በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የዓሳ ማርባት ሥራ መፈቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የዓሳ ሀብት ልማት ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ምክክር ያደረገ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ያላት ቢሆንም በተገቢው መንገድ ያልተያዘና ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድብን ሳይጨምር በተደረጉ ጥናቶች ኢትዮጵያ በዓመት 94,500 ቶን ዓሳ የማምረት አቅም እንዳላት፣ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አስቻለው ላቀው (ዶ/ር) ገልጸዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት እየተመረተ የሚገኘው በዓመት ከ60 ሺሕ ቶን ያልበለጠ ዓሳ መሆኑን አክለዋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 200 ያህል የዓሳ ዝርያዎች መኖራቸውንና 40 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ ዝርያዎች አሁን ባለው ገበያ ተፈላጊ ናቸው ብለዋል። ነገር ግን ዓመታዊ ምርቱ በቂ ባለመሆኑ የአንድ ሰው ዓመታዊ የዓሳ ፍጆታ ግማሽ ኪሎ ግራም በታች መሆኑን ጠቁመው፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአንድ ሰው ዓመታዊ የዓሳ ፍጆታ እስከ 12 ኪሎ ግራም መድረሱን ተናግረዋል። በመሆኑም ያሉትን ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ የውኃ ሀብቶች በመጠቀም የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ አክለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የዓሳ ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ሁሴን አበጋዝ በበኩላቸው የዓሳ ሀብት ልማት በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም ሕገወጥ ማርባት የዓሳ ሀብቱ እንዲመናመን እያደረገ ነው ብለዋል። በአብዛኛው ማልማት ሥራው በሐይቆች ላይ የሚደረግ መሆኑን፣ ይህም የዓሳ ዝርያዎቹ እንዲጠፉና በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ሳይሆኑ ለገበያ እንዲቀርቡ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በተለይ የዓሳ ማስገር ፈቃድ ባለመስጠቱ ምክንያት በርካታ አስጋሪዎች በማኅበር እንዳይታቀፉና ቁጥራቸውም አለመታወቁን አስረድተዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ሰው ሠራሽ ግድቦች ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ 27 በመቶ የሚሆን ድርሻ እንዳላቸው ገልጸው፣ ይህንንም ማሳደግ እንደሚገባ አክለዋል። ለዚህም የግድቦች አሠራር ለዓሳ ምርት የተመቸ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ነገር ግን በተለይም ከአሥር ዓመታት ወዲህ እየተገነቡ ያሉ ግድቦች በአብዛኛው ለዓሳ ምርት ያልተመቹና ዓሳ ማምረትን ግምት ውስጥ ያላስገቡ መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት እስከ 40 በመቶ የሚሆን የዓሳ ምርት እንደሚጠፋ አቶ ሁሴን አብራርተዋል።
አሁን በመገንባት ላይ ከሚገኙ ግድቦች ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዓሳ ምርት የተመቸ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ለትልልቅ ኢንቨስተሮች ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። አሁን ባለበት ሁኔታ ግን በአነስተኛ ደረጃ የዓሳ ማርባት ሥራ መፈቀዱን ገልጸዋል።