Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከችግሮች መላቀቅ ያልቻለው የቱሪዝም ዘርፍ

ከችግሮች መላቀቅ ያልቻለው የቱሪዝም ዘርፍ

ቀን:

የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱ የቱሪዝም ዘርፍን በእጅጉ እንደጎዳ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ በይበልጥ ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ተጎድቷል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚጎበኙ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያም ወረርሽኙ እንደሌሎች አገሮች በትሩን ማሰረፉ አልቀረም፡፡

ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት ከተወሰዱ ዘርፈ ብዙ ዕርምጃዎች ውስጥ በቱሪስቶች ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ይገኙበታል፡፡ ይህም የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች የሚባሉት አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎችና በዙሪያው የሚሠሩ ዜጎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለመከላከያ በተቀመጡ ገደቦች ተፅዕኖ በእጅጉ ተጎድተዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመጋራት መንግሥት ከእነዚህ ዘርፎች መካከል ለሆቴሎች ድጎማ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም አስጎብኚ ድርጅቶች ድጎማ ይደረግላችኋል ተብለው የነበረ ቢሆንም፣ ተፈጻሚ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም የኮሮና ወረርሽኝ እንዳይዛመት ተጥሎ የነበረው የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ለተለያዩ ዘርፎች የተነሳ ቢሆንም፣ የቱሪስቶች የመዳረሻ ቪዛ ፈቃድ መራዘሙ አስጎብኚ ድርጅቶችን እየጎዳ እንደሆነ በሥራም የተሰማሩ አካላት ይገልጻሉ፡፡

የታላቋ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ተስፋዬ እንደተናገሩት፣ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ችግሩ የጀመረው ከለውጡ በኋላ ነው፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣውን ችግር ሳይቋቋሙት ጦርነቱ መከሰቱ ዘርፉን እንደጎዳው የቱሪዝም ሥራ ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈልግ ይገልጻሉ፡፡

አስጎብኚ ድርጅቶች በተቻላቸው አቅም ማስታወቂያ እየሠሩና ጎብኚዎች ሰላም በሆኑባቸው አካባቢዎች እንዲጎበኙ ለማድረግ ብዙ መጣራቸውን፣ አገራዊ ለውጡ በተፋፋመበት ወቅት በቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደነበረውና የድርጅቶቹ ሥራ አንዳንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ መክረሙን አክለዋል፡፡

አቶ ዳንኤል እንዳስረዱት፣ አገራዊ ለውጡ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ችግር ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ዕድሎችን ቢያመጣም፣ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የተጣለው የቱሪስቶች የመዳረሻ ቪዛ ፈቃድ ክልከላ አለመነሳት ችግር ሆኖባቸዋል፡፡

ኮቪድ-19 በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመጋራት፣ ሠራተኞች ሥራ እንዳይለቁና ሌሎችንም ችግሮች ለማቃለል መንግሥት የአነስተኛ ወለድ ብድር በብሔራዊ ባንክ በኩል ለአስጎብኚ ድርጅቶች ማዘጋጀቱ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

ድጎማው በብሔራዊ ባንክ በኩል በቀጥታ መሰጠት የነበረበት ቢሆንም፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ደንበኛ በሆኑባቸው ባንኮች በኩል እንዲሰጥ መደረጉ ለባንኮቹ ጥቅም ስለማያስገኝ በተለያዩ ምክንያቶች ድጎማውን እያራዘሙና ቢሮክራሲ እየፈጠሩ በመጀመሪያው ዕድል ሆቴሎች ተጠቅመው አብዛኛው አስጎብኚ ድርጅቶች ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚያ ሁኔታ ውስጥ አስጎብኚ ድርጅቶች የነበሯቸውን ሠራተኞች ለማስቀጠል ብዙ ችግሮች እንደነበሩባቸው፣ መንግሥትም የሚሰጠው ብድር በቃልና በውሳኔ ደረጃ ከመቀመጡ ባለፈ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ምንም ያገኙት ድጋፍ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው ትልቁ ማነቆ በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበረው ጦርነት ነው፡፡ ይህም ለቱሪዝም ዘርፉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል፡፡ አቶ ዳንኤል እንደሚሉትም፣ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ዘርፉ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም በመንግሥት ኦዲት እንደተደረገና አብዛኛው ድርጅቶች ለሁለት ዓመታት ሳይሠሩ ቢቆዩም፣ ዓመታዊ ግብር መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡

አስጎብኚ ድርጅቶች ዘርፉ ላይ የተጠፈረው ችግር ሲቀረፍ ግብር የሚከፍሉበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም እንደሆነ፣ ለዚህም ለወደፊት በስምምነት እንዲከፍሉ ጊዜ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ ሁኔታዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደምትገኝ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ አስጎብኚ ድርጅቶችም በከፍተኛ ሁኔታ የተጣለባቸውን ግብር ለመክፈል ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ብዙ እንቅስቃሴ እንዳልነበረ የሚናገሩት ሌላኛው የአስጎብኚ ድርጅት ኃላፊ፣ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት እንደ ወቅቶች የተለያየ ቢሆንም በሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ይገቡ ነበር ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የቫይረሱ ሁኔታ እየቀነሰ በመሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች የመምጣት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በቱሪስት መዳረሻ ቪዛ ክልከላ ምክንያት መምጣት እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከአገር ደኅንነት አንፃር ቪዛውን ለጊዜው መስጠት እንደማይቻል እንደተነገራቸውና አሁን በድጋሚ ቢጠይቁም ምንም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

የፈረንጅ አስጎብኚዎች ድርጅት ባለቤት አቶ ጫንያለው ዘውዴ በበኩላቸው፣ መንግሥት ኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ አደርጋለሁ ብሎ እየሠራ እንደሆነ ቢናገርም፣ ቱሪስቶች የሚመጡበትን የቪዛ ሒደት መገደቡ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ደግሶ በር ዝግት›› የሚሉት አቶ ጫንያለው፣ ቱሪስቶች ሰላም በሆኑባቸው ቦታዎች ለመጎብኘት ቢፈልጉም፣ የመዳረሻ ቪዛ መስጠት ከቆመ ከሁለት ዓመታት ወዲህ መምጣት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ እንዲቀረፍላቸው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ደብዳቤ መላካቸውን፣ ነገር ግን ምንም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ቱሪስቶች በተደጋጋሚ ሰላምና ፀጥታ የተጠበቀባቸውን ቦታዎች ለመጎብኘት ፍላጎት ቢያሳዩም፣ የመዳረሻ ቪዛ ገደብ ባለመነሳቱ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም፣ ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ስለቱሪስት መዳረሻ ቪዛና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ አቶ ስለሺ ግርማንና የኢሚግሬሽን የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ተሬሳን በስልክ ለማናገር ሞክሮ ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...