Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከነዳጅ ጥቅል ድጎማ ለመውጣት የሚደረገው ሩጫና ያንዣበበው ሥጋት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም የተመለከቱ የውሳኔ ሐሳቦችን በማፅደቅ፣ ነዳጅን በተመለከተ አዲስ ተግባራዊ የሚደረግ አሠራር እንደሚኖር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

እያደገ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሒደት በማስቀረት ወደ ቀደመው የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ሥርዓት እንዲመለስ ለማድረግ የሚያስችል የዋጋ ማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ውሳኔውን ለማሳለፍ አንዱ ምክንያት እንደሆነ መንግስት በወቅቱ አስታውቋል። በተጨማሪም በሥራ ላይ ያለው ጥቅል የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሒደት ማስቀረት በሚደረገው የዋጋ ማስተካከያ ዕርምጃ ውጥን መያዙን ገልጾ ነበር። በዚህ ውጥን መሠረት የሚደረገው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የጎላ ተፅዕኖ በማያስከትል አግባብ የነዳጅ ዋጋ ድጎማ አሠራር ሥርዓት እንደሚተገበር መንግስት ባሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ተገልጿል። ይህንን ውሳኔ አስፈላጊ ያደረጉት ገፊ ምክንያቶች ከላይ የተገለጹት ስለመሆናቸው በወቅቱ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ የሚሰጠው ድጋፍ ‹‹ድጎማ›› ይባል እንጂ በትክክል ድጎማ አይደለም ብለው የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ምክንያታቸውን ሲያብራሩም ድጎማ ሲሰጥ ፖሊሲና ፕሮሲጀር (ቅደም ተከተል) ማስቀመጥ የግድ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ድጎማ የሚሰጠው ለተቸገረው ኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ የሚናገሩት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኑረዲን መሀመድ ናቸው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት እየደጎመ የሚገኘው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነና አንድን መኪና በቡድን ለሚያንቀሳቅሰውና አምስት መኪና ለሚያቀያይረው ባለሀብት ግለሰብ መንግሥት እኩል ድጎማ የሚሰጥበት አሠራር ሲተገበር መቆየቱን ያስረዳሉ።

በነዳጅ ዘርፍ ያለው ድጎማ በፖሊሲ ያልተደገፈ የጥቅል ድጎማ አሠራር እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን፣ ለአብነትም በስንዴ፣ በስኳር፣ በዘይት ላይ ያለው ድጎማ በፖሊሲ የተደገፈ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፍ የነዳጅ መሸጫ ዋጋና በአገር ውስጥ መሸጫ ዋጋ መካከል በየወሩ እየታየ መስተካከል ሲገባው አልተተገበረም። በዚህ ምክንያት በመንግሥት ላይ የመጣውን ዕዳ ከአሁኑ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴ አማካኝነት ከዓመት በፊት እንደተጠና አቶ ኑረዲን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት ነዳጅ በዓለም አቀፉ ዋጋና በአገር ውስጥ በሚሸጥበት ዋጋ ላይ የነበረው ልዩነት አነስተኛ ነበር። ይህም የሆነው መንግሥት የአገር ውስጥ የመሸጫ ዋጋን የሚደጉም በመሆኑ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት መንግስት ለነዳጅ ድጎማ የሚያወጣው አነስተኛ መሆኑን፣ ይህም በሊትር ከአምስት እስከ ስድስት ብር እንደነበር በመንግሥት አካላት ሲገለጽ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግን በዓለም አቀፍ ገበያውና በአገር ውስጥ የመሸጫ ዋጋ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ከግማሽ እንዳለፈና ይህንምም መንግሥት በድጎማ ተሸክሞ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰው ተጠቅሷል፡፡ ስለሆነም ይህንን ጉዳይ ሕዝቡ ሊጋራው እንደሚገባ መታመኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የገለጸ ሲሆን፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ የታለመውን የነዳጅ ድጎማና የዋጋ ማሻሻያን አስመልክቶም ባሳለፍነው ሳምንት ለሚዲያ አካላት ለማሳወቅ ባዘጋጀው መድረክ ላይ አስታውቋል፡፡

