Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በተለመዱት መፍትሔዎች የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት አይቻልም

በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ እየቆነጠጠ ነው፡፡ የጉዳት መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉንም የዓለማችንን አገሮች አዳርሷል፡፡ ሀብታም የሚባሉ አገሮችን ሳይቀር እየፈተነ ነው፡፡ ለክፉ ቀን ያሉትን ጥሪት እያስወጣቸው መሆኑንም እያየን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የሀብት መጠናችሁ የትየለሌ ከሆነው ከእነዚህ አገሮች መካከል አንዳንዶቹ ለዜጎቻቸው በሚያቀርቡት ነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ ከማድረጋቸው ባለፈ ነዳጅ በራሽን እስከማደል መድረሳቸው የችግሩን ጥልቀትና ሁሉንም የዓለም አገት የሚነካ ተግዳሮት መሆኑን መረዳት ይቻላል።

 ችግሩን እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ደሃ አገሮች አንፃር ስንመለከተው ደግሞ የጉዳት መጠኑ ሰፊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከነዳጅ ምርት ወጣ ብለን ብንመለከትም መሠረታዊ የሚባሉት የዓለም መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች የሆኑት እንደ ስንዴና የምግብ ዘይት ያሉ ምርቶችንም በስፋት አምርተው ለዓለም ገበያ በማቅረብ የሚታወቁት እነዚሁ ሁለቱ ተፋላሚ አገሮች ናቸው፡፡ የሁለቱ አገሮች ግጭት በፈጠረው ቀውስ ሳቢያም በእስያና በአፍሪካ የሚገኙ በማደግ ላይና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ነዳጅንም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦችን ዋጋ ጨምረው እንኳን መግዛት ተቸግረው የሕዝባቸውን የዳቦ ጥያቄ ለመመለስ ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ 

ጦርነቱ ካልቆመ ከዚህም በኋላ የበለጠ ተጎጂዎች የሚሆኑት እነዚሁ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ደሃ አገሮች ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ በሆነ አጋጣሚ ጦርነቱ መቆም ቢችል እንኳን የዓለም ኢኮኖሚ መልሶ ለማገገም ጊዜ ይወስዳልና የዓለም ኢኮኖሚ በፈተና ውስጥ መቆየቱ አይቀሬ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮች ደግሞ ቢያንስ ወደ ቀድሞ ቁመናቸው ለመመለስ የበለጠ ጊዜ ይወስድባቸዋል።

አደግን ከሚባሉት አገሮች ሥነ ባህሪ እንደምንረዳው በዚህ ጦርነት ያጡትን ለማካካስ የሚዘይዱት መላ ደሃውን በመጫን ስለሚሆን መጪው ጊዜ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላላቸው ደሃ አገሮች ከባድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ 

አሁናዊውንና መጪውን ጊዜ ከኢትዮጵያ አንፃር ስናየው ደግሞ ነገሩን የሚያከብዱ ፈርጀ ብዙ ጣጣዎች አሉ፡፡ የብሔር ግጭትና ያልተረጋጋው ፖለቲካዊ ሁኔታ አንዱ ነው፡፡ በየቦታው ያሉ ግጭቶች መቋጫቸው አልታወቀም፡፡ ለተከታታይ ዓመታት በዋጋ ንረት ስትነረት የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ገበያውን ማረጋጋት ባልቻለችበት ሁኔታ ይህ ጦርነት ይዞት የመጣውና ሊያመጣ የሚችለው ጦስ የዋጋ ንረቱን አሁን ካለበት በላይ የከፋ ያደርገዋል የሚል ሥጋት ያሳድራል፡፡

ለዚህም ነው ከፊታችን የሚጠብቀንን ብርቱ ፈተናዎች በዘዴ ለማለፍ ምን ዓይነት የመፍትሔ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢና መሠረታዊ የሚሆነው። 

ይህንን ጥያቄ መመለስ ወቅታዊና ትለቁ የመንግሥት የቤት ሥራ ብቻ ሳይሆን ከተለመደው የመፍትሔ መንገድ ተሻግሮ ማየትን የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም ግሽበትን ለመግታት የተለመዱት የመፍትሔ ዕርምጃዎች ጥቅም ላይ ውለው እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ወይም የዋጋ መረጋጋትን ሲያስከትሉ አልተስተዋለም። በግልጽ እያየን ያለነው የዋጋ ንረቱን ያወርዳሉ የተባሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎች በሙሉ በታሰበው ልክ ግብ አለመምታታቸውን ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን መቀነስ ይቅርና ማረጋጋትም አልቻሉም፡፡ እስከ ዛሬ የተወሰዱት ዕርምጃዎች እሳት ከማጥፋት የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ ጭራሽ መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ምርቶች ፍፁም ባልተጠበቀ መልኩ ዋጋቸው እየተሰቀለ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱን ለመነቀስ ለተከታታይ ዓመታት የተወሰዱት የመፍትሔ ዕርምጃዎች ውጤት ይህ ከሆነማርሽ መቀየር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለምን የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ በመያዝ ቀጣዩን መፍትሔ ማበጀት ካልተቻለ፣ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ በፍፁም መውጣት አትችልም፡፡ 

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ችግሩን ለመቋቋም ሊወስድ የሚችለው የፖሊሲ ዕርምጃ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ እሳት ማጥፋትን ብቻ ታሳቢ ካደረገ ችግሩን ያብሰዋል፡፡ የሕዝብ ብሶትን ያፋፍማል፡፡  

ስለዚህ መንግሥት በዚህ ወቅት ውስጣዊ ቀውሶችና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን የዋጋ ንረት ለመቀነስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንንም ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም መፍጠር የግድ ይለዋል፡፡ 

ገበያው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ የሚያስችል አሠራር መዘርጋትና ገበያውን ሊያውኩ የሚችሉ ማንኛውም ክስተቶች መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች ቢያንስ ከውጭ እንዲገቡ በመንግሥት የተፈቀዱ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጠነ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻል ትልቁ የመንግሥት የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡

በተለይ አሁን ላይ ከታክስ ነፃ የሚገቡ ምርቶችን፣ በፍራንኮ ቫሉታና በተመሳሳይ መንገድ የሚገቡ ምርቶች በትክክል በተመጣጠነ ዋጋ ገበያ ላይ መሸጣቸውን ጭምር ለመቆጣጠር ከቀደመው የበለጠ መጠናከር ያስፈልጋል፡፡ 

ለምሳሌ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ አድርጎ መንግሥት የሚያስገባውን የነዳጅ ምርት በከፍተኛ የገቢ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በድጎማ ሲያቀርብ የነበረበትን ለዘመናት የቆየ አሠራር ፈትሾ ማስተካከሉ በጎ ጅምር ነው።

መንግሥት ድጎማውን በከፊል አስቀርቶ መደጎም ያለበትን በመለየት ተጠቃሚ ለማድረግ መጣሩ የሚደነቅ ሆኖ ሳለ፣ የአዲስ አበባ ታክሲዎች የነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ ለመሆን በተሽከርካሪያቸው ላይ ጂፒኤስ ማስገጠም አለባቸው የሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ መውጣቱ ደግሞ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየጣረ ነው ወይስ በተቃራኒው እየሠራ ነው ያስብላል። 

የታክሲዎች ጂፒኤስ ማስግጠም የነዳጅ ድጎማው በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ መቆጣጠሪያ ካልሆነ ወይም ከዚህ ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ከሌለው ሌላ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም። ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተወሰነው ነዳጅን ቆጥቦ ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን በዋጋ ንረት ላይ የሚኖረውን ቀጥተኛ ተፅዕኖ ለማቅለልና ማኅበረሰቡን ለመጥቀም ሆኖ ሳለእነዚሁኑ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በነዳጅ ድጎማው ከሚያገኙት ጥቅም ለባሰ ወጪ የሚዳረግ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ ተገቢነትን መፈተሽ ያስፈልጋል። ተገቢ ቢሆን እንኳ የግድ አሁን መሆንና መፈጸም ያለበት ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ይህ ካልሆነ ግን በተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ብቻ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሚያወጡት ተጨማሪ ወጪ የዋጋ ንረትን ማባባሱ አይቀሬ ነው።

በአጠቃላይ እንደ ሌላው ጊዜ አጋጣሚ ተገኘ ተብሎ ለዘርፉ መነሳትን፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መሯሯጥን መንግሥት ቀይ መስመር ሊያሰምርበት ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በግለሰብ ደረጃ ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች የትርፍ ህዳግ ተቀምጦላቸው እንዲሸጡ ማድረግ ካልተቻለ ይህንን ጊዜ ማለፍ ከባድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ተቸግራ የአርቴፊሻልጉር (ሂውማን ሔር) ገበያ በአገር ውስጥ ከደራ መንግሥት ራሱንም ባንኮቹንም ሊፈትሽ ግድ ይለዋል። የአገሪቱ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፎች በውጭ ምንዛሪ ድርቅ ተመተውየተንደላቀቁ አዲስ አውቶሞቢሎች ገበያ በአገር ውስጥ ከደራ መንግሥት ራሱን መፈተሽ አለበት። ቅድሚያ መስጠት የሚገባውን ቅድሚያ መስጠት አለበት።

በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ እጅግ አደገኛ እየሆነ ያለው ከልክ ያለፈ የትርፍ ህዳግ ለመቆጣጠር ከተፈለገ በሕግ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የብዙኃኑን ጥያቄ ለመመለስ ቢያንስ ሰዎች መሠረታዊ የሚባሉ ምግብ ነክ ምርቶችን እንዲገኙ በጊዜያነትም ቢሆን ወጣ ያሉ አሠራሮችን መከተል ግድ ስለሚል ነው፡፡ አንዳንዴ የገበያ ሕጉ ወይም የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ከሚነግሩን ውጪ በመሄድ የችግሩን ወቅት ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለጦርነት ወቅት ብቻ ሳይሆን ሕዝብን ለማኖር ሲባል ሕዝብ ላይ ከሚከፈት ኢኮኖሚያዊ ጦርነት ለመከላከል ሲባል ጠንካራ ሕግና ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችልን ደንብና መመርያ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡  

እስከ ዛሬ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የተወሰዱ ዕርምጃዎች በሙሉ የሚፈለገውን ግብ ያላሳኩበት ምክንያት አንዱ ብልሹ አሠራርና ሌብነትን እንደ ሥራ የያዙ ግለሰቦች በሥራ ሒደቱ ውስጥ በዝተው መገኘታቸው ነውና በዚህ ዙሪያም ጠንከር ያለ ሥራ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ ለማንኛውም የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች ጎን ለጎን ግን በፍፁም መረሳት የሌለባቸው ቁልፍ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ አገራዊ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታዎችን በተቻለ ፍጥነት እንዲስተካከል ማድረግ ነው፡፡ የቱንም ያህል ቢታቀድ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምንም ነገር ማሳካት አይቻልም፡፡ 

ሕዝብ የሚፈልገውን ምርት በአግባቡ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ማድረስ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ የሰላም ዕጦት ለምርታማነት ፀር በመሆኑ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ገበያን ማረጋጋት አይቻልም፡፡ በረባ ባልረባው እዚህም፣ እዚያም የሚታዩ ግጭቶችን አደብ ማስያዙ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተከፈለው መስዋዕትነት እየተከፈለ የኢትዮጵያን ምርታማነት የሚያሳድጉ ሥራዎች ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ 

ከወቅታዊው የዓለም ገበያ የምንረዳው አንድ ነገር እንደ ከዚህ ቀደሙ ስንዴ ለመግዛት የሚንችልበት ጊዜ እየመጣ መሆኑን ነው። ብዙዎች አገሮች የስንዴ ያለህ እያሉ ነውና በዚህ የፍላጎት ዕድገት ውስጥ ተጫርቶ ስንዴ መግዛት ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በፍጥነት መተግበር የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። 

ምናልባት የአንዳንድ የመሠረተ ልማቶች በጀትን ወደ እዚህ በማዞር ቢያንስ የምግብ የዋጋ ንረትን መቀነስ ካልተቻለ ይህንን ወቅት መሻገር ከባድ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ወቅቱን ያገናዘበና የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም የሚበጁ ልዩ የፖሊሲ መፍትሔዎች አሁኑኑ ማፍለቅና መተግበር ያሻናል የምንለው፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት