ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች መካከል ተጠቃሽ የሆኑት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ልማት ለማስፋፋት እየቀረበ ያለው የመሬት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉ ተጠቆመ፡፡
የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር እንዳመለከተው በተለይ የአበባ እርሻዎችን ለማስፋፋት የሚጠይቁ ተጨማሪ የመሬት ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ባለመገኘታቸው ዘርፉ ሊያስገኝ የሚገባውን ያህል የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኝ እያደረገ ነው፡፡
በዘርፉ አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮች የመሬት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ያመለከቱት የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታዎድሮስ ዘውዱ ተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ የሚችለው ይህ ዘርፍ በማልሚያ ቦታ እጥት እየፈተነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአበባ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በማስፋት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ አስፈላጊውን የመሬት አቅርቦት ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን መሬት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ብዙ ባለሀብቶች ያላቸውን እርሻ ማስፋፋት ይፈልጋሉ፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ‹‹እነዚህ ባለሀብቶች ገበያ ያላቸው፣ አቅም የፈጠሩና ምርቶቻቸውን በሚገባ ያስተዋወቁ በመሆኑ የምርት መጠናቸውን ለመጨመር ይፈልጋሉ፣ ለዚህ ደግሞ ቦታ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
ችግሩ በአበባ ልማት ዘርፍ ላይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በአትክልትና በፍራፍሬ ልማት ዘርፍም ተመሳሳይ ችግር በመኖሩ መንግሥት ይህንን የመሬት አቅርቦት ጥያቄ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ክልሎችም ዘርፉ ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር መሬት ማዘጋጀት ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ አቶ ቴዎድሮስ መክረዋል፡፡
በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል አንዱ መንገድ የሆርቲካልቸር ልማትን ማስፋፋት እንደሆነ ማኅበራቸው በፅኑ እንደሚያምን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ለዚህ ደግሞ ክልሎች ቦታ ማዘጋጀት እንዳለባቸው፣ የፌዴራል መንግሥትም ይህንን ማስገንዘብ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
ከዚሁ የመሬት ፍላጎት ጋር በተያያዘና አጠቃላይ የሆርቲካልቸር ስለዘርፉ የልማት እንቅስቃሴ በተመለከተ ማኅበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን ውይይት አድርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ በዚህ የውይይት መድረክ ላይም መንግሥት በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍላጎትና ሊያስገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ታሳቢ በማድረግ ለዘርፉ የመሬት ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ እንዲሰጥ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በተካሄደው የውይይት መድረክ በአሁን ወቅት የአበባ ምርት ከሚለማባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ ሌሎች ክልሎችም የማልሚያ ቦታ አዘጋጅተው የዘርፉ ልማት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፋ ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑ ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠበት እንደነበር ታውቋል፡፡ ለአገራዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝትም ሆነ ኢንቨስትመንቱን በክልሎች በማስፋፋት የክልሎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በውይይቱ ያጋራ መግባባት መፈጠሩን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
በመሆኑም ክልሎች ለአበባ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ የማልሚያ ቦታ ዝግጅት ያደርጉ ዘንድም ጥያቄ መቅረቡን አስረድተዋል።
ውይይት መድረኩ ላይ የክልል የኢንቨስትመንትና ግብርና ቢሮ ተወካዮች የተሳተፉበት ሲሆን፣ ከማልሚያ ቦታ ዕጦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሲዳማ፣ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችና የደቡብ ክልሎች ተወካዮች የዘርፉ አልሚዎች ወደ ክልሎቻቸው ቢመጡ የማልሚያ ቦታ እንደሚቀርቡና በአሁኑ ወቅትም የማልሚያ ቦታ በተጨባጭ ተዘጋጅቶ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አቶ ቴዎድሮስ በበኩላቸው የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማልሚያ ቦታ ማዘጋጀታቸውን የገለጹ ክልሎች ያዘጋጁትን መሬት መጠን ጭምር የጠቀሱ ቢሆንም የመሬት አሰጣጡ ቀልጣፋና ውጣ ውረድ የሌለበት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በቃል የገለጹትንም በተግባር ለመለወጥ መቻላቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ፣ ይህንን ማድረግ ከቻሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ዘርፉ እየተቀላቀሉ የሚገኙ አዳዲስ ባለሀብቶችን መሳብ እንደሚችሉ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአበባ ምርት እየለማ የሚገኘው አጠቃላይ የመሬት ይዞታ 1750 ሔክታር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 85 በመቶው የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ቀሪው ይዞታ ደግሞ በደቡብና በአማራ ክልሎች እንደሚገኝ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የተጠጋ ሲሆን ይህንን ገቢ በእጥፍ ለማሳደግ ውጥን ያለው መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል፡፡ ለምርቶቹ ሰፊ ዓለም አቀፍ ገበያ በመኖሩ የመሬት አቅርቦች ችግርን በመፍታት የምርት መጠኑን በመጨመር ገቢውን ለማሳደግ እንዲቻል የመንግሥትን ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሻ ተጠቁሟል።