መንግሥት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ወደ ታች የሚመለስበት ዕድል ስለሌለ ቀስ በቀስ የታለመ ድጎማ ወይም የዋጋ ማስተካከያን ወደ ተጠቃሚው የሚተላለፍበትን ሥርዓት ቀይሶ ወደ ተግባር የመግባቱ ተገቢነት ብዙዎች ይቀበሉታል። ነገር ግን በርካታ ውጫዊና ውስጣዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተንሰራፍተው በሚገኝበት በዚህ ወቅት ወደ ትግበራ የሚደረገው መንደርደር ጊዜውን ያልጠበቀ አካሄድ ነው የሚሉትም ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በነዳጅ ዘርፉ ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ባለሙያ የትራንስፖርትና የንግድ ትራንስፖርትን ለመደጎም የታሰበውን ውሳኔ አስታውሰው ውጤታማነቱን ግን በጥርጣሬ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ መንግሥት አፈጻጸሙን ከሚያደርግበት ዘዴ አንዱ ከኩፖን ጋር የተገናኘ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ባለሙያው ዕምነት በኩፖን አገልግሎት መሆኑ ለሙስና የሚያጋልጥ ነው፡፡ አሁን በሚታየው አሠራርና ብዙ ነገሮች ባልተደራጁበት ሁኔታ የቁጥጥር ሥራው በጣም ደካማ በሆነበት ሁኔታ፣ በዚህ መሠረት ይሠራል ማለት ሌላ የሙስና መንገድ መክፈት ነው ብለዋል፡፡ 

በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚቻልን ጉዳይ መቆጣጠር ያልቻለ አካል አዲሱ አሠራርን ለመቆጣጠር ይከብደዋል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ባለሙያው ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ነዳጅን በተመለከተ ያሉት ተቆጣጣሪ አካላት ዋነኛ ሥራቸው ሕግ ማስከበር ሊሆን ይገባል የሚሉት ባለሙያው፣ ሕግ ማስከበር የተለያዩ ችግሮችን የሚቀርፍ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከብር የመግዛት አቅም መውረድ ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ የከፋ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት የሚፈለገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋትን ዓላማ አድርጎ ባፀደቀው አዋጅ እየተመራ ቢቆይም፣ የአገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የዓለም አቀፉን ዋጋ በሚያንፀባርቅ መልኩ በየጊዜው እየተከለሰ ለሸማቾች እንዲቀርብ ባለመደረጉ በዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ላይ ከፍተኛ ዕዳ እየተከማቸ መሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚያነሱት ሐሳብ ነው።  

የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ መነሳት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው ወገኖች ለማስረጃነት የሚያስቀምጡት ነጥብ ቢኖር ተፅዕኖው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ የሚወድቅ መሆኑን ነው። 

የነዳጅ ጭማሪ ገበያ ውስጥ የዋጋ መናርን ያስከትላል፣ ሁሉንም ይነካካል የሚሉት ባለሙያዎች፣ በተለይ የተወሰነ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ በሸቀጦች ላይ የሚደረጉ አንዳንድ ጭማሪዎች ከወዲሁ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል ይላሉ፡፡ 

በሌላ በኩል አቶ ኑረዲን እንደሚያስረዱት ድጎማ ማድረግ ካስፈለገ በትክክል ድጎማው የሚያስፈልገው የደሃ ኅብረተሰብ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ላይ የተከማቸውን ዕዳ ከዚህ በላይ እንዳያሻቅብ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህንንም ለማድረግ የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያና የዋጋ ማሻሻያውን በመተግበር ቀስ በቀስ በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ መካካል ያለውን ልዩነት እንዲቀንስ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ የሚደግፍ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ የሚያደርሱ ዘርፎችን በመለየት ድጎማ ማድረግ ሲሆን፣ የነዳጅ ድጎማ አሠራሩ የመንግሥት በጀት ላይ የሚያስከትለውን ከፍተኛ የሆነ የዕዳ ጫና መቀነስ ሌላኛው ታሳቢ የተደረገ ጉዳይ እንደሆነ ይገለጻሉ፡፡ 

ነዳጅ ላይ የሚደረገው ድጎማ በፖሊሲ ያልተቀመጠና መንግሥት በጀት ያልመደበለት ስለሆነ የፋይናንስ ምንጩ ግልፅ ሆኖ መቀመጥ እንደሚገባው የሚናገሩት አቶ ኑረዲን፣ እንዲሁም ከኅብረተሰብ ፍጆታ ጋር የተገናኙ ነዳጅ ምርቶች ላይ ድጎማው ቀስ በቀስ የሚነሳበት አግባብ ይቀመጥ የሚል ምክረ ሐሳብ  እንደቀረበ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ኑረዲን እንዳስረዱት፣ ከድጎማው ለመውጣት በኮሚቴ ቀርቦ የፀደቀው ውሳኔ የግል ተሽከርካሪዎችን የሚመለከት ሲሆን ይህም በየስድስት ወሩ 25 በመቶ ወይም በወቅቱ (በታኅሳስ 2014 ዓ.ም) በነበረው የ20 ብር ልዩነት መካከል አምስት ብር እየተቀነሰ በሁለት ዓመት ውስጥ ከድጎማ ሥርዓቱ መውጣትን ያለመ ነው፡፡

ድጎማው እንዲያገኙ ተብለው የተመረጡ እንደ ሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላሉት ደግሞ ድጎማው በሂደት እየተቀነሰ በአምስት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከድጎማ እንዲወጡ መወሰኑን ገልጸዋል።

ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ነገሮች በከፍተኛ ሁኔታ መለወጣቸው በተለይም ከዩክሩይንና ሩሲያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በፍተኛ ደረጃ ንሯል። ከዚህ ቀደም በቀረበው ጥናት በዓመት ውስጥ መንግሥት ለነዳጅ ዘርፍ 33 ቢሊዮን ይደጉም የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከ73 ቢሊዮን ብር በላይ አሻቅቧል። በአጠቃላይ ከፍጆታ ማደግ ጋር ተዳምሮ አሁን ካለው ዋጋ የተሻለ መረጋጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይከሰታል ተብሎ ባለመታመኑ መንግሥት በድጎማ የተሸከመውን ከፍተኛ ጫና ለኅብረተሰቡ ካላጋራ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚገጥመው አቶ ኑረዲን አመላክተዋል፡፡

ድጎማው ተግባራዊ ሲሆን የታሰበው ነገር ቢኖር ድጎማው በማደያ ደረጃ እንዲደረግ የሚል ታሳቢ ጉዳይ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ለአብነትም አንድ ባጃጅ ማደያ ሄዶ የነዳጅ ዋጋው 33 ብር ሆኖ የሚከፍለው 28 ብር ሲሆን፣ አምስት ብሩን ለማደያው መንግሥት የሚከፍል ይሆናል፡፡ በነዳጅ ማሽኑ ‹‹ዲስፔንሰር›› ላይ ሁለት ዓይነት ዋጋ ማስገባት ስለማይቻል ለሁሉም በ33 ብር ደረሰኝ ተቆርጦ እንዲገለገሉና አምስት ብሩ ግን በመንግሥት ለማደያው የሚከፈል እንደሆነ ገልጸዋል። በመንግሥት ተከፋይ የሚሆነው ብር የዱቤ ካርድ ተቆርጦበት በየሳምንቱ ወይም በወሩ መጨረሻ ማደያው ከመንግሥት ክፍያውን እንዲሰበስብ የሚል አሠራር ተግባራዊ እንዲደረግ ሐሳብ ቀርቦ ነበር።

በሁለተኛነት የቀረበው አማራጭ አሠራር አማካይ የነዳጅ አጠቃቀምን የተመለከተ መረጃ በመሰብሰብ ተሰልቶ እንዲተገበር የሚል ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ አንድ ባጃጅ በቀንና በወር ስንት ሊትር ይጠቀማል? የሚለው ተሰልቶ የሚደረስበትን የድጎማ ክፍያ መጠን አስቀድሞ ለማደያ በመክፈል ማደያው በየጊዜው የቆረጠውን የዱቤ ካርድ ይዞ ሲቀርብ ከዕዳው ላይ እንዲቀነስ ማድረግ የሚል አማራጭ እንደነበረ አቶ ኑረዲን ተናግረዋል፡፡

በሦስተኛነት የቀረበው አማራጭ የኩፖን ግብይት ሥርዓትን መተግበር ሲሆን፣ የድጎማ ዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ኩፖን ይዘው ወደ ማደያ በመሄድ ተፈርሞላቸው፣ አንድ ኩፖን ለማደያው፣ ሌላኛው ለተጠቃሚው፣ ሦስተኛው ደግሞ ከማኅደር ጋር ቀሪ ሆኖ እየተወራረደ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚል ሐሳብ እንደሆነና ይህ አሠራርም ተቀባይነትን እንዳገኘ አብራርተዋል።

የታለመ የነዳጅ ድጎማና የዋጋ ማሻሻያው እንዴት ይተግበር? ሲባል ስድስት ወር የመለማመጃ ጊዜ እንዲሆን የሚል ሐሳብ እንደቀረበ ያስታወቁት አቶ ኑረዲን፣ ከስድስት ወር በኋላ የሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን መስጠት፣ አሠራሩን መፈተሽ ከዚያ በኋላ መተግበር የሚለው ሲሆን፣ በዚህ ልክ ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ፀድቆ ከጥር 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የዝግጅት ጊዜ እንደተሰጠ ተናግረዋል፡፡

ይህ ከሆነ አራት ወራት ቢቆጠሩም እስካሁን ሥራው 70 ከመቶ ያህል እንዳልደረሰ የታወቀ ሲሆን፣ አተገባበሩ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. መጀመሩ አጠራጣሪ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሚደጎሙት መኪኖች ዝርዝር የመረጃ ቋት ውስጥ ገብቶ መታወቅ ስላለበት ነው፡፡ ሁለተኛው መኪኖች በሙሉ ታግ መለጠፍ፣ አሽከርካሪዎቹ መታወቂያ መያዝ ስለሚገባቸው፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በበቂ ልክ እንዳልተሠሩ ይገለጻል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኘው 1.3 ሚሊዮን ተሽከርካሪ ውስጥ ወደ ድጎማ አሠራር ውስጥ የሚገቡት ብዛት ከ300 ሺሕ እንደማይበልጥ አቶ ኑረዲን አስታውቀዋል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ ወር በተከናወነ ጥናት የቀረበ መረጃ እንደሚያሳየው የሕዝብ ትራንስፖርት ተብለው በከተሞች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡት እንደ አንበሳ፣ ሸገርና ፐብሊክ ባስ ተብለው የሚጠሩት ተሽከርካሪዎች ብዛታቸው 1,683 ሲሆን፣ ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት ያሉ በመላ አገሪቱ በ232 የጉዞ መስመሮች የሚንቀሳቀሱ 1,518 መደበኛ የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ተሸርካሪዎች አሉ፡፡

የመጫን አቅማቸው ከ12 እስከ 47 የሆኑ መለስተኛ አውቶቡሶች ብዛታቸው 84,787 እንደሆነ የተገኘው አኃዛዊ መረጃ የሚሳይ ሲሆን፣ የኮድ አንድና ሦስት የሚኒ ባስ ታክሲዎች ቁጥር ደግሞ 95,452 ናቸው፡፡ የድንበር ተሻጋሪ ጭነት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 15,248 እንደሆነ በጥናቱ የቀረበ ሲሆን ሆኖም እነዚህ ተሽከርካሪዎች በውሳኔ ወቅት እንዲወጡ መደረጋቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል እስከ ሚያዚያ ወር ከ11ዱ ክልሎች በተሰበሰበው መረጃ መሠረት የባለ ሦስት እግር ተሽርካሪዎች ቁጥር 112 ሺሕ ይደርሳል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ልዩ የሳሎን ታክሲዎች ብሎ የሚጠራቸው እንደ ራይድ፣ ሰረገላ እንዲሁም የቅንጦት ባስ ተብለው ከሚመደቡት ደግሞ እንደ ሰላም፣ ገዳ፣ አፍሪካ ባስ ዓይነቶቹ ምክንያቱም ተጨማሪ የጉዞ ማይሎችን ሄደው ምቾትን ጠብቀው አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ ሳቢያ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ማዕቀፍ ውስጥ የማይካተቱ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ 

በሌላ በኩል የ2014 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የኢኮኖሚ አፈጻጸምን በማስመልከት፣ ከብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመላከተው ነዳጅን በተመለከተ የዋጋ ንረቱን ተከትሎ የሚኖርውን የበጀት ጫና መቀነስ ይቻል ዘንድ፣ ወጥ ከሆነው የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ በመውጣት በተጠና መንገድ ድጎማው ለሚያስፈልጋቸው አካላት ብቻ እንዲሆን በዕቅድ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች