Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዩክሬንን ‹‹አቻ የአውሮፓ ማኅበረሰብ›› ማድረግ ይቻል ይሆን?

ዩክሬንን ‹‹አቻ የአውሮፓ ማኅበረሰብ›› ማድረግ ይቻል ይሆን?

ቀን:

ምዕራባውያኑና ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የውክልና ጦርነታቸውን ለመጀመራቸው አንዱ  ምክንያት ዩክሬን የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ለመሆን ዳር ዳር ማለቷ ነበር፡፡

ምንም እንኳ እ.ኤ.አ. በ2014 በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት ተደርጎ የዩክሬን ክፍለ ግዛት የነበረችው ክሬሚያ ወደ ሩሲያ ብትቀላቀልም፣ ለአሁኑ ጦርነት ዋና መንስዔው፣ ሩሲያ በዙሪያዋ ያሉ አገሮች አውሮፓውያኑና አሜሪካ ጦራቸውን ካጣመሩበት ኔቶ  አባል ሆነው ለደኅንነቷ ሥጋት እንዳይሆኑ ማስጠንቀቋና ዩክሬንም ለዚህ ፈጣን ምላሽ አለመስጠቷ ነው፡፡

ዩክሬን የኔቶ አባል አገር ለመሆን የነበራትን ጥያቄ መተዋን የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ቢያሳውቁም፣ ከሩሲያ ወታደራዊ ዕርምጃ አላመለጡም፡፡ ምዕራባውያኑም ጦርነቱን አስታከው ለዩክሬን የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በሩሲያ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡

ማዕቀቡ ደግሞ ሩሲያን ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያኑንም እየጎዳና የኑሮ ውድነት እያስከተለ ነው፡፡ ደሃ አገሮችን ደግሞ የጎላ ችግር ውስጥ ከቷል፡፡

ጦርነቱ ከዩክሬን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰደዱ፣ ሕንፃዎች፣ ፋብሪካዎችና የጦር መንደሮች እንዲወድሙም አድርጓል፡፡ በሺዎች ለሚቆጠሩት ሞትም ምክንያት ሆኗል፡፡

ቱርክ ጦርነቱ በንግግር ይፈታ ዘንድ የውይይት መድረክ ብታመቻችም ጦርነቱ ሊቆም አልቻለም፡፡

ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ እስከመጨረሻው ራሳቸውን ለመከላከል በቆረጡበትና ምዕራባውያኑ እጅ እንዲያውሷቸው በሚለማመኑበት በዚህ ወቅት፣ ዩክሬንን የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ለማድረግ አሥር ዓመታት እንደሚወስድ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ማክሮን የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በስትራስበርግ በነበረው ስብሰባ ላይ ተገኝተው፣ ‹‹ዩክሬንን የአውሮፓ ኅብረት አባል ለማድረግ አሥር ዓመታት ይወስዳል፡፡ በመሆኑም ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ከአውሮፓ ኅብረት ጎን ለጎን የሚሠራ አቻ የአውሮፓ ማኅበረሰብ  ሆና እንድትታይ፤›› ሲሉ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

‹‹አቻ የአውሮፓ ማኅበረሰብ›› ሌሎች የኅብረቱ አባል መሆን ለሚፈልጉ አገሮችም በር ይከፍታል፣ የአውሮፓ የደኅንነት ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡም ያስችላል ብለዋል፡፡

ዩክሬን የአውሮፓ አባል አገር ለመሆን ይፋዊ ደብዳቤ ለኅብረቱ ያቀረበችው በየካቲት 2014 ዓ.ም. ከሩሲያ ጋር ጦርነት በገባች በአራተኛው ቀን ነው፡፡

ጥያቄዋ ዕውን እንዲሆን ደግሞ በርካታ ዓመታትን የሚፈጅ የአሠራር ሥርዓት አለ፡፡ ማክሮን እንደሚሉትም፣ የኅብረቱ አባል አገር ለመሆን የተቀመጡ መሥፈርቶች ካልተቀነሱና የአውሮፓን አንድነት ለማስቀጠል  ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዳግም ማሰብ ካልተቻለ ዩክሬንንም ሆነ ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን የአካባቢው አገሮች የኅብረቱ አባል ማድረግ አይቻልም፣ ረዥም ዓመታት ይወስዳል፡፡

እንደ ዩክሬንና እንግሊዝ ያሉ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ አገሮችን የአውሮፓ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ሲሉም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የዩክሬንን ማመልከቻ ለማፋጠንም ሆነ በአውሮፓ ውስጥ ያሉና ተመሳሳይ እሴት ያላቸው ሕዝቦችን ወደ ኅብረቱ በአፋጣኝ ለማምጣት በአስቸኳይ ‹‹አቻ የአውሮፓ ማኅበረሰብ›› መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአውሮፓ ኮሚሽንም ዩክሬን የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን ያስገባችውን የመጀመርያ ማመልከቻ አስመልክቶ የመጀመርያ አስተያየቱን በሰኔ 2014 ዓ.ም. የሚያስታውቅ ሲሆን፣ የኬቭ ባለሥልጣናትም ሁለተኛውን የአውሮፓ አባልነት ጥያቄ ማመልከቻ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

‹‹የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን አገሮች በርካታ ዓመታትን በድርድር ያሳልፋሉ፤››  የሚሉት ማክሮን፣ በዚህ ፈንታ ሞልዶቪያ፣ ጆርጂያ፣ ስዊድንና ፊላንድን ጨምሮ ዴሞክራቲክ ሥርዓት ያላቸው የአካባቢው አገሮች የሚካተቱበት የፖለቲካ ማኅበረሰብ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ለመሆን፣ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ጥንካሬ መገለጫ የሆኑ ጠንካራ ሕጎችን ጨምሮ የተለያዩ መሥፈርቶችን ማሟላት ይጠበቃል፡፡

ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ግን በልዩ አሠራር አሁኑኑ ዩክሬን የኅብረቱ አባል እንድትሆን እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡

ማክሮን ለዳግም ፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ በኋላ የመጀመርያ በሆነው የውጭ ጉብኝታቸው ከጀርመን መራሔ መንግሥት ሾልትዝ ጋር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ጦርነት  ምላሽ ለመስጠት መክረዋል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት መተዳደርያ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ፣ ሌሎች የአካባቢው አገሮችን የኅብረቱ አባል ለማድረግ ወይም ከኅብረቱ ጎን ለጎን የአውሮፓ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሥራት ይገባል በሚለው ሐሳባቸው ላይ በቀጣይ የኅብረቱ ስብሰባ እንደሚደረግ ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

የማክሮን ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ዩክሬን ከአውሮፓ ኅብረት ወይም ይፈጠር ተብሎ ሐሳብ ከተሰነዘረበት አቻ የአውሮፓ ማኅበረሰብ ትቀላቀል ይሆን?

 (ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...