Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊረሃብን ከማስታገስ ወደ ተመጣጠነ ምግብ እየተሻገረ የሚገኘው የተማሪዎች ምገባ

ረሃብን ከማስታገስ ወደ ተመጣጠነ ምግብ እየተሻገረ የሚገኘው የተማሪዎች ምገባ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከ800 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በትምህርት ቤቶቹ የሚማሩ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚሆን ግብዓቶችን በማጣታቸው ከትምህርት ገበታቸው ሲቀሩና ሲያቋርጡ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በየግላቸው የምገባና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍና አገልግሎቱን በአንድ ተቋም ሥር ወጥነት ባለው መንገድ ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀድሞ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ደብተር፣ እስክሪብቶና ሌሎች ግብዓቶችን እንዲያገኙ ማስጀመራቸውም ይታወሳል፡፡

ድጋፉ እያደገ መጥቶ ለተማሪዎች ግብዓቶችን ከማቅረብ ባለፈ፣ በከተማ አስተዳደሩ ወጪና በሌሎች ባለሀብቶች ድጎማ በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ከ600 ሺሕ በላይ ተማሪዎች የምግብ አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

ከተማሪዎች ምገባ በተጨማሪም የምገባ ማዕከሎችን ቁጥር ከፍ በማድረግ በከተማዋ በቀን አንድ ጊዜ መብላት የማይችሉ ከአሥር ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በየዕለቱ እየመገበ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አንቺነሽ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው በቀን አንድ ጊዜ መብላት የማይችሉ ዜጎች የዕለት ጉርስ እንዲያገኙ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡

በተለይም የምገባ ማዕከሎችን ቁጥር ከፍ በማድረግ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ዜጎች በየቀኑ እየተመገቡ መሆኑን፣ ፕሮግራሙም በተጀመረበት ወቅት ኤጀንሲው ትኩረት አድርጎ ይሠራ የነበረው ረሃብን የማስታገስ ላይ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን በማሻሻል የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በእያንዳንዱ የምገባ ማዕከል ለመመገብ የሚመጡ ዜጎችን ምግብ ከመስጠት ባለፈ ያላቸውን ዕውቀት ተጠቅመው ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ሥልጠና እንደሚሰጥም አክለዋል፡፡

በከተማዋ የመጀመርያና የሁለተኛን ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከ800 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ከእነዚህ ውስጥ በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ብቻ የምገባ አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ ሱሶችና በሌሎች ነገሮች ወደ ጎዳና የወጡ ዜጎችን የክህሎት ሥልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን፣ ይህንንም ዘላቂ ለማድረግ ኤጀንሲው ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

‹‹በማዕከሎቹ ውስጥ የሚሰጡ ምግቦች ደረጃቸውን የጠበቁና የተመጣጠነ ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ አቅም ያላቸው አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች ጭምር በማዕከሉ በመግባት የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑንና ይኼም ችግር እንደሆነባቸው አብራርተዋል፡፡

ማዕከሎቹ የከፋ የጤና ችግር ላለባቸውና ጧሪና ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን በቋሚነት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአብዛኛው ማዕከሎችም እዚያው ምግብ የሚዘጋጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዕለት ምግብ መመገብ የሚችሉ አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ወደ ማዕከሉ እንዳይገቡ ለማድረግ የማጣራት ሥራ ለመሥራት እንደተቸገሩ፣ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በቂ የሆነ ግንዛቤ ኖሯቸው አቅም ለሌላቸው ወገኖች ቅድሚያ መስጠት እንዲችሉ የመገናኛ ብዙኃን ትልቁን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ለመቆጣጠር ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ አንቺነሽ፣ ይህም ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንደኖረው ይረዳል ብለዋል፡፡

የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ይህ ነው የሚባል ችግር እንደሌለበት፣ የከተማ አስተዳደሩም ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ተማሪዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ እንዲያገኙ በየጊዜው ክትትል እንደሚደረግ፣ በተለይም ምግብ ለሚያበስሉ እናቶች በቂ ግብዓቶችን በማቅረብ ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለተማሪዎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በምግብ ዕጦትና የደንብ ልብስ ባለማግኘት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንደሚሰናከሉ፣ በዚህም የተነሳ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጡ እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ዝናብ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ችግር በመረዳት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ከ600 ሺሕ በላይ ተማሪዎች የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ የብዙ እናቶችን ችግር ሊያቃልል እንደቻለ አቶ ሁሴን አብራርተዋል፡፡

የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ700 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚሆኑ ግብዓቶችን በነፃ እያገኙ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ከዚህም በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት በኩል ማኅበራዊ ትስስርን በማጉላት ያለው ያቅርብ፣ የሌለው ይመገብ በሚል መሪ ሐሳብ በስድስት ክፍለ ከተሞች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን መመገብ እየተቻለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ባስጀመረው ፕሮጀክት የዕለት ጉርሻ ያጡ አሥር ሺሕ ዜጎችን በቀን እየመገበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሆቴሎችና መንግሥታዊ በሆኑ ተቋሞች በኩል የግንባታና የምግብ አቅርቦት ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፣ ይህንን ፕሮጀክት በማሳደግና ወደ ተሻለ ቦታ በማድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ማዕከላት እንዲኖሩን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ማዕከሎችን ቁጥር በማሳደግ ለማዕከሎቹ በቂ የግብዓት አቅርቦቶችን ተደራሽ በማድረግ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በኑሮ ውድነት ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ፣ እነዚህን ዜጎች ለመታደግ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ወ/ሮ አንቺነሽ ተናግረዋል፡፡

በማዕከሎቹም 150 የሚሆኑ ዜጎች በጊዜያዊነት ተቀጥረው እየሠሩ እንደሆነና ቀጣይነት እንዲኖራቸው የባለሀብቶች ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