Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ዓመታዊ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከስድስት በመቶ በላይ ዕድገት እንደሚኖረው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የ2014 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የኢኮኖሚ አፈጻጸምን በማስመልከት፣ ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት በሰጠው መግለጫ፣ የአገር ውስጥ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት በአማካይ 6.6 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት ሩብ ዓመታት የተመዘገበው ዕድገት መሠረት በማድረግ የዓመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ በ6.6 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለዚህም በዋነኝነት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሰብል ምርት ላይ የታየው ዕመርታ ተጠቃሸ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።

ከመኸር ምርት በተጨማሪ በበጋ ስንዴ ምርት በ613 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ከ25 ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል ብሏል።

ከውጭ ንግድ ከተገኘው 2.95 ቢሊዮን ዶላር ውስጥም የግብርናው ድርሻ 2.05 ቢሊዮን ሲሆን ከግብርናው በመቀጠል የማዕድን ዘርፉ 453 ሚልዮን ዶላርና አምራች ኢንዱስትሪው በ378.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘባቸው ዘርፎች መሆናቸውን በመግለጫው አንስቷል፡፡

የዘጠኝ ወራት የውጪ ምንዛሪ ግኝት ዝቅ ያለ ቢሆንም ከነበረው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት አንፃር በበጀት ዓመቱ የሚጠበቀውን የውጭ ዕዳ ክፍያ በአግባቡ ለመከፈል ችለናል።

ከኢንቨስትመንት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው የብድርና ቁጠባ መጠንም ላይ ጭማሪዎች የተመዘገቡበት ነው ያለው ምክር ቤቱ፣ የባንኮች አጠቃላይ የቁጠባ መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ በማደግ 1.6 ትሪልዮን ብር መድረሱን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወስጥ 1.4 ሚልዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና ሙያዊ ሥልጠና ወስደው በውጭ አገሮች ማለትም በኳታር፣ በዮርዳኖስና በተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው መኖራቸውን ገልጿል።

በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና የሆነው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ሲሆን፣ ከአምናው የሚያዚያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36.6 በመቶ መድረሱን ገልጾ፣ በተለይም ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ይበልጥ አሳሳቢ ነው ብሏል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ በርካታ ዕርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም፣ በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት ጥረቱ በቂ ውጤት ሳያመጣ መቅረቱም አክሏል፡፡

በቀጣይ የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይትና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዥን በተገቢው ሁኔታ እንዲካሄድ፣ በእነዚህ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ መንዛዛት እንዳይኖር በግዥ ሥርዓቱ ላይ አስፈላጊው ማስተካከያ ይወሰዳል ሲል ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአንዳንድ አስመጪዎች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በተደረገ ውል በዱቤ አማካይነት እንደ ዘይት፣ ስንዴና ስኳር ያሉ መሠረታዊ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው ብሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች