Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ክልል ታስረው የነበሩ 59 የምርት ገበያ ሠራተኞች ተለቀቁ

በኦሮሚያ ክልል ታስረው የነበሩ 59 የምርት ገበያ ሠራተኞች ተለቀቁ

ቀን:

የታሸጉ የምርት ገበያው ቅንርጫፎች አልተከፈቱም

በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይል ታስረው የነበሩ 59 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሠራተኞች ከእስር ቢለቀቁም፣ የታሸጉት የምርት ገበያው ቅርንጫፎች ግን እስካሁን አልተከፈቱም፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሰባት የምርት ገበያ ቅርንጫፎችን በማሸግ የስድስቱ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ከሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ታስረው ከቆዩ በኋላ፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋስ መለቀቃቸውን ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡

እንደ ምርት ገበያው መረጃ ከሆነ 59ኙ ሠራተኞች ከእስር የተለቀቁት መታወቂያ፣ የቤት ካርታና የመሳሰሉትን ዋስትና በማቅረብ ነው፡፡ ሠራተኞቹ በእስር የቆዩት ለዘጠኝ ቀናት ሲሆን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ስማችን አይጠቀስ ያሉ ከእስር የተለቀቁ ሠራተኞች ስለታሰሩበትና በቆይታቸው ያጋጠማቸውን ሁኔታ በተመለከተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሥራ ገበታ ላይ እንዳሉ ‹ትፈለጋላችሁ› ተብለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ነው የታሰሩት፡፡ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ለምን እንደታሰሩ ሲያቀርቡ ለነበረው ጥያቄ የያዙዋቸው ፖሊሶችም ሆኑ አዛዦቻቸው ምንም የሚያወቁት ነገር አለመኖሩን፣ ነገር ግን  ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ መያዛቸውን እንደገለጹላቸው ነው የተናገሩት፡፡

ከስድስቱም የምርት ገበያው ቅርንጫፎች በተመሳሳይ ሰዓት የተያዙት ሠራተኞች፣ ከዘጠኝ ቀናት በእስር ያሳለፉት በየከተሞቹ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹የምንጠየቅበት ጉዳይ ካለ ይህ ሊገለጽልን ይገባል፤›› በማለት ሲጠይቁ እንደነበር የገለጹት እነዚሁ ሠራተኞች፣ ‹‹በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት መቅረብ አለብን›› በማለት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ‹‹እናንተ የአደራ እስረኞች ስለሆናችሁ ፍርድ ቤት ልናቀርባችሁ አንችልም›› መባላቸውን አስረድተዋል፡፡

በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ ትፈለጋላችሁ ተብለው  ከመታሰራቸው ውጪ ፖሊስ ቃል እንኳን እንዳልተቀበላቸው የሚገልጹት ሠራተኞቹ፣ በዘጠነኛው ቀናት ግን ትዕዛዙን ሰጠ የተባለው የበላይ አካል ይለቀቁ ብሏል ተብሎ ዋስ እየጠሩ መውጣታቸውን  ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ሁኔታ መደናገጣቸውን የሚገልጹት ሠራተኞቹ የታሰሩበትን ምክንያት ሳያውቁ በፖሊስ ጣቢያ የቆዩባቸው ቀናት ሲጨምሩ ግን፣ ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ፍርድ ቤት አቤት ለማለት በተዘጋጁበት ወቅት መለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በእስር ቆይታቸው አንዳንዶች ስልክ የማግኘት ዕድል ስለነበራቸው፣ ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት ያሉበትን ሁኔታ ሲያሳውቁ እንደነበሩም የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የታሰሩበትን ምክንያት ካለማወቃቸው በስተቀር በነበሩባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች የገጠማቸው ችግር እንዳልነበረም ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ሆኖም ለእስር ያበቃቸውን ምክንያት ሳያውቁ ለዘጠኝ ያህል ቀናት መቆየት ከባድ እንደነበርና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው በጣም ሲያሳስባቸው እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአዳማና ራቅ ባሉ ከተሞች የታሰሩ ሠራተኞች ደግሞ ዓቃቢያነ ሕግ እንደ ጎበኟቸውና እንዳነጋገሯቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም የዓቃቢያነ ሕግ ስለታሰሩበት ምክንያት ይመለከታቸዋል የተባሉ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችን ጠይቀው፣ ምክንያቱን ለማወቅ ሲቸገሩ መታዘባቸውንም ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሠራተኞቹ ሲታሰሩ ሰባቱም የምርት ገበያው ቅርንጫፎች የታሸጉ ሲሆን፣ እስካሁን ተከፍተው አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም፡፡ ቅርንጫፎቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ አሸገ ለተባለው አካል ጥያቄ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጭምር ያሉባቸው የምርት ገበያው መጋዘኖች ታሽገው በመቆየታቸው፣ ከዚህ በኋላ በመጋዘን ውስጥ ያሉ ምርቶችን ሳይበላሹ ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡

በየቅርንጫፎቹ ለውጭ ገበያ ጭምር ምርቶችን ያስገቡ አምራችና ላኪዎች፣ ምርቱ የሚበላሽባቸው ከሆነ መሸጥም ሆነ መግዛት፣ እንዲሁም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ስለማይችሉ ኪሳራው እንዲከፈላቸው መንግሥትን እንጠይቃን እያሉ ነው፡፡ ከሠራተኞቹ ከእስር መፈታት በኋላ በተለይ አንዳንድ ላኪዎች በመጋዘን ያሉ ምርቶቻቸውን በተመለከተ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ባልተለመደ ሁኔታ በበላይ አካል ትዕዛዝ ታስረው ነበር የተባሉት እነዚህን ሠራተኞች ለማስፈታት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ለሌሎች ይመለከታቸዋል ለተባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ሠራተኞቹ ከእሱ ዕውቅና ውጪ ታስረው ለቀናት መቆየታቸውን በማስታወሱ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው መጠየቁ አይዘነጋም፡፡

ሠራተኞቹ የተፈቱት በቀረበው አቤቱታ መሠረት ግፊት ተደርጎ ይሁን አይሁን ማወቅ ባይቻልም፣ ምርት ገበያው ሠራተኞቹ ቅዳሜ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈትተው ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸው እንዳስደሰተው አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የታሸጉበትን ቅርንጫፎች መልሶ አገልግሎት ለማስጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሏል፡፡ ታስረው የነበሩት ሠራተኞች እንዲያርፉ የተደረገ ሲሆን፣ ታሽገው የቆዩት መጋዘኖች ውስጥ ያሉ ምርቶችን ቆጠራ በማካሄድ፣ እንዲሁም ተያያዥ ሥራዎች ከተከናወኑ በኋላ ሠራተኞችን ወደ ሥራ በመመለስ አገልግሎቱን ለማስጀመር ማቀዱ ተሰምቷል፡፡

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ታሽገውበት የቆዩት ሰባቱ ቅርንጫፎች የነቀምት፣ የጅማ፣ የጊምቢ፣ የበደሌ፣ የመቱ፣ የአዳማና የቡሌ ሆራ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቅርንጫፎች ለግብይት ከተዘጋጁ ምርቶች መካከል ቡና፣ ሰሊጥና የመሳሰሉ ምርቶች እንደሚገኝ ታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...