Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወቸ ጉድ!

እነሆ ከፈረንሣይ ሌጋሲዮን ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ጎህ ቀዷል ፍጥረት አልገፈፍ ካለው የጨለማ ኑሮ ሊሸሽ መንገዱን ተያይዞታል። ልብ ባይከተለው፣ ቀልብ ስንቅ ባይሆነው፣ እግር ልማዱ ነውና እየተራመደ ያስኬደናል፣ እንራመዳለን፡፡ እንደ ሰነፍ ገበሬ ማሳ በቆምንባት መሬት የዘራነውን ዘር አረም ይጫወትበታል። ቀና ሲሉ አንገት መድፋት፣ አደግን እያሉ መቀጨት ከጥንትም የዓለም ጠባይ ሆኖ ደግሞ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ያደረሰን መንገድ ነገን ሊያሳየን በተስፋ ደግፎ ወዲያ ወዲህ ያንቀዠቅዠናል። አለሁ ሲሉ እንደ ዋዛ መቅረት፣ በረታሁ ሲሉ በአልጋ መያዝ፣ ሆነልኝ ሲሉ አመድ ማፈሱን ተላምደነዋል። ከመላመዳችን ብዛት ሞትና ሕይወትን በምትለይ ቀጭን የመሆንና ያለ መሆን መስመር መጓዛችንም አያስደነግጠንም። ይህ መዛል ይባላል። እያደር በአቅጣጫው ልብን የኋሊት እየጎተተ የሚጥለው ፋይዳ ቢስ ጉዳይ መጨመር አያስበረግገንም። ‘እህሳ?’ ስንባል ‘ይህችን ታህል አለሁ፣ ይህችን ታህል እተነፍሳለሁ’ ነች መልሳችን!

ቸልተኝነት ሳንወድ በግድ ተግተናት ከነፍስና ሥጋችን ጋር ያዋሀድናት የራዕያችን ሁሉ መነሻ መሆኗ ጥቂቶችን ፀጉር ያስነጫል። በቀረው መንገዱን አማን አገሩን ሰላም ያድርገው የሰርክ መፈክር ነው። ከዚያ አልፎ ጉጉት፣ ከዚያል አልፎ ውጥን እንኳን ‘በዘንድሮ በአምናውም አልተዳርኩ’ እያሰኘ እጃችንን አጣጥፎ አስቀምጦናል። በዳና ጉሰማ ተመላልሰን ካጎደጎድነውና ካረስነው መሬት ይልቅ፣ እንዲህ በየጥጋጥጉ ነገር ዓለሙን ለባለፀበሎች በፈቃዳችን ትተን የተቀመጥንበት ሥፍራ ጥልቀት አለው። የማጣታችን መለኪያም ክፍለ ዘመን ነው። ዳገቱን የወጣንበትን፣ ቁልቁለቱን የተንደረደርንበት ዕድሜ ቀርጥፎ ይበላዋል። መንገድ እያመጣን መንገድ እየወሰደን አንዴ ሲያጣላን አንዴ ሲያዋድደን በቅብብሎሽ እዚህኛው ፌርማታ ላይ በዚህ ስሜት ተገናኝተናል። ‘ዋ’ አለ አሞራ!

“አንተዬ እስኪ ቶሎ ቶሎ በል! ምን ያለው ቀርፋፋ ነው እናንተ?” የአነጋገሯ ዘዬ ከተሜ ባያስብላትም ሞንሟና በመሆኗ ወያላውን ይዛዋለች። “አይዞሽ! አሁን ይሞላል። ያውም በእኛው ተነሳሽነትና በእኛው ድምፅ ነው የምንሞላው። እንኳን እዚህ ላይ ዓባይ ላይ ቆርጠናል…” ወያላው ንጭንጯን አብርዶ እሷው ውስጥ ትውስታ ለመቆስቆስ ያሰበ ይመስላል። ጓደኞቹና ተራ አስከባሪ ወጠምሻዎች ላይ እንደ አንበሳ እየተንጎማለለ፣ እዚህች ልጅ ጋ ሲደርስ ወገቡን እንደተመታ እባብ ይርመጠመጣል። “ስለሌላ ነገር ማን ጠየቀህ? ወሬውን ትተህ ጥራማ!” ትላለች። ሐሳቧን ማርጋት ቀልቧን መሰብሰብ እንደ ከበዳት ያስተዋለ፣ በጠዋት አክለፍልፎ ያስወጣትን የማጀቷን አኳኋን እንዲሰልል ይገፋፋል። ወያላው፣ “ይሞላል ስልሽ፣ ዋናው ማመን ነው…” አላት። ይኼን ሲላት እርጎ የመሰለ ነጠላቸውን በወጉ ያጣፉ ሴት ወይዘሮ እጁን ተደግፈው ይገባሉ። ሥፍራቸውን እንደያዙ በረጅሙ ተንፍሰው፣ “ዋናው ማመን ነው አልክ?” አሉት። “አዎ፣ ምንም ሳንይዝ አለማመን ተጨምሮማ እንዴት ሆኖ?” አላቸው። ሳቅ ብለው፣ “ኧረ ልክ ነህ ይኼው አለን እንዳመንን። ቋጠሯችን ሳይፈታ፣ ጥያቄያችን ሳይመለስ፣ ስንጮህ ዝም እያለ ይኼው አለን እንዳመንን…” አሉ እንደ ማቃሰት ብለው። መቼ ይሆን በመንግሥት የምናኮርፈው አንሶን ወደ ፈጣሪ የዞርነው?

