Monday, December 4, 2023

የወልቃይት ጥያቄ ከየት ወዴት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የወልቃይትን ጉዳይ ቀለል አድርገው ለማቅረብ የሞከሩ አንዳንድ ወገኖች የአማራ ተወላጆች ‹‹ጠገዴ›› ብለው የሚጠሩትን፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ‹‹ፀገዴ›› ብለው ይጠሩታል እያሉ ጉዳዩን ከቋንቋና ከቀዬ ጋር አጋምደው ሊያስቀምጡት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ጉዳዩ የዘዬ ወይም ቀዬ ሳይሆን ትልቅ የፖለቲካ አጀንዳ ነው የሚሉ ወገኖች ግን፣ ወልቃይት የደም መሬት ነው ሲሉት ይደመጣሉ፡፡ ከሁለቱም ጎራ ያልሆኑት ደግሞ የወልቃይት አጀንዳ በመሠረታዊነት አገሪቱ በምትከተለው የፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት ላይ ጥያቄ ያስነሳ፣ ከአካባቢ ሽኩቻነት አልፎ ሁለት ክልሎችን ወደ ጦርነት ያስገባ፣ አለፍ ሲልም በጂኦ ፖለቲካው ረገድ የአገሪቱን የፖለቲካ ገጽታ የሚቀይር ከባድ አጀንዳ መሆኑን ሲናገሩለት ይደመጣል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝን ቦታ በተኩ በሁለት ሳምንታቸው ጎንደር ከተማን ረገጡ፡፡ ከወልቃይት የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ጋር ተገናኙ፡፡ በጊዜው ለኮሚቴው አባላት የወልቃይት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሕጋዊ መንገድ እንደሚፈታም ቃል ገቡ፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) አራት ዓመታት በሥልጣን ላይ አስቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን የወልቃይት ጥያቄ እስከ አሁንም ለመፍታት ቀላል አልሆነም፡፡ 

የወልቃይትን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተለው ጸሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን፣ ለወልቃይት ጉዳይ አለመፈታት አገሪቱን የሚመራውን ብልፅግና ፓርቲን ዋና ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ‹‹ብልፅግና ጊዜ ጠላቱ እንደሆነ ያልተረዳ፣ መሽቶ በነጋ ቁጥር ወደ ውድቀቱ እያመራ መሆኑን ያልተረዳ፣ ራሱን በራሱ የሚበላ ፓርቲ ነው፡፡ በውስጡ በርካታ የፍላጎት ግጭቶች ያለበት ነው፡፡ ወያኔን የአማራ መያዣ ዕዳ አድርጎ ማቆየት የሚፈልግ ኃይል በዚህ ድርጅት ውስጥ አለ፡፡ የወልቃይት ጉዳይ እንዲፈታ ያሳየው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው፤›› በማለትም የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ዳተኛነት ችግር መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ 

የወልቃይት ጉዳይ ከአራት ኪሎ አልፎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የደረሰ አጀንዳ ቢሆንም፣ እስካሁን የሚጨበጥ ዕልባት ገና አላገኘም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. ጁላይ (ሐምሌ) በተጠራ የትግራይ ጦርነትን በተመለከተ ስብሰባ ላይ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር)፣ ስለዚሁ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ‹‹ምዕራብ ትግራይ የምትሉት የወልቃይት አካባቢ አማሮች የጥንት አባቶቻችን መሬት ነው የሚሉት ቦታ ነው፡፡ እኔ ራሴ ከዚያ አካባቢ የመጣሁ ሰው በመሆኔ ጉዳዩን በቅርበት አውቀዋለሁ፡፡ ሕወሓት አካባቢውን የጠቀለለውና ወደ ትግራይ ክልል ያካለለው ሕገ መንግሥቱ ሳይፀድቅና ሕግና ሥርዓትን ባልተከተለ መንገድ በ1991 (1983) መንግሥት ከመፅደቁ በፊት ነበር፡፡ ችግሩ በሕገ መንግሥታዊ አግባብ ሕግን ተከትሎ ኢትዮጵያ የምትፈታው ይሆናል፤›› ሲሉ ታዬ (አምባሳደር) ገልጸው ነበር፡፡ የእሳቸውን ማብራሪያ ተከትሎም በአንዲት ጋዜጠኛ፣ ‹‹ጉዳዩ በሕግ እስኪፈታ በአካባቢው የአማራ የፀጥታ ኃይሎች ይቆያሉ ማለት ነው?›› የሚል ሌላ ጥያቄ ቀረበ፡፡ የታዬ (አምባሳደር) ምላሽም፣ ‹‹አዎ፣ በእርግጥም የሚሆነው እሱ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡

በትግራይ ልሂቃን በተለይ በሕወሓት ወገን ያለው ሙግት ደግሞ ይህን ፍፁም የሚቃረን ነው፡፡ በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ያሉ የሕወሓት ሰዎች ወልቃይት ለድርድር የማይቀርብ የትግራይ ግዛት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወልቃይት ወደ አማራ የሚካለለው በመቃብራችን ላይ ነው ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ የሕወሓቱ መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት ሰፊ መግለጫ ይህንኑ የሚያረጋግጥ አስተያየት ነበር የተናገሩት፡፡

‹‹የትግራይ ሉዓላዊ መሬት ይመለሳል፣ የትግራይ ሕዝብን በመጨፍጨፍ የተሳተፉ ሁሉ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ የአማራ ተስፋፊ ልሂቃን ያሰማሩት የፀጥታ ኃይል፣ እንዲሁም ወራሪው የኤርትራ ጦርና መከላከያ የሚባሉ ኃይሎች ከምዕራብ ትግራይ ሲወጡ ብቻ ነው ሰላምና የድርድር ጉዳይ ሊኖር የሚችለው፤›› በማለት ነበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡

ደብረ ጽዮን ብቻ ሳይሆኑ የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከዚህ ቀደም፣ ‹‹የተወሰደች እያንዳንዷ የትግራይ መሬት ተቆጥራ ትመለሳለች፤›› በማለት መናገራቸው ከዚሁ የወልቃይት ጉዳይ ጋር ተገናኝቶ መቅረብ የሚችል ነው የሚሉ አሉ፡፡

ዛሬ ዛሬ ደግሞ ተከታታይ መግለጫዎችን በወልቃይት ጉዳይ ሲያወጡ የሚታዩት ምዕራባዊያኑ የአማራ ኃይሎች ከአካባቢው በአስቸኳይና ያለ ቅድመ ሁኔታ ይውጡ የሚል ጥያቄ ደጋግመው ያነሳሉ፡፡ ምዕራባዊያኑ ይህን የፈለጉትና ለተፈጻሚነቱም ተደጋጋሚ ጫና የሚያሳድሩት በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት አስቸኳይ የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት የሚቀርብበት ነፃ የሰብዓዊ ኮሪደር ለመፍጠር መሆኑን ቢናገሩም፣ ይህ ግን ከሕወሓትና ከደጋፊዎቹ ውጪ ብዙዎችን የሚያሳምን አይደለም፡፡  

ሕወሓት ከምዕራብ ትግራይ የአማራ ኃይሎች፣ የመከላከያና የኤርትራ ጦር ይውጡልኝ የሚለው በሱዳን በኩል የመሣሪያ ዝውውርና ወታደራዊ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር አገሪቱን በፈለገው መንገድ ለማጥቃት እንዲያስችለው ነው የሚለው እምነት በብዙዎች ዘንድ ሚዛን ይደፋል፡፡

በአዲስ አበባ የወልቃይት ጠገዴ አማራ የሰላምና የልማት ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) ‹‹ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የተረዳው አይመስልም፤›› ሲሉ ነው የሚተቹት፡፡

‹‹ተደጋጋሚ ትንኮሳ በወልቃይት በኩል ሕወሓት ቀጥሏል፡፡ ያን መስመር ክፍት ማድረግ ለኢትዮጵያ መፍረስ ምክንያት እንደሚሆን ቢታወቅም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የኤርትራ መንግሥትን ያህል እንኳ ትኩረት የሰጠው አይመስልም፡፡ ሕወሓት በዚያ አካባቢ የሚያደርገው ተደጋጋሚ ትንኮሳ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያለው ጭምር ነው፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ ከፍተኛ ሥቃይ በሕወሓት የደረሰበት የዚያ አካባቢ ሕዝብ ባለው መሣሪያ እየተከላከለ እየጠበቀው ነው፡፡ ሕወሓት ያን ቀጣና ለምን እንደሚጠቀምበት መንግሥትም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም በደንብ ያውቃሉ፡፡ የዚያ አካባቢ ሕዝብ ጥያቄና የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ ለሥልጣን ለመብቃት ምክንያት እንደሆነው የረሳ የሚመስለው መንግሥት ግን፣ የወልቃይት ችግር እንዲፈታ ጥረት እያደረገ አይደለም፤›› በማለት ነው አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) ሁኔታውን የሚያስረዱት፡፡

ችግሩ እንዴት ይፈታ?

በደርግ ዘመነ መንግሥት ስሜን ወገራ አውራጃ ይባል የነበረው የወልቃይት አካባቢ ዳባትን ዋና መዲናው አድርጎ የተካለለና ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሑመራን ያካተተ ሰፊ ግዛት ነው ሲሉ ታሪክ እናውቃለን የሚሉ ስለአካባቢው ይናገራሉ፡፡ ከደርግ በፊት በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ደግሞ በጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ተብሎ ጎንደርን መዲናው ያደረገ አካባቢ ነበርም ይሉታል፡፡

የሚታረስ ሰፊ ለም መሬት ባለቤት ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ ማሽላና ሰሊጥ የሚታፈስበት ሁሉን አብቃይ ምድርም ይሉታል፡፡ ታላቁ ተከዜን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ በየሜዳው የሚፈነጩ ወንዞች ባለቤት ነው ይባላል፡፡ በብዙ በረከቶች የተሞላ መሆኑ የሚነገርለት ወልቃይት አካባቢ ሆኖም ለረዥም ዘመናት በተቃርኖ ፍላጎቶች የተሞሉ የጦር ቡድኖች ለረዥም ጊዜ ሲፋለሙበት የኖረ ምድርም መሆኑን ቀድመው የሚያወሱ በርካቶች ናቸው፡፡

ኢሕአፓ፣ ኢዴኀ (EDU)፣ ሕወሓትና ሌሎችም የትጥቅ ቡድኖች በዚህ ቀጣና ተኩሰዋል፣ ገድለዋል፣ ተጋድለው ሞተዋል፡፡ ለዚህ ይመስላል ብዙዎች ወልቃይት የበረከት ብቻ ሳይሆን የደም ምድር ነው ሲሉት የሚደመጠው፡፡ አማራና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ያነሱበት ወልቃይት፣ ዛሬም ድረስ በጠመንጃ ለመቆጣጠር አንዱ ከሌላው ከባድ ፍልሚያ የሚያካሂድበት የጦር ዓውድማ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ቀጣናው ከሱዳንና ከኤርትራ ጋር አገሪቱን የሚያዋስን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ቦታ መሆኑን የሚጠቅሱ ወገኖች በበኩላቸው፣ ወልቃይት ዛሬም ልክ እንደ በፊቱ ብዙ ኃይሎች የተሠለፉበት የፖለቲካ ትኩሳት መነሻ ነጥብ እየሆነ ከመጣ ቆይቷል ይላሉ፡፡

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ መሪ ደመቀ ዘውዱ (ኮሎኔል)፣ ‹‹እስከ 1984 ዓ.ም. የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጎንደር ክፍለ አገር ዳባት አውራጃ ውስጥ በጠገዴ፣ በወልቃይትና በሰቲት ሑመራ ወረዳዎች ተከፋፍሎ ይኖር ነበር፡፡ ክፍለ አገሩ ቀደም ሲል በጌምድር ወይም ስሜን ጠቅላይ ግዛት እየተባለ የሚጠራው ጎንደር ነበር፡፡ ሕወሓት በ1983 ዓ.ም. ነው ወልቃይትን ወደ ትግራይ ያካለለው፡፡ በ1984 ዓ.ም. በሽግግር መንግሥቱ አዋጅ ቁጥር 7/1984 ደግሞ የክልሎች አስተዳደር ወሰን ከ1966 ዓ.ም. በፊት በነበረው እንዲሆን ተወስኗል ብሎ በአዋጅ ወልቃይትን ወደ ትግራይ ወሰደ፤›› በማለት፣ ስለወልቃይት ጉዳይ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በቀረበ አንድ ዘጋቢ ፊልም ተናግረው ነበር፡፡

ጸሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን በበኩሉ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ መግፋት እንዴት እንደጨመረ ሲያስረዳ፣ ‹‹አሁንም ብዙ ትግሬዎችና የሌሎች ብሔረሰብ ሕዝቦች በወልቃይት ይኖራሉ፡፡ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጎንደር ላይ የተቀጣጠለው የወልቃይት ጉዳይ የመላው አማራ የፖለቲካ ጉዳይ ሆነ፡፡ የአምባገነኑ ሥርዓት መውደቂያ ከሆኑ ዓብይ ምክንያቶችም አንዱ ነው የሆነው፡፡ የወልቃይት መሬት የተወሰደው በኃይል ነው፡፡ በሕገ መንግሥት ሳይሆን ዝም ብሎ ነው ወልቃይትን ሕወሓት የወሰደው፡፡ ሊመለስ የሚችለው በፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ አንደኛው መንገድ ይኼው ነው፤›› በማለትም መፍትሔ ከሚለው ሐሳብ ጋር ያብራራል፡፡

‹‹የዚያ አካባቢ ችግር በቀላሉ የመጣ አይደለም፣ በቀላሉ የሚፈታ ችግርም አይደለም፤›› ሲሉ የሚናገሩት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ችግሩ በዋናነት በሕወሓት የፖለቲካዊና የኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ግፊት መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቋንቋ የምትል ትንሽ አመክንዮ በማቅረብ ዓመቱን ሙሉ ወንዝ የሚፈስበት፣ ዝሆንና አንበሳ የሚቦርቅበት ጫካ ያለው፣ ዕጣንና ሙጫ የተትረፈረፈበት፣ ወርቅ፣ ሰሊጥና ማሽላ የሚመረትበትን ሰፊ ለም መሬት መውረስ ነው ፍላጎታቸው፡፡ ትግራይ በወርቅ አንደኛ ብትባልም ሀቁ ግን የጠገዴ ወርቅ ነው፡፡ ከፍተኛ ሰሊጥ አመረትን ይላሉ፡፡ በጆርናል የታተመውን ብናገር በ2007 ዓ.ም. ብቻ ስምንት ቢሊዮን ብር ከሰሊጥ አግኝተናል ብለዋል፡፡ ይህን ጨምሮ ማሽላ ይመረትበታል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ወያኔ ለሚፈልገው አገር የማተራመስ ዓላማ ከግብፅ ጀምሮ በሱዳን በኩል ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጭምር የሚያገናኝ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው፤›› ሲሉ አሰፋ (ዶ/ር) ስለወልቃይት ችግር ምንጭ ያሉትን ያስረዳሉ፡፡  

ጥያቄው ያገባናል የሚሉ ይህን ቢሉም፣ የወልቃይት ሕዝብ ችግር ባለመፈታቱ ሲጨምር እንጂ ሲቆም አለመታየቱን ነው፣ ማኅበረሰቡ አካባቢው ነፃ ከወጣ በኋላ ያለውን ሁኔታ የሚናገረው፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የፌዴራል መንግሥት በጀት ባለመመደቡ የመሠረተ ልማትና የሕዝብ አገልግሎት በአካባቢው መስጠት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን፣ ከሰሞኑ የወጣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘገባ ያመለክታል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሕዝብ ግንኙነት ለሚዲያው እንደተናገሩት፣ ‹‹ዞኑ በጀት አልተለቀቀለትም፣ በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችም መልሰው እንዲገነቡ ድጋፍ አልተደረገለትም፡፡ ከነበሩ 71 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ብዙዎቹ ታጥፈው 51 ቀሩ፡፡ ነገር ግን ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ በቅርቡ ሁሉም ይዘጋሉ፡፡ 41 ሺሕ ተማሪዎች ነበሩ፣ ዘንድሮ የመዘገብነው ግን 15 ሺሕ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም አራት ሺሕ የሚሆኑት ትምህርቱን አቋርጠዋል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ዘገባ ላይ፣ ‹‹በወልቃይት ሰቲት ሑመራ ዞን 52 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ፣ 152 ተማሪ ቤቶች ደግሞ በከፊል ወድመዋል፡፡ 134 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ‹‹ኔትወርክ፣ ጤና፣ ትምህርትና መብራት በሌለበት አንድ ዓመት ለሰባት ወራት ያለ ምንም በጀት ነው አካባቢው እየተዳደረ ያለው፡፡ አማራነታችን በተፈጥሮ የታደልነው ፀጋ ነው እያልን ያለነው፣ ግን ኢትዮጵያዊነታችን ይከበርልን ነው፤›› ሲሉ ነበር ምሬታቸውን ያሰሙት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናትና ቁፋሮ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውና በግፍ የተጨፈጨፉ ናቸው የተባሉ ሰዎች ቅሪተ አካል በቁፋሮ መውጣቱ፣ የብዙዎችን ትኩረት ዳግም ወደ ወልቃይት የመለሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር የከረመው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሒዩማን ራይትስዎች በጋራ አጠናቅረነዋል ያሉት በምዕራብ ትግራይ (ወልቃይት) በትግራይ ተወላጆች ላይ ጭፍጨፋ እየተካሄደ እንደሆነ የሚያትት ሪፖርት፣ ራሱን የቻለ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ነው የከረመው፡፡

አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን የአምነስቲና ሒዩማን ራይትስዎች ሪፖርትን በሚመለከት፣ ‹‹የሪፖርቱ ዓላማ የአሸባሪው ቡድን ሁሌም ጫና ውስጥ የወደቀ በመሰላቸው ጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ሽፋን ለመስጠት ያወጡት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሌላው ደግሞ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ18 ወራት የፈጀ ጥናት አድርጎ፣ የአሸባሪው ኃይል የቀደሙ ወንጀሎችን ቆፍሮ በማውጣት ማጋለጥ መጀመሩን ተከትሎ፣ አቅጣጫ ለማስቀየስ የተደረገም ሊሆን ይችላል፡፡ ‹ገሃነብ› በተባለው ማጎሪያ ቦታ ወደ አምስት የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል፡፡ ባዶ ስድስት በተለምዶ በሚባለው ደጀና ላይ ብዙ የቆዩ የወያኔ ግፎች እየተጋለጡ ነው፡፡ ሌላው የሪፖርቱ ዓላማ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጫና ለማገዝ የተደረገም ነው፤›› በማለት ይተቻል፡፡

አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ከ1972 ዓ.ም. ጀምሮ ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል፣ ተቀብረዋል፡፡ ሕወሓት ወልቃይት እግሩ ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ያልተፈጸመ ግፍ የለም፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ተረስቶ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቆፍሮ ግፋቸውን ሊያጋልጥ ሲል የዓለም የሰብዓዊ መብት ጠበቆች ነን የሚሉ የውጭ ተመፃዳቂ ተቋማት በመግለጫ በአማራ ላይ የተነጣጠረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፈቱ፤›› በማለት ነበር ዓለም አቀፉን በወልቃይት ላይ የተደረገ ትኩረት የተቹት፡፡

‹የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የእኔ ነው› የሚሉት ትግራይና አማራ ክልሎች ብዙ መከራከሪያዎች ያቀርባሉ፡፡ የሁለቱ ክልሎች ልሂቃን ታሪክ እያጣቀሱና አለን የሚሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ እያቀረቡ ወልቃይት በታሪክ የእኛ ነው እያሉ መከራከር ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ የአማራ ልሂቃን በተለይ በ1967 ዓ.ም. ወደ ደደቢት በረሃ ለትጥቅ ትግል የገባው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ሕወሓት)፣ በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1968 ዓ.ም. ባወጣው ማኒፌስቶ ወልቃይትን ለመውረር መንደርደሩን የሚያመላክት ሐሳብ ማስቀመጡን በማንሳት ይከራከራሉ፡፡ የታላቋ ትግራይ ድንበር በደቡብ አልኀ፣ በምዕራብ ወልቃይትና በፀለምት ነው ብሎ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ማኅበራዊ መሠረቱ የሆነው ሕዝብም፣ ትግርኛ የሚናገረው ከትግራይ ውጪ ያለውም በሙሉ ኩናማ፣ ሳሆ፣ አፋር ወይም ታልታ፣ አገውና ወልቃይትን እንደሚጨምር አስቀምጧል ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በዋናነት ወልቃይት የአማራ ነው የሚለውን ሙግት ከሚያጠናክርባቸው መከራከሪያዎች ደግሞ፣ አንጋፋ የትግራይ ልሂቃንና የተናገሩትን ንግግር በማስረጃ ማቅረብ ነው፡፡ የቀድሞው የትግራይ አስተዳዳሪ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በአንድ ወቅት ለቪኦኤ የተናገሩትና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ድንበር በኤርትራ በኩል ድንበሩ መረብ ሲሆን፣ በበጌምድር ደግሞ ተከዜ መሆኑን ነው የማውቀው የሚል መልዕክት ያለው ንግግራቸው አንዱ ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል፡፡

የቀድሞ የሕወሓት አመራር አብረሃም ያየህ በካርታ አስደግፈው ጭምር በደርግ መውደቂያ ዋዜማ በቴሌቪዥን መስኮት ያቀረቡት፣ በትግራይ ካርታ ነዳፊዎች ወልቃይት ወደ ትግራይ ተካሎ ተሠርቷል የሚለው ነጥብም ሌላው ማስረጃ ተብሎ የሚቀርብ ነው፡፡ በሌላ በኩል አሁን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ትዴፓ) የሚመሩት የሕወሓት መሥራቹ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ በአንድ ወቅት ተናግረውታል የተባለው ማስረጃም ሌላ መከራከሪያ ንብ ሆኖ ይቀርባል፡፡ አረጋዊ (ዶ/ር)፣ ‹‹ወልቃይት ለእህል፣ ለመሣሪያና ለሌላም ነገር በሱዳን በኩል ለማስገቢያነት ይሆናል ተብሎ ስለታመነ ነው በሕወሓት በትግል ወቅት የተያዘው፤›› ሲሉ መናገራቸው ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ መከራከረያ ማስረጃ ሆኖ ነው የሚቀርበው፡፡

የሕወሓት ሌላው መሥራች አቶ ስብሃት ነጋ በአንድ ወቅት ስለትግራይ መገንጠል ጉዳይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ‹‹ትግራይ ትገንጠል ቢባል ወዴት ነው የምትገነጠለው? ፍጅትና ቀውሱም ማለቀያ የለውም፡፡ የአማራ ልሂቃን ወልቃይትና ራያ የእኔ ነው እያለ እንዴት ነው ዝም ብለን የምንገነጠለው?›› ሲሉ መናገራቸው፣ በወልቃይት ያለውን የባለቤትነት ጥያቄ ክብደት ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ማስረጃ ነው፡፡ ለአንዳንድ የሕወሓት ልሂቃን ግን ጉዳዩ በሕግ የሚፈታ ራሱን የቻለ አካሄድ ያለው ቀላል ጥያቄ ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡

ለአብነት ያህል የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ‹‹ራያ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴና አላማጣ ትግራይ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የማንነት ጥያቄ ካላቸው ወደ ትግራይ ክልል መንግሥት በማመልከት ይጠይቃሉ፡፡ ትግራይ ካልመለሰ ወደ እኛ በይግባኝ ይመጣል፡፡ ያን ጊዜ እኛ መልስ እንሰጣለን፤›› በማለት ነው ጉዳዩ ራሱን የቻለ አካሄድ ያለውና ቀላል ነው በማለት ተናግረው ነበር፡፡

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ መሪው ደመቀ (ኮሎኔል) በጉዳዩ ላይ የወልቃይት ሕዝብ መሄድ ያለበትን ርቀት ሁሉ ሄዶ ጥያቄ ማቅረቡን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹የወልቃይት ጥያቄ በጠመንጃ ሲቀርብ ነበር፡፡ ይህ መሆን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ወያኔ ከክላሽ ይልቅ በወረቀትና ስክሪብቶ እንደሚሸነፍ ስለምናውቅ፣ የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አደራጅተን ታገልን፡፡ ለሰላማዊ ጥያቄያችን እስር፣ አፈናና ግድያ ነበር መልሳቸው፤›› በማለት ጥያቄው በቀላሉ ሳይመለስ መቆየቱን ያስረዳሉ፡፡   

ባለፈው ሳምንት በሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ተሟገት ዓምድ ላይ የግል አስተያየታቸውን የከተቡት አቶ ድልበቶ ደጎዬ ዋቆ የተባሉ አንድ ጸሐፊ ‹‹የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እንዴት ይፈታ?›› በሚል ርዕስ ከረዥም ጊዜ በፊት በሥራ አጋጣሚ በአካባቢው ተመድበው ሲሠሩ ካገኙት ልምድ በመነሳት የሚከተለውን ሐሳብ አጋርተው እንደነበር ይታወሳል፡፡  

‹‹ከ1967 እስከ 1970 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በተለይም መዘጋ፣ ቃፍትያ፣ አዲረመጥ፣ አርማጭሆና ሌሎች የሰሜን ተራራ ኮረብታማ ወረዳዎችና ዋሻዎች የኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ሠራዊት ምሽጎች እንደነበሩ ይነገር ነበር። በ1970 ዓ.ም. ሕወሓት የኢሕአፓን ድርጅት ከአሲምባ ምሽጉ በጦር ኃይል አስገድዶ ሲያስወጣና ድርጅቱ ከውስጥ አንጃዎች፣ ከውጭ ደግሞ የሕወሓትና የሻዕቢያን ዱላ ለመቋቋም ባለመቻሉ ተፍረክርኮ ሲበታተን አብዛኞቹ ወደ ሱዳንና ወደ ተለያዩ አገሮች ተሰደዱ፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ምሽጎቹን ለሕወሓት ታጋዮች ለቅቆ መውጣት የግዴታው ስለነበር ይህንን ስትራቴጂካዊ የሱዳን መውጫና መግቢያ በር ሕወሓቶች ፈጥነው ለመቆጣጠር እንደበቁ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን እስከሆኑ ድረስ ጥያቄና ተቃውሞ አልተሰነዘረባቸውም በዚያን ዘመን።

‹‹ከዚያንጊዜአንስቶየሕወሓትሠራዊትአባላትናደጋፊዎችየሑመራንናየአካባቢውንለምየእርሻመሬቶችሁሉቀስበቀስበተወላጆቻቸውቋሚይዞታሥርለመጠቅለልበቅተዋልማለትነው፡፡በዚህምሳቢያየወልቃይትነባርተወላጆችን (ወልቃይቶችን) በግድያምሆነበማፈናቀልከገዛመሬታቸውነቅለውእንዲሰደዱአደረጓቸውማለትነው።

‹‹በዚህምየተነሳዛሬበአንድወገን፣የወልቃይትጠገዴአካባቢየወልቃይቶች (የአማራክልል) ነው፣ጥንትምዛሬም፡፡በሌላወገንደግሞየለምየትግራይነውጥንትምሆነዛሬየሚሉእርስበርስየሚጣረሱአቋሞችእየተራገቡናቸው።አሳዛኝትርክትነው።ይህበዚህእንዳለቢሆንም፣የኢሕአፓርዝራዦችየነበሩትጓዶች ‹‹ኢሕዲን›› (በኋላ ‹‹ብአዴን›› ተብሎየክርስትናስያሜበሕወሓትተሰጥቶት) የሚልየሕወሓትተቀጥላድርጅትመሥርተውእስከዛሬለመዝለቅበቅተዋል።

‹‹ሆኖም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች መሠረት የተከናወኑት የክልሎች አከላለል ሒደቶችና አፈጻጸሞች በሰላማዊ መንገድ የተከናወኑ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ ክልሎች ደም አፋሳሽ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ የሰዎች ሕይወት ሳይቀጠፍና የንብረት ውድመት ሳይኖር የተከናወነ የክልል አወሳሰንና አወቃቀር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ይህ በዚህ እንዳለ ዛሬ የወልቃይቶችንም ሆነ የማንኛውንም ዘውግ ማንነት የሚወስኑት ራሳቸው ማኅበረሰቦቹ እንጂ፣ ማንም ሌላ አካል የእነሱን የዘውግ ማንነት እንደ ቦሎ አይለጥፍላቸውም፡፡ እንዲሁም ያለ ፈቃዳቸውና ያለ ፍላጎታቸው ወደ የትኛውም ክልል እንዲካለሉ መወሰን የማንም ሥልጣን አይደለም፤›› ነበር ያሉት፡፡

‹‹ወልቃይትን ከረዥም ዓመታት በፊት አውቀዋለሁ›› ያሉት አቶ ድልበቶ ይህን ቢሉም፣ ለወልቃይት የሚሆን መፍትሔ የፖለቲካ ልሂቃኑ ማፍለቅ ላይ ሲቸገሩ ነው የሚታየው፡፡ አንዳንዶች በሕዝበ ውሳኔ ይፈታ ይላሉ፡፡ ሌሎች በልዩ የፖለቲካ ውሳኔ ይቋጭ ሲሉ፣ አንዳንድ ደግሞ የኃይል አማራጭን ወይም አኔክሴሽንን መፍትሔ አድርገው ያስቀምጡታል፡፡

ለአብነት ያህል አሰፋ (ዶ/ር)፣ የወልቃይት ጉዳይ በትግራይና በአማራ ልሂቃን መካከል በሚደረግ ድርድር ሊፈታ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በዚሁ ጉዳይ አስተያየት የሚሰጠው አቶ ሙሉዓለም ግን ሕወሓት ለድርድር ዝግጁ ነው ብሎ እንደማያምን ነው የሚገልጸው፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በዚህ ሁኔታ በምን ይቋጭ ይሆን የሚለው ገና መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -