Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ ከፍተኛ አመራሮቹን ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባዔውን ያደርጋል

ኢዜማ ከፍተኛ አመራሮቹን ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባዔውን ያደርጋል

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በግንቦት ወር መጨረሻ ሊያካሂድ ወጥኖ የነበረውን አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ሰኔ 11 እና 12 2014 ዓ.ም. ለማድረግና የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮችም በዚሁ ጉባዔ ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ከሦስት ዓመት በፊት ሲመሠረት በነበረው ጉባዔ አማካይነት ከፍተኛ አመራሮችን መርጦ የነበረ ሲሆን፣ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የፓርቲው መሪና አቶ አንዷለም አራጌ ደግሞ በምክትል መሪነት ተመርጠው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ፓርቲውን በሊቀመንበርነት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ ሲሆኑ፣ በምክትል ሊቀመንበርነት ደግሞ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ናቸው። እነዚህ ኃላፊነቶችን ጨምሮ ለጸሐፊና ፋይናንስ ኃላፊነቶችም ምርጫው የሚካሄድ ይሆናል።

ከጉባዔው በፊት ለ19 ቀናት ከዕጩዎቹ ለአባላቱ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም ጉባዔው ሁለት ቀን ሲቀረው ቅስቀሳው የሚቆም ይሆናል።

የፓርቲው አመራሮች ሦስት ዓመታት ከስሞላቸውና በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት አመራር በድጋሚ መምረጥ እንዳለበት ስለተደነገገ፣ በሚመጣው ጉባዔ ምርጫ እንደሚያካሂድ ተገልጿል። ለዚህም ሦስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴና ሰባት አባላት ያሉት የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መቋቋሙ ተጠቁሟል።

የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙሉዓለም (ዶ/ር) ተገኝወርቅ ፓርቲው በሚያካሂደው በዚህ ጉባዔ ላይ የፓርቲው አራት አካላትና አንድ የውጭ ኦዲተር ሪፖርት እንደሚያቀርቡ፣ ጉባዔውም ይህን አድምጦ ውይይት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

እንደ ሙሉአለም (ዶ/ር) ገለጻ ከሆነ ሁለቱ የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴና አስመራጭ ኮሚቴ ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ የሥራዎቻቸውን ማከናወኛ መመርያ ማፅደቅን፣ የሥራ ዕቅድና በጀት ማዘጋጀትንና ንዑስ ኮሚቴዎችን ማዋቀርን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር አክለዋል።

‹‹ከምርጫ ቦርድ በሕገ ደንቡ ላይ እነዲሻሻሉ ጥቆማ የተሰጠባቸውን ነጥቦች መሠረት በማድረግ፣ የሕገ ደንብ ማሻሻሉ ሥራ የሚያከናውኑ ንዑሳን ኮሚቴዎች ውስጥ በጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ተቋቁሟል፤›› ሲሉ ሙሉዓለም (ዶ/ር) በመግለጫው ተናግረዋል።

ፓርቲው አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ለማድረግ አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ባልተገለጹ ምክንያቶች ወደ ሰኔ ወር አጋማሽ መገፋቱን ተገልጿል። ግንቦት 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከተመሠረተ ሦስት ዓመት የሞላው ኢዜማ በሕገ ደንቡ መሠረት በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ መደበኛ ጉባዔውን የሚያካሂድና አመራሮቹን የሚመርጥ ሲሆን ይህም የመጀመርያው መደበኛ ጉባዔ ይሆናል።

አስመራጭ ኮሚቴው ሲያከናውናቸው ከነበሩት ሥራዎች መካከል ዕጩ ተወዳዳሪዎችን መመዝገቢያ መስፈርት ማዘጋጀት ሲሆን፣ ለሁሉም የምርጫ ክልልሎች እንዲደርሳቸውና ማንኛውም የፓርቲው አባል ዕጩ መሆንና መወዳደር እንዲችል ማድረግ መሆኑን የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ሥዩም መንገሻ ገልጸዋል።

‹‹ለእያንዳንዳቸው ኃላፊነት ቦታዎች ሦስት ሦስት ዕጩዎች ለመጨረሻ ውድድር የሚካፈሉ ሲሆን፣ ኃላፊነት ቦታዎቹም ለመሪ፣ ምክትል መሪ፣ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ዋና ጸሐፊና የፋይናንስ ኃላፊ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ ሥዩም ገልጸዋል።

በ19 ቀን ውስጥ ለሚካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ ዕጩዎቹ በኃላፊነት፣ በመከባበርና የፓርቲውን እሴትና ሕገ ደንብ በማክበር መሆን እንዳለበት፣ ጠቁመው፣ አሁን ያሉት የፓርቲው አመራሮች የኃላፊነት ጊዜያቸው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ጉባዔው እስኪካሄድ ድረስም በኃላፊነት እንደሚቆዩም ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...