ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መግባት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ተጨማሪ ማበረታቻዎችን ለመስጠት ጥናት እየተደረገ መሆኑን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች የውጭ ባለሀብቶች መሆናቸውን፣ ይህም ፓርኮቹ ከተገነቡበት የአገር ውስጥ አምራቾችን የማሳደግ ዓላማ አንፃር ውጤታማ እንዳልሆነ የሚያሳይ መሆኑን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ዳይሬክተር አቶ አያልነህ አባዋ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለይም ማሽነሪዎችን ማስገባት የሚችሉበት ማበረታቻ በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ማሽነሪዎችን ከውጭ ለማስመጣት ጥያቄ አቅርበው ከሁለት ዓመታት በላይ የጠበቁና ምላሽ ያላገኙ ድርጅቶች መኖራቸውን አክለዋል። በተጨማሪም ብድር አግኝተው ወደ ሥራ ለመግባትም እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ ለዚህም የባንኮች የብድር አሰጣጥ ሒደት በርካታ መሥፈርቶች የሚጠየቁበት መሆኑ ዋነኛው ምክንያት ነው ብለዋል።
የኢኬቲ ትሬዲንግ ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ አሰፋ አያሌው በበኩላቸው፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበርና ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል። ቦታ ከማግኘት ጀምሮ ያሉት ሒደቶች ቀላል አለመሆናቸውንና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ማበረታቻዎች አለመኖራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ወደ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለመግባት የነበራቸውን ፍላጎት በመተው፣ በነበራቸው ፋብሪካ ላይ ማስፋፊያ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከፍተኛ ውድድር የሚጠበቅባቸው በመሆኑና በማምረት ዘርፍ ያላቸው ልምድ አነስተኛ ስለሚሆን ፈታኝ እንደሚሆንባቸው የሚገልጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል፣ ለዚህም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአብዛኛው ከማምረት ይልቅ በንግድ ዘርፍ የመሰማራት ልምድ እንዳለ ገልጸው፣ በተለይ የማምረቻ ዘርፉ የሚጠይቀውን በረዥም ጊዜ የሚገኝ ትርፍ አውቆ መግባት ላይ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ግንዛቤ ሊፈጠርላቸውና እንዲበረታቱም ጥቅማ ጥቅሞች ሊሰጧቸው ይገባል ይላሉ። የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲመጡ የራሳቸውን ማሽነሪዎች ማምጣት ስለሚችሉ በቀላሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን እነዚህን የካፒታል ዕቃዎች በቀላሉ ማስገባት አለመቻላቸው አስቸጋሪ እንደሚያደርግባቸው አክለዋል።
ወደ ማምረት የመግባት ልምድ ያላቸውም ቢሆኑ ያመረቱትን መሸጥ የሚችሉበት ገበያ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ለውጭ ገበያ ብቻ እንዲቀርቡ ከማድረግ ይልቅ ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የሚነሳባቸውን የጥራትና ተወዳዳሪነት ችግር እንዲፈቱ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል።
የአገር ውስጥ ባለሀብቶቹ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዳይገቡ የሚያደርጓቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለማሻሻልና አዳዲስ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥናት እያደረገ መሆኑን አቶ አያልነህ ተናግረዋል።
ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ በመሆን የሚደረገው ጥናት በ2014 በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ፣ የተጠየቁትን ማበረታቻዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በተለይም ብድርን በተመለከተ በባለሀብቶችና በባንኮች መካከል ልዩነት መኖሩን ገልጸው፣ ‹‹ባንኮች ተበዳሪ አጣን ሲሉ፣ ባለሀብቶች ደግሞ አበዳሪ አጣን ይላሉ፤›› ብለዋል። ይህንን ልዩነት በማጥናትም በባንኮች ዘንድ የሚጠየቁ ወይም ባለሀብቶች ማሟላት የሚጠበቅባቸው መሥፈርቶች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ጥናት መሆኑን አክለዋል።