“ምነው እትዬ?” እንዲያሳልፉት አልያም እንዲጠጉለት ፈልጎ ዓይን ዓይናቸውን የሚያይ ወጣት ፊታቸው ቆሟል። ወይዘሮዋ ወጣቱን ቀና ብለው ዓይተው አንገቱን አንቀው ይስሙታል። “አንተ፣ ና እስኪ ጎኔ ቁጭ በል። ሥራ ይዘህ ከራስህ የሚተርፍ ገንዘብ ኖሮህ ምርኩዝ ባትሆነኝም፣ እንዲህ ትልቅ ሰው ሆነህ ሳይህ እኮ እንዴት እንደምደሰት አታውቅም?” ይሉታል። ለመሆኑ ሥራ እየፈለግክ ነው? ታመለክታለህ በየመሥሪያ ቤቱ?” ይጠይቁታል። “አይ እማማ እንኳን ለሥራ ‘ፌስቡክ’ ላይም ‘ሪኩዌስት’ የሚመልስ ሰው እየመነመነ ነው…” ሲላቸው ፈቀቅ ብለውለት ተቀመጠ። ታክሲያቺን ስለሞላ መንቀሳቀስ ጀምረናል። ከአንድ አካባቢ የተሰበሰቡ ተሳፋሪዎች በአብዛኛው ስለሚተዋወቁ ለዓውደ ዓመት የተሰባሰቡ ቤተ ዘመድ መስለዋል። ጋቢና የተቀመጠው መጨረሻ ወንበር ወዳለው ዞሮ፣ “ሒሳብ እኔ ነኝ እሺ? ትናንት የተሸነፋችሁት ይበቃል…” ይላል። የዕቁብና የዕድር ስብስቦች በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ታዳሚዎች ማኅበራት መቀየራቸውን በፎርም የሚነግረን ይመስላል። “ብቻ ዲግሪህን ደህና ቦታ አስቀምጠው። ጋዋን ለብሰህ የተነሳኸውን ፎቶም አሳጥበህ በትልቁ ግድግዳ ላይ አኑረው። የት አባቱ፣ ማንን ደስ ይበለው ብለህ? እውነት በሥራ የሚያልፍ ቢሆን ኖሮ አህያ ላይ የሚደርስበት አለ?” ወይዘሮዋ ሳይታሰብ ጮሁ። ሆድ ለባሰው የሚሆን ማንፀሪያ የማይገጥም ፍጥረት ጠቀሱ። “ሥራ ፍለጋ ከምንባክነው በላይ አፅናኝ ፍለጋ ዓለምን ባንዞር ከምላሴ ፀጉር…” ይላል አንዱ ወደ መጨረሻ ወንበር። ድሮስ ሰው ወደ ኋላ ቀረት ቀረት የሚለው ለነገር አይደል? 

ጉዟችን ተጀምሯል። “አይ ዛሬ ቀን፣ አይ ዕድሌ…” ያጉተመትማል አንድ ጎልማሳ። “ምንድነው እሱ? ምንድነው የምትለው?” ወያላው እሱን መስሎት ይጮህበታል። “ኧረ እባክህ አንተ ሰውዬ ተወኝ ወዲህ ነው። ኧረ፣ ኧረ ምን አደረግኩህ?” ወደ ላይ አንጋጦ የዛቻ ያህል ከምስቅልቅሉ መነሻ ጋር በሐሳብ ይፋጠጣል። “ምን እህህ እያልክ ብቻህን ታምጠዋለህ? የሆንከውን ንገረንና መፍትሔ እንፈልግ፣ ካልሆነ ዝም በል…” አለው ከአጠገቡ የተቀመጠ ወጣት ተሳፋሪ። ቀጠለና ደግሞ፣ “ከዚህ የበለጠ በሽታ አለ ግን? ሲሞላልንና ሲሳካልን የምንደነፋውን ያህል ባይሆን እንኳ ምነው ሲያመን ብንናገር? ሁሉን በሆዳችን ይዘን ሁሉን በሆዳችን ሰፍረን እንችላለን እንዴ?” ይላል። ጋቢና የተሰየመች መለሎ፣ “ቆይ አንተ የሆድ ሐኪም ነህ? ወይስ ጆሮ ጠቢ? ምነው ይኼን ያህል የሰው ቁስል አሳከከህ?” ትለዋለች ሳይሰማት። ይኼኔ ሰውዬው ችግሩን ማውራት ይጀምራል። ይሻለዋል!

