የ5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ በቅድመ ሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በኔትወርኩ ካሉት አጠቃላይ ደንበኞች 110 ሺሕ የሚሆኑት አገልግሎቱን መጠቀም የሚችሉበት ቀፎ ባለቤት እንደሆኑ አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ደንበኞቹ የአምስተኛው ትውልድ የኔትወርክ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚገለገሉባቸው መገልገያዎች (ዲቫይስ) ኔትወርኩን ለመቀበል የሚያስችሉ መሆን እንዳለበት ያስታወቁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ከዚያም በሻገር የደንበኝነት ሲም ካርዳቸው 5ጂን መጠቀም የሚያስችል መሆን እንዳለበት አገግሎት ይፋ በተደረገበት መርሐ ግብር ወቅት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የ5 ጂ ዞን ባላቸው እንደ ወዳጅነትና አንድነት ፓርኮች፣ ሸራተን ሆቴል አካባቢ፣ ቸርችል ጎዳናና የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢዎች አገልግሎቱን እንዳስጀመረ የተነገረ ሲሆን፣ አገልግሎቱም የቅድመ ገበያ ሙከራ እንደሆነ ግቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል በነበረው መርሐ ግብር ላይ ተጠቅሷል፡፡
በ12 ወራት ውስጥ 150 የሚሆኑ የ5ጂ ሳይቶች በአዲስ አበባና ከአዲስ ውጭ እንደሚኖሩት ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ይህም ለዘመናዊነትና ተዝናኖት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂውን በመጠቀም አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ችግርን ለመቅረፍ የሚለውን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የ5ጂ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለውን የፍሪክዌንሲ ምደባ ለኢትዮ ቴሌኮም መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የቻይናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው ሁዋዌ አገልግሎቱን የማቅረቡን ሥራ እንዳከናወነ ታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የ4ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ከተዋወቀ ከአሥር ዓመት በኋላ ቴክኖሎጂው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ያስታወቁት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ቴክኖሎጂ ዘግይቶ ተግባራዊ በተደረገ ቁጥር አዲስ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የሚኖረው ዓቅም ከመጠቀም የሚያግድ ይሆናል ብለዋል፡፡
‹‹ይህ ዘመን ግን ሊያልፈን አይገባም›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የ5 ጂ አገልግሎት በጤናው፣ በግብርናውም ሆነ በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ወደ ገንዘብና አገልግሎት ሊቀይሩት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ የኔትወርክና አገልግሎት ማስፋፊያዎችንና የኔትወርክ ተደራሽነትን ተግባራዊ ሲያደረግ እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም የደንበኞቹን ቁጥር በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 69 ከመቶ አድጎ 64 ሚሊዮን ደንበኞችን እንዳፈራ ታውቋል፡፡