂአይዜድ) የግሉ ዘርፍ ዕድገት በኢትዮጵያ (Private Sector Development in Ethiopia(PSD-E) በሚል ከዚህ ቀደም ስምምነት የተደረገበትን ፕሮጀክት በይፋ ወደ ሥራ ባስገቡበት ወቅት ነው፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሚሸከምበት ደረጃ እንዲደርስ የግሉ ዘርፍ ሚናው ጉልህ በመሆኑ ለዘርፉ ዕድገትም ሆነ የዕቅድ አፈጻጸም ስኬት የተደላደለ የቢዝነስ አመቺነት ሊፈጠርለት እንደሚገባ በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ይፋ በተደረገው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ ጥናት ላይ ተጠቅሷል፡፡
በጀርመን መንግሥት የኢኮኖሚ ትብብር ልማት ሚኒስቴር የፋይናስ ድጋፍ የሚደረግለት ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦች፣ በሐረሪና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ እንደተናገሩት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ የተሻለ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
አገሪቱ በዚህ ወቅትም ሆነ በቀጣዮቹ ዓመታት በምትተግብረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አውራ አንቀሳቃሹ የግሉ ዘርፍ እንደሚሆን የተናገሩት ሚንስትር ዴኤታው፣ በዚህም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተግባር ተኮር ፖሊሲ መሠረት አድርጎ የቴክኖሎጂ ለውጦች ከግንዛቤ የከተተ፣ ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ እንዲሁም በገበያ ውስጥ የሚገጥመውን የገበያ እጥረት ችግሮች በመፍታት ረገድ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንዳስታወቁት፣ የተቃዱና የታሰቡ ፕሮጀክቶች በተወጡነት ልክ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተፈለገ የቢሮክራሲ ውጣውረዶችን ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በጂአይዜድ የግል ዘርፍ ልማት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ አረጋሽ አስፋው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ጂአይዜድ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በቀጥታ ሳይሆን የሚደግፈው እነዚህን አካላት የሚያግዙትን መንግሥታዊ ተቋማትን አቅም በማጠናከር ነው፡፡
‹‹ሁል ጊዜ በዕርዳታ ድርጅት ድጋፍ በመደገፍ ሳይሆን ያለውን መዋቅር በምን ዓይነት ሁኔታ በማጠናከር ወደ ፊት መቀጠል ይቻላል?›› የሚለውን ድርጅቱ የሚደግፍ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊዋ፣ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፉትን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አቅም የማጎልበት ሥራ በፕሮጀክቱ የሚሠራ ቁልፍ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቷ ከላይ የተጠቀሱትን ኢንዱስትሪዎችን የተመለከቱ በርካታ የወጡ ሕጎች እንዳሉ ያስታወሱት ወ/ሮ አረጋሽ፣ ለአብነትም የአሥር ዓመታት መሪ የልማት ዕቅዱ፣ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ላይ የሰፈሩት ጉዳዮች ምን ያህል ወደ ታች ወርደው እየተሠራባቸው ይገኛሉ? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡በመሆኑም ይህንን ጥያቄ በመመለስ ሒደት ውስጥ አስፈጻሚ የሆኑትን የመንግሥት ተቋማት አቅም የማጠናከር ሥራ የሚሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በሻገር ኢንዱስትሪዎቹንና የሰው ኃይሉን በተመለከተ የአገናኝነት ሚና ያላቸውን በተለምዶ ኢንኩቤተሮች፣ አክስለሬተሮች የሚባሉትን ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ልክ የሚያድጉበትንና እነሱም ለጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች በሥልጠና መልክ ትምህርት የሚሰጡበትን መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የፕሮጀክቱ ግብ እንደሆነ ወ/ሮ አረጋሽ አስረድተዋል፡፡
ካለፈው ዘጠኝ ወር አንስቶ ፕሮጀክቱ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደቆየ የተናገሩት ወ/ሮ አረጋሽ፣ ከዚህ በኋላ ለፕሮጀክቱ በተመለመሉት ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች አማካኝነት የተግባር ሥራውን የሚጀምር ይሆናል ብለዋል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ጂኤዜድ መሠረታዊ ሚናው የዕውቀት ሽግግሩን የተመለከተው ተግባር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በሻገር ፋይናንስ የሚያቀርቡ ድርጅቶችን በመለየት እነዚህን የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