“እኔ አላመመኝም፣ ምን ሊለኝ ነው እናንተ፡፡ እኔ ‘ዲግሪ’ ያለኝ ሰው ነኝ። ሥራ ልወዳደር ከክልል ነበር የመጣሁት። እዚህ ስደርስ ያመጣኝ ‘አይሱዙ’ የመጣህበትን ክፈለኝ ብሎ የዲግሪ ምስክር ወረቀቴን ወሰደብኝ። መላው ጠፍቶብኝ ነው እባካችሁ? እኔ ልመና አልችልበትም…” አለና ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እባካችሁ እኔ ለአገሩ እንግዳ ነኝ። የመሣፈሪያዬን 600 ብር ብታወጡልኝና አገሬ ብገባ? እንዲያው ሌላ አላስቸግርም…” ብሎ አረፈው። ይኼኔ የሰማውን ሰምቶ አላስችል ያለው መተረብ ጀመረ። “ዝም አትበሉ እንጂ እሳት አደጋ ጥሩ፣ የፀሐይዋ ቃጠሎ ሳያንሰን ደግሞ በባለዲግሪ እንቃጠል? ወይ ዘመን?”  ሲል ከአጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ከፊታችን ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አዛውንት ቀበል አድርገው፣ “እንደ እኔ አስተያየት እንደ ዘንድሮ የአለማመን ሥልት መራቀቅ ከሆነ፣ 8100 ላይ ለህዳሴው ግድብ የምናዋጣው ገንዘብ ሳይቀር በ‘ሳይበር አታክ’ እንዳይዘረፍ ነው…” አሉ። ወዲያው ለቀልድና ተረብ ይራኮት የነበረው ተሳፋሪ ሁሉ በአዛውንቷ አስተያየት ከማግጠጥ ተቆጥቦ እንደ መደንገጥ ሲል ይታያል። ‘‘መንገድ ለመንገድ አልችለው ብለናል ልመና ጭራሽ በቴክኖሎጂ ሊታገዝ? የለንማ…’’ የሚለው ብቻውን ይስቃል፡፡ ዘመኑ እንዲህ ሆኖ ይረፈው?

 በዚህ ሁሉ ጫጫታ መሀል መጨረሻ ወንበር ጥጓን ይዛ የተቀመጠች አጭር የጠይም ቆንጆ፣ “አወይ ልጅነቴ! እኔስ ደርሶ ልጅነቴ እየናፈቀ አስቸገረኝ…” ብላ ሲያመልጣት በአካባቢዋ ያሉ ሁሉ ሰሟት። “እንዴት?” ሲላት ከጎኗ ተጣቦ የተቀመጠው ቀውላላ፣ “አታየውም ኑሯችንን? ደስታችን፣ ሰላማችን፣ ሳቃችን፣ ሐዘናችን፣ ጭንቀታችን ምኑ ቅጡ፣ ሁሉ ነገር ከገንዘብ ጋር ተቆራኝቶ ስታይ የምንም ነገር ባሪያ ያልሆንክበት፣ ስለምንም ነገር የማትጨነቅበት ዛሬህን ብቻ የምትኖርበት የልጅነት ዘመን አይናፍቅህም? ማደግ እኮ እንዴት ያለ ክፉ ነገር መሰለህ?” አለችው። “እዚህ ጋ ወራጅ አለ፣ አደራ የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር ስትደጋግሚው ሰው እየመረጥሽ…” ብሎ ወያላው በሩን ከፈተው። እኛም መጨረሻችን መሆኑን አውቀን ቀስ በቀስ ተግተልትለን ወርደን ተበታተንን። ጉዳያችን ወደፊት ልባችን ወደኋላ እየቀረ፣ ‘ወቸ ጉድ!’ እያልን ተለያየን። መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት