Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውጭ ኩባንያ የተሸጠው ኤድና ሞል ታድሶ ሲጠናቀቅ ይከራያል መባሉ  ግርታ ፈጥሯል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሕንፃውን በሚመለከት ዝምታን መርጧል

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም. ላይ በተደረገው ጨረታ፣ ቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኘውን ኤድናሞል ሕንፃ በ810 ሚሊዮን ብር የገዛው የቻይናው ኩባንያ ኢስት ስቲል፣ ሕንፃውን አድሶ ለገበያ ማዕከልነት እንደሚያከራይ መግለጹ ከኢንቨስትመንት ሕጉ ጋር በተያያዘ ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ግርታ ፈጥሯል፡፡

ኤድና ሞልን የገዛው የውጭ ኩባንያው በምን ዓይነት አግባብ ሕንፃውን ለማከራየት እንዳሰበ ያልገለጸ ከመሆኑም ሌላ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በበኩሉ ኩባንያው ሕንፃውን የማከራየት አገልግሎት መስጠት የመቻሉን ጉዳይ ጥናት እያደረገበት መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በተደረገው ጨረታ ኤድናሞል ሕንፃ በ810 ሚሊዮን ብር የገዛው የቻይናው ኢስት ስቲል ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለ13 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ሕንፃ አድሶ ዘመናዊ የገበያ ማዕከልነት ሊያቀርብ ማቀዱን ከሁለት ሳምንት በፊት ሰኞ፣ መጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕንፃው ውስጥ በለጠፈው ማስታወቂያ  ገልጿል፡፡ ለዘጠኝ ወራት ሕንፃውን ለመረከብ የሚያስችሉትን ሥራዎች ሲያከናውን እንደነበር በማስታወቂየው የገለጸው ኩባንያው በቀናት ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃውን ሙሉ ለሙሉ እንደሚረከብ አክሏል፡፡

ኢስት ስቲል ሕንፃውን ከተረከበ በኋላ ዘመናዊ ሞል ለማድረግ ዕድሳት እንደሚያደርግ አስታውቆ ተከራዮች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ንብረታቸውን እንዲያወጡ ጠይቋል፡፡ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ያልወጣ ንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት እንደማይወስድ ከገለጸ ከሳምት በኋላ በተሰጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ንብረታቸውን ያላወጡ ተከራዮች ቢኖሩም ከሰኞ፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሕንፃው ታሽጓለ፡፡

ኤድና ሞልን እንደተረከበ የዕድሳት ሥራ እንደሚጀምር ያስታወቀው ኢስት ስቲል የሕንፃው ዕድሳት ሲጠናቀቅ አሁን እንዲወጡ የተደረጉትም ሆነ ማንኛውም የሕንፃውን ክፍሎች በመደብርነት መከራየት የሚፈልጉ ተከራዮች አዲስ የኪራይ ውል መፈጸም እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

የቻይናው ኩባንያ ኢስት ስቲል ሕንፃውን ለለኪራይ ሊያቀርብ መሆኑ ለዓመታት ገበያ የገነቡት የኤድና ሞል ተከራዮች የቀድሞ ቦታቸውን እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ባለሀብቶች የሕንፃ ባለቤት ከሆኑ በኋላ ማከራየት የመቻላቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡

የሕግ ባለሙያ አቶ ሚካኤል ተሾመ ለሪፖርተር እንደተናገሩት በ2012 ዓ.ም. የወጣው የኢንቨስትመንት ደንብ አንቀጽ አራት ንዑስ አንቀጽ አምስት የችርቻሮ ንግድን የሚፈቅደው ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ነው፡፡ ‹‹ችርቻሮ ንግድ›› የሚለው የሕንፃ  ኪራይንም እንደሚያካትት የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው የተለየ ስምምነት እስከሌለ ድረስ ይሄ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች የተከለከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም. ወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ የተለዩ አሠራሮችን እንደሚመለከት ደንግጓል፡፡ የቦርዱን ሥልጣንና ተግባር የሚወስነው የአዋጁ አንቀጽ 31 በንዑስ አንቀጽ አንድ/ሸ ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ዘርፍ አካላት ጋር ተገቢውን ምክክር በማድረግ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት የሚካሄዱ፣ ወይም ለአገር ውስጥ ባለሀብት የተከለሉ፣ ወይም ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብት የቅንጅት ኢንቨስትመንት የተከለሉ የኢንቨስትመንት መስኮች ለውጭ ባለሀብት ክፍት እንዲሆኑ እንደሚወስን አስቀምጧል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢስት ስቲል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዩ ጀን ሕንፃውን የማከራየቱ ሐሳብ ላይ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ስለመኖሩ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ምንም አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው ጉዳዩ ለኮሚሽኑ አዲስ በመሆኑ የተዋቀረ ቡድን በጉዳዩ ላይ ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ኮሚሽኑ ጉዳዩን እየተመለከተው ስለሆነ አሁን ላይ ምንም መረጃ መስጠት አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

ባለሰባት ሕንፃው የመዝናኛ ማዕከል ኤድና ሞል ከዚህ ቀደም የታዋቂው ባለሀብት ተክለ ብርሃን አምባዬ የነበረ ሲሆን፣ ባለሀብቱ ሕንፃውን በማስያዝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ ሊመልሱ ባለመቻቸው ሕንፃው በሐራጅ ተሸጧል፡፡ በ2004 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የቻይናው ኢስት ስቲል ኩባንያ ሕንፃውን የገዛው ለጨረታው በመነሻነት ከቀረበው 237 ቢሊዮን ብር ከሦስት እጥፍ በላይ 810 ሚሊዮን ብር በማቅረብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች