Tuesday, April 16, 2024

የድጎማ ፖለቲካ በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በታኅሳስ ወር ላይ መንግሥት የነዳጅ ድጎማን በሒደት ለማንሳት ማሰቡን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩ ወራት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎች በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ላይ ሲደረግም ታይቷል፡፡ ቅዳሜ ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ይኸው ቀጥሎ 31.74 ብር በሊትር የነበረው ቤንዚን በአማካይ የአምስት ብር ጭማሪ በማሳየት 36.87 ብር በሊትር እንዲሸጥ መንግሥት ወስኗል፡፡ ይህ ጭማሪ የዓለም የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ ያስከተለው ነው ቢባልም፣ ነገር ግን መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ከላዩ ላይ የማንሳት ፍላጎቱን ለማሳካት የተደረገ ዕርምጃ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

በሚያዝያ ወር ብቻ ለነዳጅ ከ12.8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን የሚገልጸው መንግሥት፣ በ2014 ዓ.ም. በአሥር ወራት ውስጥ ለዘርፉ 73.5 ቢሊዮን ዶላር መደጎሙን ሲናገርም ተደምጧል፡፡ ይህን ሁሉ የነዳጅ ድጎማ ወጪ በመቀነስ ዘርፉ በዓለም ገበያ እንዲመራ በማድረግ ገንዘቡን ለሌሎች ልማቶች እንደሚያውል፣ እንዲሁም የነዳጅ ኮንትሮባንድ ንግድን ለመቅረፍ ማቀዱን የሚናገረው መንግሥት የነዳጅ ድጎማው ይበቃኛል እያለ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ አገሪቱ አሁን ባለችበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ላይ ተጨማሪ ተፅዕኖ ያመጣል ብለው የፈሩ ወገኖች፣ የነዳጅ ድጎማው እንዲቀንስና የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር መደረጉን አጥብቀው እየተቹት ነው፡፡ ዜጎች በኑሮ ውድነትና በዋጋ ንረት በሚፈተኑበት በዚህ ወቅት ድጎማን ማንሳት የነዳጅ ገበያ አለመረጋጋት ከመፍጠር ተጨማሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ያስከትላል የሚለው ፍራቻ ብዙኃኑን ማኅበረሰብ ማሳሰቡ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች በሚንፀባረቁ ሐሳቦች ይሰማል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ከመነገሩ በፊት ‹‹የነዳጅ ጭማሪና ድጎማ›› በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ቀጠሮ ለእሑድ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ይዞ የነበረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ አጋጣሚው በመገጣጠሙ፣ ጠንከር ያሉ ሐሳቦችን ያንሸራሸረ የውይይት መድረክ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ መድረክ ከማመቻቸት ውጪ የፓርቲው አቋም አይንፀባረቅበትም ብሎ ኢዜማ ባስታወቀው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተጋበዙት ሁለቱ ፓናሊስቶች ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) እና አቶ ሙሼ ሰሙ በዋናነት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ በማቅረብ የሚታወቁ ሲሆን፣ ከነዳጅ ድጎማ በተጓዳኝ ስለድጎማ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረታዊ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡ በዚህ ውይይት መድረክ ላይ የነዳጅ አቅራቢዎች ማኅበር አባላት በዘርፉ ግብይት ላይ ያለውን ውስብስብ ችግር ያስተጋቡ ሲሆን፣ ድጎማ በተለይ የነዳጅ ድጎማ ከግብርና ጀምሮ እስከ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን ተፅዕኖ ተወያዮች አውስተዋል፡፡

ድጎማ በብዙ የዓለም አገሮች አንዱ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማረጋጊያ መንገድ መሆኑን ጥናት አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከመንግሥት ጫና አለመላቀቁንም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ድጎማ ሲደረግ በምን ሁኔታና ለምን ዓይነት የኢኮኖሚ መስኮች መደረግ እንደሚገባው በጥንቃቄ ካለመፈተሹ በተጨማሪም፣ ድጎማ በሚተገበርባቸው ሁኔታዎች ላይ የምዝበራና የሙስና ችግሮች እንደሚንፀባረቁ አስረድተዋል፡፡ ከድጎማ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ በመነሳትና የነዳጅ ድጎማን ማሳያ በማድረግ፣ የድጎማ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ሊተገበር የሚችልባቸውን ውጤታማ አማራጮች ጥናት አቅራቢ ፓናሊስቶቹ ምልከታቸውን አቅርበዋል፡፡ በነሱ ሐሳብ ላይ ከተወያዮች ሐሳብ የተሰጠ ሲሆን፣ ለተሰጡ ሐሳቦችም የተለያዩ ማብራሪያዎች ቀርበዋል፡፡

የፓናሊስቶቹ ምልከታ

ድጎማ እንደ ስትራቴጂክ ማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፖሊሲ መሣሪያ (Subsidy as Strategic Macro Economic Stabilizer Policy Instrument in Ethiopia) በሚል ርዕስ የውይይት ሐሳብ ያቀረቡት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የድጎማ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ምንነትን በማብራራት ነው ሐሳባቸውን የጀመሩት፡፡ በተለይ የገበያ ክፍተት ወይም ጉድለት ሲኖር፣ እንዲሁም ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ በሀብት ወይ በገቢ ረገድ ኢፍትሐዊ ክፍፍል ካለ ያንን ለማረም መንግሥት ከሚወስዳቸው አማራጮች አንዱ ድጎማ ነው ሲሉ የድጎማ ጥቅል ምንነትን ተርጉመውታል፡፡

ድጎማ በኢኮኖሚ ውስጥ ከኢኮኖሚና ከገበያ ፍትሐዊነት ጋር የተያያዘ ማንነት አለውም ብለዋል፡፡ ታክስ መቀነስ፣ ኮታ፣ ራሽን፣ ታሪፍ ሳይቀሩ የድጎማ መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ድጎማ በካሽ በቀጥታ በሚሰጥ ገንዘብ ወይም በተዘዋዋሪ በሚሰጥ ጥቅማ ጥቅም ሊተገበርም ይችላል በማለት፣ በኢትዮጵያ ከነዳጅ ድጎማ ጋር የተያያዙ ሐሳቦችን አነሳስተዋል፡፡

ሁለት ዓይነት የዋጋ ግሽበት እንዳለ የጠቀሱት ደምስ (ዶ/ር)፣ አንዱ የፍላጎት መጨመር የሚያመጣው (Demand Push Inflation) የዋጋ ግሽበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የነዳጅ ዘይት ምርቶች ግን በኢትዮጵያ ከሁለተኛው ግሽበት ዓይነት፣ ማለትም የወጪ ግፊት (Cost Push Inflation) የዋጋ ግሽበት ከሚያስከትሉ ምርቶች ውስጥ ይጠቀሳል ብለዋል፡፡ ነዳጅ ዘይት ከውጭ በውድ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የሚገባ ብቻ ሳይሆን፣ በርዕሱ ላይ የሚታይ ጥቂት ጭማሪ በትንሹ ከ15 ባላነሱ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ ላይ ተፅዕኖው የሚታይ በመሆኑም ነው በማለት የነዳጅ ዘይት ምርት ዋጋ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የተፅዕኖ ክብደት አስረድተዋል፡፡ ነዳጅ የማይነካው የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደሌለ ያስረዱት ተመራማሪው ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች ነዳጅን የሚደጉሙት ወደው አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለ ድጎማ የነዳጅ ምርት ማቅረብ ይቻላል የሚል እምነት እንደሌላቸው የተናገሩት ደምስ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ምን ያህል ድጎማውን በመቀነስ ዋጋው እንዲጨምር ማድረግ አለበት? የሚለው ጉዳይ ላይ ግን በጥልቅ መታሰብ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ድጎማ  በነዳጅም ሆነ በሌላው ሸቀጥ ላይ በማናቸውም ጊዜ እንደ አንድ የፖሊሲ መሣሪያነት ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚል አቋም እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹የዛሬ ሃያ ዓመት ከውጭ ወደ አገር ቤት ስገባ የገጠር ልማት ፖሊሲን በተመለከተ ድጎማ ይደረግ ብዬ ታግያለሁ፡፡ ነገር ግን የጊዜው መሪዎች ድጎማን በግብርናው አታስቡት ብለው መለሱልን፡፡ ለእነ ዓለም ባንክና ለምዕራባውያኑ የስትራክቸራል አጀስትመንት ፖሊሲ ለመገዛት ቃል የገባው መንግሥት ግብርናውን አልደጉምም ሲል ቢቆይም፣ ነገር ግን በእኛ ግፊት ሐሳቡን ቀይሯል፡፡ ገንዘብ የለኝም፣ ድጎማ አይታሰብም ያለው መንግሥት ሰኔ ሲመጣና በጀት ሲያወጣ ግን ለግብርናው በምግብ ዋስትና በኩል አንድ ቢሊዮን ብር እደጉማለሁ አለ፡፡

ድጎማ በተጠናና ውጤታማ በሆነ መንገድ መደረግ አለበት ብዬ ስሞግት ነበር፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር በጊዜው ማለት የግብርናው ዘርፍ ሩብ በጀት ማለት ነበር ቀላል አልነበረም፡፡ ድጎማን ለምንና እንዴት መደረግ አለብት? የሚለውን ብዙ አጥንቻለሁ፡፡ ድጎማ በተመረጡና ስትራቴጂካዊ በሆኑ ምርቶች ላይ መደረግ አለበት እላለሁ፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች ገንዘብ የለንም ይላሉ፡፡ ነገር ግን በተለያየ መንገድ የሚባክነው ገንዘብስ? በግሌ ለምሳሌ የቤቶች ግንባታ ለሚባለው ፕሮጀክት መንግሥት ኢንቨስት ማድረጉን ብዙም አልቃወምም፡፡ ዘርፉ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ይደጎማል፡፡ ነገር ግን በበውጤቱ እንዳየነው ውጤት አልባ ነው ዘርፉ፡፡ በግሌ ዘርፉ ከመንግሥት ውጭ መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ድጎማን በሚመለከትም ዕይታችን መስተካከል እንዳለበት ነው የሚገባኝ፤›› ብለዋል፡፡

ነዳጅ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባ ምርት መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም ላይ ያለው ዋጋ በአንድ ዓመት ብቻ ከ40 ወደ 140 ዶላር በበርሜል መድረሱን፣ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ሳቢያ የዓለም ነዳጅ አቅርቦት በግማሽ መቀነሱ እየተነገረ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ካለብን የዶላር እጥረት ጋር ተዳምሮ ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ጋር አብረው መሄድ የሚችሉ ስትራቴጂክ የፖሊሲ መሣሪያዎችን መተግበር አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ያለንበትን አስቸጋሪ ጊዜ በአግባቡ መወጣት ካለብን ኢኮኖሚው ላይ ጠንካራ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በዘርፉ ሚናውን የጠበቀ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ኢኮኖሚያችንን ለቀቅ እናድርገው፡፡ ብዙ ችግር ውስጥ እየገባ ነው፡፡ መንግሥት ሁሉንም ነገር እኔ ነኝ የማደርገው፣ እኔ ነኝ የማስገባው እያለ ሁሉንም መያዙ አግባብ አይደለም፡፡ ይህን ስል ግን በግሉ ዘርፍም ጤናማ ያልሆኑ አሠራሮችና ተዋንያን እንዳሉ መናገር እፈልጋለሁ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ከድጎማ ጋር በተያያዘ መረሳት የሌለበት ጉዳይ ለማንና ለምንድነው የሚደጎመው የሚለው መሆኑን የሚናገሩት ደምስ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለክልሎች የሚደረገው ድጎማ ለምሳሌ እጅግ ብዙ ነው፡፡ በራሳቸው የሚሰበስቡትና ለራሳቸው የሚያፈሱትን በጀትን ሳናውቅ ነው ፌዴራል መንግሥቱ የሚደጉማቸው፡፡ የኢትዮጵያ በጀት ከ500 እስከ 600 ቢሊዮን ብር እየሄደ ነው እንላለን፡፡ ነገር ግን ለክልሎች የሚደጎመውን እንዘለዋለን፡፡ የኢትዮጵያ በጀት ወደ ትሪሊዮን ብሮች እየገሰገሰ ነው፡፡ በዚያው ልክ ግን ይህን ወጪ የሚመጥን ልማትና ዕድገት እያየን ነው ወይ የሚለው መጠናት አለበት፡፡ ክልሎች በራሳቸው የሚያመነጩትና ለራሳቸው የሚመድቡት በጀትም በግልጽ አይታወቅም፡፡ ይህ ካልታወቀ አላግባብ የሚደረገውም ሆነ ተገቢው የክልሎች ድጎማችን ሊታወቅ አይችልም፡፡ በድጎማ ረገድ በጣም ወሳኝና መደጎም አለባቸው በሚባሉ አካባቢዎች እጅግ ከፍተኛ ሙሰኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የሚስፋፋባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ተቋምና አሠራር ተበጅቶላቸው እየተሠሩ ነው ቢባልም ሙስናና ብልሹ አሠራር በሰፊው ይታይባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡  

ሁለተኛው የውይይት ሐሳብ አቅራቢ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ‹‹በቀዳሚነት በተለያየ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነት ውስጥ የምንኖር ሰዎች ተሰባስበን ስለአገራዊ ጉዳዮች በጋራ ለማውራት ዕድሉ በመፈጠሩ ደስ ብሎኛል፤›› ሲሉ ነው የመድረኩን አስፈላጊነት በመግለጽ ሐሳባቸውን ያቀረቡት፡፡

‹‹ድጎማ (ፍላጎት)፣ አቅርቦት በሚባሉ ሁለት ተመጋጋቢ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎች ሊደረግ ይችላል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ፋብሪካዎችንና ኢንዱስትሪዎችን ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ወይም በቅናሽ ማሽኖችና ማምረቻዎችን እንዲያስገቡ በማድረግ የአቅርቦት ድጎማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን በማድረግ የሸቀጦችን ገበያ ማረጋጋት ይቻላል፡፡ ሌላኛው የድጎማ መንገድ ደግሞ ፍላጎት መፍጠር ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በቀጥታ ለሕዝቡ ገንዘብ በመስጠት መፍጠር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ የፋይናንስ ቀውሱ በተፈጠረበት እ.ኤ.አ.  በ2007 እና 2008 አካባቢ ለሕዝቡ የድጎማ ገንዘብ ሲከፈል ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ደግሞ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሕዝቡን የመግዛት አቅም ለመፍጠር አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ አገሮች ሕዝባቸውን ደጉመዋል፤›› ሲሉ ነው ሐሳባቸውን የጀመሩት፡፡

‹‹በሌላ መንገድ ይህን ብናየው ደግሞ ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃትና ምርታማነትን ለመጨመር፣  እንዲሁም የመግዛት አቅምን ለመፍጠር ሲባል በቀጥታ ገንዘብ በመስጠት የሚደረግ ድጎማ እንዳለ ሁሉ በተዘዋዋሪ የሚደረጉ ድጎማዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ ተዘዋዋሪ ድጎማዎች ደግሞ መብራት፣ ውኃ፣ ስልክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዋጋ በመቀነስም ድጎማ ማድረግ ይቻላል በማለት አስቀምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ድጎማን በተመለከተ በዓለም ላይ የቀረ ወይም ተቀባይነት የሌለው የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ብዙ የዓለም አገሮች ግን ከድጎማ ተላቀው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ መንግሥት የነዳጅ ፍለጋን፣ ማውጣትንና ማቅረብን በተመለከተ ዓምና 5.9 ትሪሊዮን ዶላር ድጎማ አድርጓል፡፡ ድጎማው የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ ለማግኘት የተደረገ ጭምርም ነበር፡፡ ለምሳሌ በሱዳን አሜሪካኖች ብዙ ደጉመዋል፡፡ ይህን ያደረጉት ደግሞ የዓለም ነዳጅ አቅርቦትን ለመጨመር ነው፡፡ የነፃ ገበያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ዋና አራማጅ ነን የሚሉት አሜሪካኖቹ ሌሎችን ቢከለክሉም ራሳቸው ግን የድጎማ ዕርምጃዎችን ሲተገብሩ ነው የምናገኘው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የነዳጅ ድጎማ በኢትዮጵያ የሚያሳስበው ለምንድነው?›› ሲሉ የጠየቁት አቶ ሙሼ፣ ‹‹መንግሥት ለነዳጅ የማመጣውን የድጎማ ገንዘብ ከየት አገኛለሁ?›› ይላል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ግን ማምጫው መንገድ ያንተ ነው ነዳጅ ባለመደጎሙ ከሚደርስብኝ የዋጋ ተፅዕኖ መዳን አለብኝ እንደሚል፣ የደሃ አገር መንግሥት መሆን ሁሌም ከባድ ነውና ይህን እንዴት እናስታርቅ የሚለው ማሳሰቡ እንደማይቀር፣ መንግሥት በዋናነት ገንዘብ እያተመ ድጎማ ወደ ማድረግ ከገባ ከታሰበው በተቃራኒ ድጎማው የዋጋ ግሽበት እንደሚያስከትል ይረዳል ተብሎ እንደሚታመን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ሊትር ነዳጅ 15 ኪሎ ሜትር የሚነዳ መኪናን እንዲሁም በአንድ ሊትር ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሄድ መኪናን፣ እኩል መደጎም ትንሽ የድጎማ ፍትሐዊነትን እንደሚነካ፣ ድጎማው መደረግ የሚችለው አንድ አገራዊ ፕሮጀክትን በማጠፍ ወይም ከሌላ ቦታ በጀት በማዘዋወር ነው ከተባለም እንዲሁ የድጎማው ጉዳይ ማከራከሩ እንደማይቀር፣ ድጎማ በእነዚህ ሁሉ የተነሳ እንዴት? ለማን? በምን ሁኔታ ይካሄድ? የሚል መልስ የሚፈልግ ጉዳይ ነው ሲሉም መሠረታዊ ያሉትን ጉዳይ ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን በከተሞች ያለው አኗኗር ደግሞ ከተማ መካከል ቤት ገንብቶና ገዝቶ መኖር የሚያስችል ስላልሆነ፣ ብዙ ባለመካከለኛ ገቢ በከተማ ዳርቻዎች ኑሮውን መሥርቶ በትንሽ የነዳጅ ፍጆታ በሚሠሩ መኪኖች እየተመላለሱ መኖርን የሚጠይቅ እየሆነ ነው፡፡ በገጠር አካባቢ ያሉ ከተሞች ደግሞ ከዲዝል ኃይል ማመንጫዎች መብራት እያገኙ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነዳጅ ድጎማው ጉዳይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚነካ ነው፡፡ ነዳጅን እየደጎምኩ እዚህ ደርሻለሁ ከእንግዲህ አልችልም የሚለው መንግሥት ለዚህ ሁሉ መፍትሔ ከማፈላለግ በተጨማሪ፣ እስካሁን ዘርፉን የመራበትን መንገድ በተመለከተ ግልጽ መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ከግዥ ጀምሮ እስከ ማከፋፈል የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ ለሙስና የተጋለጠ ነው፡፡ ከጨረታ ጀምሮ እንዴት እንደሚገዛ፣ የመቼ ግዥ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ጥራት ያለው ነዳጅ እንደሚገዛና በምን መንገድ እንደሚቀርብ ብዙ ግልጽ ሊሆኑ የሚገባቸው መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሦስት ወራት ክምችት አላት ይባላል፡፡ ነገር ግን ይህን ሳትነካ በአናቱ እየገዛች ታቅርብ ወይስ ከቆጠበችው ትቅዳ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በምን ያህል ዋጋ እንደተገዛም ሆነ ከብሬንት ይሁን ከኒውዮርክ ገበያ መገዛቱ አይታወቅም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢመደበኛ በሆኑ መረጃዎች በድርድር ነዳጁ እንደሚገዛ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ በስቶክ ማርኬት ተወዳድራ ገበያ ወጥታ እንደማትገዛም ይነገራል፡፡ በጥራት ደረጃም ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጠውና ከፍተኛ የሊድ ዝቃጭ ያለው ለጤና ጎጂ የሆነ ነዳጅ እንደምትገዛ ይሰማል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የአገሪቱን የነዳጅ ግብይት ገጽታ ለማሳየት አያስችልም የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ መንግሥት ነዳጅ ገዝቼበታለሁ ብሎ የሚነግረን ዋጋ እውነተኛ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ነዳጅ ሥርጭቱ ከወደብ እስከ ማደያ ድረስ የሚታወቅ ነው እየተባለ ለጎረቤት አገሮች በኮንትሮባንድ ይቸበቸባል መባሉም ያጠራጥራል፡፡ አንድ ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገር እንዴት ሊሄድ ይችላል? አንድና ሁለት ቦቴ በመሄዱ ለገዥው እንዴት ያዋጣዋል? እኛ ላይስ ምን ጉዳት ያመጣል? በመንገድ ትራንስፖርት በነዳጅ ፍጆታ እየተጓጓዘ ነዳጅ በኮንትሮባንድ መቸብቸቡ ሊያዋጣ ይችላል ብሎ ማመን ያጠራጥራል፡፡ ነዳጅ በኮንትሮባንድ ስለሚቸበቸብ ነው ድጎማውን የማነሳው መንግሥት ማለቱ አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም፤›› ሲሉም ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

አቶ ሙሼ ሲቀጥሉም የአራት አፍሪካ አገሮችን የነዳጅ ዋጋ ዓይቻለሁ ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዶላር 0.618፣ ግብፅ 0.582፣ ሱዳን 1.26፣ ሩዋንዳ 1.37፣ እንዲሁም ኡጋንዳ 1.48 ዶላር ነው የሚቸረቸረው ብለዋል፡፡ ‹‹ከእነዚህ አገሮች መካከል በዘርፉ ከፍተኛ ምርት ካላት ከግብፅ ውጪ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ርካሽ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ጎረቤታችን ነዳጅ እያላት ከእኛ ውድ በሆነ ዋጋ ነው የሚቀርበው፡፡ ነገር ግን ማወቅ ያለብን አገሮቹን በዜጎች የመግዛት አቅም ስንመዝናቸው፣ ከኢትዮጵያ በእጅጉ የሚበልጥ ገቢ ነው ያላቸው፡፡ ድጎማ የሚያስፈልገው ኢኮኖሚ አልያዙም፡፡ ከጎረቤት ኬንያ፣ ኡጋንዳ ወይም ሱዳን ጋር ሲነፃፀር የእኛ አገር አንድ ሠራተኛ ደመወዝ በእጥፍ ያነሰ ገቢ ነው ያለው፡፡ የነዳጅ ዋጋን ከእነሱ ዋጋ ጋር ተወዳዳሪ ይሁን ስንል፣ የእኛ አገር ዜጋን የመግዛት አቅም ታሳቢ ካላደረግን አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም የነዳጅ ድርጅት ድጎማን በማስቀረት ላይ የሚሰጣቸውን አመክንዮዎች ለመቀበል እቸገራለሁ፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ድጎማ ለማድረግ አስገዳጅ ሁኔታዎች አሉ ወይ ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹በደንብ አሉ›› ሲሉም አቶ ሙሼ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የማኅበረሰቡ የመግዛት ወይ የገቢ ሁኔታ ከጎረቤትም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡፡ የነዳጅ ምርት ሲደጎም የቆየው ዋጋው በዓለም ገበያ በሚቀንስበት ወቅት ለመጠባበቂያ ተብሎ በሚጠራቀም ገንዘብ ነው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በዓለም ገበያ ካሳየው ጭማሪ ውጪ ለረዥም ጊዜ ነዳጅ በርካሽ ሲሸጥ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ የተጠራቀመው የመታደጊያ ድጎማ ገንዘብ ዛሬ የት ነው ያለው? የነዳጅ ድርጅቱ የሚያቀርበው መረጃ ተዓማኒነት ከዓለም አቀፉ ሁኔታ ጋር መጣጣም መቻሉ ሊፈተሸ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ድጎማን በተመለከተ ግን ድጎማ አግላይ ካልሆነ በስተቀር ለአገሮች ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ግብርናው ለምሳሌ 83 በመቶው አርሶ አደራችን ከነዳጅ ድጎማ ምን ይጠቀማል ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ አብዛኛው የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የከተማው ነዋሪ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የነዳጅ ድርጅቱ በአንድ ወር 12 ቢሊዮን ብር ነዳጅ ደጎምኩ ይላል፡፡ ይህን ቀንሰን ግብርናውን ብንደጉምበት ግን ለአገሪቱ የበለጠ ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን፤›› በማለትም ሐሳብ አቅራቢው አቶ ሙሼ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡ 

