ጀግኖች አባቶችና እናቶች ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ያደረጓትን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል፣ በሕፃናትና ወጣቶች ላይ መሥራት አማራጭ የሌለው የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
ሕፃናት ቦርቀው፣ ወጣቶች ተኩለውና ተድረው፣ አዛውንቶች ተከብረውና ተጡረው ለመኖር፣ መጀመርያ አገር መኖር አለባት፡፡ አገር እንድትኖር ደግሞ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ሰላም መኖር አለባት፡፡
የሰው ልጆች አምረው፣ ደምቀውና ተፋቅረው ሲኖሩ ችግርና ደስታን በጋራ ይወጡታል፡፡ ኢትዮጵያ በዓድዋ፣ በካራማራና ሌሎችም አካባቢዎች ተቃጥተውባት የነበሩትን የቅኝ ግዛትና የወረራ ጦርነቶች አንድ በመሆን፣ በመተሳሰብና በመፈቃቀር እንዴት ድል እንዳደረገች ታሪክ ማገላበጡም ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
አሁን አሁን በተለይም ከ30 ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያዊነት አንድነትና የመተሳሰብ ሁኔታ፣ ከዓመት ዓመት እያስፈራና ግራ እያጋባ ነው፡፡ በዘርና ቋንቋ ላይ የተመሠረተ የመጠላለፍና የመጠፋፋት አባዜ እያደገ መጥፎና አስፈሪ ሁኔታ ላይም ተደርሷል፡፡
በተለይ ደግሞ ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ሁኔታው ተባብሶ በመቀጠሉ ጉዳዩ ከመንግሥትም በላይ ለወላጅና ቤተሰቦች አሳሳቢና ሥጋት ላይ የሚጥል ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ችግርና ሥጋት እንዴት ሊመጣ ቻለ? የችግሩ ምንጭ ምንድነው? ችግሮቹን ለምን መቅረፍ አልተቻለም? እንዴትስ ማስተካከል ይቻላል? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሹ አንድና አንድ በሕፃናት ላይ መሥራት ነው፡፡
ሕፃናት ተጫውተው፣ ቦርቀው፣ አንብበውና ፍቅር ተሰብከው እንዲያድጉ ማድረግ የመጀመርያውና የመጨረሻው አማራጭ ነው፡፡ በመሆኑም ሕፃናትን ትኩረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ባሉ ደረጃዎች ሁሉ በየዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል፡፡
ሰሞኑን ሕፃናት ላይ ትኩረት ያደረገ ወይም ሕፃናትን መዳረሻ ያደረገ አንድ መጽሐፍ ታትሞ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ ‹‹ቼላ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምሕንድስና ተማሪ የሆነችው ወጣት ረድኤት በፈቃዱ ትባላለት፡፡
የቀድሞ አራዶች ሃምሳ ሳንቲምን ‹‹ቼላ›› ብለው በሚጠሩት ስያሜ መጽሐፏን ‹‹ቼላ›› ብላ የሰየመችው ረድኤት፣ ትርጉሙ ‹‹ሃምሳ ሳንቲም›› መሆኑን ያወቀችው ከታላላቆቿ ጠይቃ መሆኑን የገለጸችው መጽሐፉን እሑድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በቸርችል ሆቴል በተመረቀበት ዕለት ነው፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጠበቆች፣ ደራሲያን፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት በጥቅሉ በርካታ ሰዎች በተገኙበት የተመረቀው ‹‹ቼላ›› መጽሐፍ ወጥ ታሪክ ሲሆን፣ በአሥር አጫጭር አርዕስት የተከፋፈለ ነው፡፡
መጽሐፉ ለሕፃናት ዓይን የሚማርኩ ሥዕሎች በየገጹ የተሣሉበት ሆነው ከታሪኩ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የመጽሐፉ ታሪክ ሕፃናት ጓጉተው እንዲያነቡትና እናት አባቶቻቸው ሲተርኩላቸውም ልብ አንጠልጣይ ታሪክ ያለው ቢሆንም፣ በውስጡ ያሉ መልዕክቶች ግን ዘመን ተሻጋሪና አስተማሪነታቸው እጅግ በጣም ድንቅ ናቸው፡፡
ሕፃናት የቤተሰብ ትዕዛዝ ሰምተው እንዴት መተግበር እንዳለባቸው፣ የሚፈልጉት ነገር ሲኖር በትህትና እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸው፣ ሲያጠፉም እንዴት ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸውና ጥሩ ነገር ሲደረግላቸውም እንዴት ማመስገን እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው፡፡
ይህ መጽሐፍ አሁን ኢትዮጵያ ያጣችውንና ትውልዱ እየደገፈው ግን (እያጣው) ያለውን የመከባበር ሥርዓት የሚያመላክት ከመሆኑም ባለፈ፣ ለሕፃናት ደግሞ እንዴት ተቀርፀው ማደግ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው፡፡
‹‹ክፉ ለሚያደርግብህ ሁሉ ትሁት ሁን›› የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በደንብ የሚያሰርፅ፣ ሁልጊዜም ቢሆን እውነት መናገር አስፈላጊ መሆኑንና አስፈላጊ ማስረጃዎችንና መረጃዎችን ሕፃናት ይዘው መጓዝ እንዳለባቸው ከመምከሩም ባለፈ፣ እንደ አገርም ሁሉም ሊያደርገው የሚገባ አስተምህሮ የያዘ ነው፡፡
ወጣቷ ደራሲ ረድኤት በፈቃዱ፣ በ2012 ዓ.ም. በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ከዩኒቨርሲቲ ለአሥር ወራት ተማሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ በተደረጉበት ወቅት ይህንን የሕፃናት መጽሐፍ መድረስ መቻሏን በመጽሐፉ ምርቃት ላይ ተናግራለች፡፡
በወቅቱ የተከሰተውን ወረርሽኝ ፈጣሪ ቀላል እንዲያደርገውና ለአገሯም ምሕረትን እንዲያወርድ ፀሎት ለማድረስ በአካባቢዋ ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በሄደችበት አንድ ቀን ላይ፣ ሕፃናት በቤተ ክርስቲያኑ ተገኝተው ያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴ ተመልክታ ስትመለስ ‹‹ቼላ›› የሚለው ስያሜ በአዕምሮዋ በመሣሉ፣ ወደ መጽሐፍ ቀይራ ለሕፃናት ማበርከቷን ተናግራለች፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ላይ የተገኙም ዳኞችና ጠበቆች ገጣሚና ጸሐፊ ታገል ሰይፉ፣ ታዋቂው አነቃቂና ሰባኪ መምህር መጋቢ ሐዲስ ዓለማሁና ሌሎች ታዳሚዎች በመጽሐፉ ላይ ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት፣ በቀጣይ ሌሎች ሥራዎቿን እንደሚጠብቁ በመግለጽ ደራሲዋን አበረታተዋል፡፡