የተወያዮች ሐሳብ

ከነዳጅ አቅራቢዎች ማኅበር መምጣታቸውን የጠቀሱት ኤፍሬም የተባሉ ተወያይ፣ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚቸበቸበውን የኮንትሮባንድ ነዳጅ ምርትና ለነዳጅ ቸርቻሪዎች የሚፈቀደው ትርፍ ምጣኔ ማነስ መሠረታዊ የዘርፉ ችግር መሆኑን አውስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰባት አገሮችን የምትጎራበትና በሁሉም ጎረቤት አገሮች የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ከኢትዮጵያ በእጅጉ የሚበልጥ መሆኑን የገለጹት ተናጋሪው፣ ከ10 እስከ 15 በመቶው የኢትዮጵያ ነዳጅ ወደ እነዚህ አገሮች በኮንትሮባንድ እንደሚሰደድ ተናግረዋል፡፡ በነዳጅ ችርቻሮ ዘርፍ ለተሰማሩ የሚፈቀደው የትርፍ መጠንም እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ የሚያሠራ የትርፍ መጠን ለነጋዴዎች በመፍቀድ በዘርፉ የተስፋፋውን ሕገወጥነት መቅረፍ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

አሁን በሕጋዊ መንገድ ነዳጅ አቅርቦ ከሚያገኘው ይልቅ በኮንትሮባንድ ሸቅጦ ብዙ ማትረፍን ነጋዴው ስለሚያስበልጥ ሕጋዊ የነዳጅ ሥርጭቱ በእጅጉ መዛባቱን ነው አቶ ኤፍሬም የተናገሩት፡፡ በአዲስ አበባና በመሀል ከተሞች ሕግ ማስከበሩ ጠንከር ስለሚል ነዳጅ ማደያዎች በተገቢው ዋጋ ቢሸጡም ትንሽ ከከተሞች ወጣ ሲባል ግን ከፍተኛ ትርፍ እየተጠየቀ በሕገወጥ ዋጋ ነው ነዳጅ የሚቸረቸረው በማለትም የዘርፉን ከባድ አደጋ አስረድተዋል፡፡ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ከመነገድ ይልቅ በሕገወጥ መንገድ መሥራት በዘርፉ አዋጪ ሆኖ በመገኘቱ ነዳጅ አቅራቢዎች በመንግሥት ዋጋ መሸጥን አይፈልጉም ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ ይህ ችግር የሚቀረፈው ለአቅራቢዎች የትርፍ ምጣኔን በመጨመር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው ተወያይ በበኩላቸው መንግሥት ጫማ ጠበበን ለሚሉ ዜጎች እግራችሁን አሳጥሩትና ተጫሙ የሚል መፍትሔ ይሰጣል በማለት ተችተዋል፡፡ በመንግሥት አካባቢ ስትራቴጂካዊ መፍትሔዎችን ማፍለቅም ሆነ የረዥም ጊዜ ፖሊሲዎችን መቅረፅ ከባድ ችግር መሆኑን ተናጋሪው አውስተዋል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እጅግ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ወደ ጎን ተብለው ቀስ ብሎ ለሚደረስባቸው ዘርፎች እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ሲሉም መንግሥትን ወቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርብርብና ውስብስብ ችግር ባለባት አገር ውስጥ የነዳጅ ድጎማን ካላነሳሁ ሞቼ እገኛለሁ የሚል መንግሥት መታየቱ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር የአመራር ችግር እንደገጠማት ዋና ማሳያ መሆኑንም አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡

ድጎማው በቀጥታ ለሕዝቡም ሆነ ወሳኝ ለሆኑ ለአገር ለሚፈለጉ ዘርፎች አልደረሰም ሲሉ የነዳጅን ድጎማ ሥርዓት ከተቹ አስተያየት ሰጪዎች መካከል፣ ከቡታጅራ አካባቢ መጣሁ ያሉና አርሶ አደር መሆናቸውን የጠቀሱ ተናጋሪ ይገኙበታል፡፡ ‹‹በሊትር 70 እና 80 ብር እየገዛን ነው በውኃ መሳቢያ ሞተር በመጠቀም ቲማቲምና ሽንኩርት የመሳሰሉ እርሻዎችን የምንሠራው፤›› ያሉት ተናጋሪው፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ ግብርናውንም እንደሚጎዳው ነው ያመለከቱት፡፡ ‹‹እስከ ዛሬ እየተደጎመ ለእኛ ለአርሶ አደሮች ግን የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አላየንም፤›› ያሉት ተናጋሪው፣ አሁን መንግሥት ድጎማውን ቢያስቀረውም ሆነ ባያስቀረው ችግራቸው እንደማይቀረፍ ነው ያስረዱት፡፡

‹‹የነዳጅ ድጎማን ለማንሳት ወቅቱ ነው?›› ወይ ሲሉ የጠየቁ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ ይህ ሁኔታ ከኢኮኖሚ አልፎ የፖለቲካውን አለመረጋጋት የበለጠ እንዳያባብስ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፖለቲካው ኢኮኖሚውን መጫን እንደማይኖርበትና ዓለም አቀፉን የገበያ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ኢኮኖሚው ቢመራ ውጤታማ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡

መንግሥት በድጎማ ማንሳትና ማድረግ ላይ ሕዝብን ቢያወያይ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን የገለጹ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ ድጎማ ለማንሳት ምን ምቹ ሁኔታ እንዳለ ከማወቅ በተጨማሪ በዋጋ ግሽበት ላይ ዕርምጃው የሚኖረውን ተፅዕኖም ለመረዳት ጠቃሚ መንገድ ነው ሲሉ ሕዝብ ማማከርን በበጎ ጎን አውስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚጠቀሰውና ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከድጎማ መነሳት ጋር ተያይዞ መታየት እንደሚኖርበት ባለሙያ የሆኑ አስተያየት ሰጪ አሳስበዋል፡፡ የኢነርጂ ምንጮችን ለማስፋትና የነዳጅ ጥገኝነትን ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች የት ደረሱ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ባቡሩ ምን ያህል የአገሪቱን ሎጂስቲክስ አቀለለ? ተገኘ የተባለው ነዳጅ ጋዝ የት ደረሰ? እንዲሁም ነዳጅን በኤታኖል ምርት ለመተካት የተጀመሩ ሙከራዎች የት ገቡ? ሲሉም በአገር ደረጃ ሊነሱ ይገባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች ጠቃቅሰዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ፣ ‹‹እኔ የከተማ ነዋሪ ነኝ ድጎማም አያስፈልገኝም፣ ለጤናዬ ጥሩ በመሆኑ ዎክ ማድረግ እችላለሁና ሌሎች ዘርፎች ይደጎሙልን፤›› በማለት ሐሳቡን ያንፀባረቀው አስተያየት ሰጪ የገጠመው ምላሽ አስቂኝ ነበር፡፡ አማራጩ ‹‹ዳቦ በሙዝ ብንበላስ?›› ከሚለው የተለየ አይደለም የሚል ምላሽ ነበር የተሰጠው፡፡ በዚህ መድረክ ከፓናሊስቶቹም ሆነ ከተወያዮቹ ኢኮኖሚው በስትራቴጂና በዕቅድ መመራት አለበት የሚል ሐሳብ የተንፀባረቀ ሲሆን፣ የድጎማ አማራጭም በተመረጠና በተጠና ሁኔታ መተግበር ይችላል የሚለው ጎልቶ ተወስቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -