Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየቀድሞ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ (1933 - 2014)

የቀድሞ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ (1933 – 2014)

ቀን:

‹‹የኔ ምኞትና ፍላጎት እኩልነት፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀና የበለፀገች አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ ዓላማ በመንደር ልጅነት፣ በጎሳና በዘር የሚለወጥ አይደለም፡፡ በዚያ አብዮት ወቅት የተጋረጠብንን ሴራና ተንኮል በመቋቋም የገባሁትን ቃል ኪዳንና መሃላ ጠብቄ በንፁህ ህሊናና ቅንነት አገሬንና ሕዝቤን አገልግያለሁ፡፡ ደርግ በወሰዳቸው በጎ ዕርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ፣ በማወቅ በድፍረት፣ ባለማወቅ በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ ሙሉ ኃላፊነትን በመውሰድ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡››

የመጀመርያው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ፣ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚል ርዕስ ሐምሌ 2007 ዓ.ም. በአሜሪካ አገር በሎስ አንጀለስ ከተማ ባሳተሙት መጽሐፍ ሽፋን ላይ ደስታቸውንና ፀፀታቸውን የገለጹበት ነበር፡፡ በዚህ አቋማቸውም በርካታ ኢትዮጵያውያን አድናቆታቸውን ከመቸር አልተቆጠቡም፡፡

በ1966 ዓ.ም. በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሥልጣኑን የጨበጠው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግን ከጠነሰሰው የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት አንዱ የክብር ዘበኛ የጦር ክፍል ነበር፡፡

- Advertisement -

ይህን የጦር ክፍል ከወከሉት መኰንኖች አንዱ ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ናቸው፡፡ ኮሎኔሉ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ‹‹የኢትዮጵያ ትቅደም›› ዓላማን ለማስረዳት በሰሜን ክፍላተ ሀገር የተጓዘውን ቡድን መርተዋል፡፡

የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በቆየባቸው 13 ዓመታት (1967 – 1979) ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ከሠሩባቸው ቦታዎች መካከል የደርጉ ረዳት ዋና ጸሐፊነት ትልቁ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን (ኢሠፓ) እንዲያዋልድ በ1972 ዓ.ም. በተመሠረተው የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሆነውም መሥራታቸው ይታወቃል፡፡

በ1977 ዓ.ም. ኢሠፓ ከተመሠረተ በኋላ የፓርቲው የፖለቲካ ቢሮ አባል ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ደርግን በ1980 ዓ.ም. የተካው የኢሕዲሪ መንግሥት የመጀመርያው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል፡፡

ከዘውዳዊው ሥርዓት ማክተም አምስት ዓመት በኋላ ለአገር ባለውለታዎች ስለሚሰጥ ሜዳይና ኒሻን የሚመለከት የሜዳይና ኒሻን ኮሚሽን ለመጀመርያ ጊዜ ሲቋቋም የመሩት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ነበሩ፡፡

ከትግርኛና አማርኛ፣ ጉራጊኛም ባሻገር የእንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጣሊያንኛ ተናጋሪው ኮሎኔል፣ ሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ከምዕራብ አውሮፓና ስካንዲኒቪያን አገሮች ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል፣ ስለ አብዮቱ ለማስረዳትና የኢኮኖሚ ትብብር እንዲጠናከር የተላከውን ቡድን የመሩት እሳቸው መሆናቸው በገጸ ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡

ከሦስት አሠርታት በላይ አገርን በተለያዩ መስኮች ያገለገሉት ፍሥሐ ደስታ፣ በዓቢይነት ከሚጠቀስላቸው ተግባራት አንዱ በአብዮቱ የመጀመርያ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተፈጥሮ የነበረው መንገዳገድና ከተከተለው ኪሳራ ለመታደግ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ያከናወኑት ይጠቀሳል፡፡

ኮሎኔሉ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ከዳሰሷቸው አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ነው፡፡ ‹‹የ1966ቱ ሕዝባዊ አመፅ ሲፈነዳ የፖለቲካው ወላፈን አየር መንገዱ ውስጥም ገብቶ ያምሰውና ያተራምሰው ገባ፤›› ያሉት ጸሐፊው፣ ‹‹ተራማጅ ነን የሚሉ የደርግ አባላት፣ ሚኒስትሮችና ካድሬዎች አየር መንገዱ ከቦይንግ [አሜሪካ] ወደ ኤሮፍሎት [ሶቪየት ኅብረት] እንዲሰጥ›› ያደርጉት የነበረው ጥረት የከሸፈው ‹‹ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አየር መንገዱ ወደ ውድቀት ማምራቱን ሲገነዘቡ ሥር ነቀል ዕርምጃ በመውሰድ መፍትሔ እንዲያስገኙ ለፍሥሐ ደስታ፣ ለአማኑኤል ዐምደሚካኤልና የሱፍ አህመድ ጥብቅ መመርያ በመስጠታቸው እንደሆነ በታሪካቸው ላይ ሰፍሯል፡፡

ከአገር ወጥተው በተለያዩ አገሮች በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩት የአየር መንገዱ የቀድሞ ኃላፊዎች ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ፣ ካፒቴን መሐመድ አህመድ፣ አሰፋ አምባዬና ወልደ ገብርኤል ፀሐይ በሦስቱ ከፍተኛ ሹማምንት አማካይነት እንዲመጡ በማድረግ አየር መንገዱ ከውድቀት መታደጋቸው ተጽፏል፡፡

በሌላ በኩልም ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ በማኅበራዊ ሕይወታቸው በዘመነ ዘውድ የክብር ዘበኛን በመወከል የጦር ኃይሎች ስፖርት ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል የነበሩ ሲሆን፣ ለጦር ኃይሉ በብሔራዊ ፌዴሬሽን ይሰጥ የነበረውን የእግር ኳስ ዳኝነት ኮርስን ተምረዋል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ከመጨበጡ አንድ ወር በፊት በመንግሥት ትዕዛዝ በጡረታ የተገለሉት ምክትል ፕሬዚዳንት ፍሥሐ፣ ከሁለት አሠርታት በላይ ታስረው እስራቸውን ፈጽመው መውጣታቸው ተገልጿል፡፡ 

ከአባታቸው ከብላታ ደስታ ወልደ ማርያም እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ኅርይተ ሥላሴ ትኩእ ሚያዝያ 13 ቀን 1933 ዓ.ም. በትግራይ ጠቅላይ ግዛት ዓድዋ ከተማ የተወለዱት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ እስከ 7ኛ ክፍል በዓድዋ ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት፣ 8ኛ ክፍልን በዓዲግራት አግአዚ ትምህርት ቤት ፈጽመዋል፡፡

በ1947 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው፣ በ1951 ዓ.ም. የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ/ሐረር የጦር አካዴሚ የ3ተኛ ኮርስ አባል በመሆን ለሦስት ዓመታት ከሠለጠኑ በኋላ በ1995 ዓ.ም. በምክትል መቶ አለቃ ማዕረግና ዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

በ1962 ዓ.ም. በአሜሪካ በሚሰጠው ከፍተኛ የእግረኛ መኮንንኖች ኮርስ ለመሳተፍ ተወዳድረው በከፍተኛ ነጥብ በማለፍ፣ ጆርጂያ በሚገኘው የፎርት ቤኒንግ ትምህርት ቤት ተካፍለው በጥሩ ውጤት በማለፍ ዲፕሎምና የምስጋና ወረቀት ማግኘታቸውን፣ እንደተመለሱም የ3ኛ ብርጌድ የትምህርትና ዘመቻ መኰንን በመሆን በማገልገል ላይ እንዳሉ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በማታ ጀምረውት የነበረውን የሕግ ትምህርት በቀን ተማሪነት ተከታትለዋል፡፡

የየካቲት ሕዝባዊ ዓመፅ እንደፈነዳ በሌሉበት ስብሰባ የ3ኛ ብርጌድ ተወካይ በመሆን ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. በደርግ አባልነት የተመረጡት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ፣ በትዳር ዓለምም በ1962 ዓ.ም. ወ/ሮ ሐረገወይን ገብረ ሥላሴን አግብተው ዘለዓለም ፍሥሐ ደስታን ያፈሩ ሲሆን፣ ከዚሁ ብቸኛ ልጃቸውም አንድ ወንድ የልጅ ልጅ አግኝተዋል፡፡

ባደረባቸው ሕመም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት  ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በ81 ዓመት ዕድሜያቸው አርፈው ከሁለት ቀን በኋላ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓት ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

በክብር ዘብና በማርሽ ባንድ በታጀበው ሥርዓተ ቀብር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ እንዲሁም የቀድሞው የኢሕዲሪ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንትና ጄኔራል መኰንኖችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡

የኢሕዲሪ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ኮሎኔል መንግሥት ኃይለ ማርያም በስደት ከሚኖሩበት ዚምባቡዌ (ሐራሬ) የሐዘን መልዕክት በተወካያቸው ወ/ሮ ገነት አየለ በኩል ልከዋል፡፡

‹‹ጓድ ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ከአብዮቱ ዘመን ዋዜማ ጀምሮ እስከ ኢሠፓአኮ/ ኢሠፓ ምሥረታና ኢሕዲሪ መንግሥት መቋቋም ድረስ በአገራችን እና በፓርቲያችን የተሰጠውን ኃላፊነት በሙሉ ትጋትና ቁርጠኝነት የተወጣ ጓድ ነበር፤›› ያሉት ኮሎኔል መንግሥቱ፣ ‹‹ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በሚያቀርባቸው ሐሳቦች መንግሥትና ፓርቲያችን በእጅጉ ተጠቃሚ ነበሩ። ጓድ ፍሥሐ አገሩን እና ሕዝቡን ከልብ የሚወድ፣ ከሌብነት የፀዳ፣ ከብሔርና ጎሳ አስተሳሰብ ፍፁም ነፃ የሆነ ታማኝ የሕዝብ አገልጋይ ነበር፤›› ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል፡፡

የሕይወት ታሪካቸውን በዓውደ ምሕረቱ ላይ ያነበቡት የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዓለሙ አበበ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዘመኑ አጠራር ጓድ ፍሥሐ ደስታ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ደርግንና ያሁኑን ለውጥ እንዲያስተያዩ  ጭምር እየተጠየቁ ሰፊ እና ግልጽ ማብራሪያ በመስጠት ይታወቁ እንደነበር አውስተዋል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ፣ ‹‹ሁሉም ነገር በኃይል አይፈታም፣ ስህተት ባይደገም ደስ ይለኛል፣ ይሄ ትውልድ ዕዳ ከፋይ መሆን የለበትም፣ በጎሳ/በዘር መደራጀት ከማርክሲዝም የመጣ በሽታ ነው፣ መገዳደሉ በእኛ ይብቃ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ ዕርቅ መደረግ አለበት፣ ሥልጣንና ሀብት ኃላፊና ጠፊ ነው፣ ሕዝብ ግን ዘለዓለማዊ ነው፣ ኃይል አያዋጣም፣ በውይይት ይፈታ በማለት ምክራቸውን ሲለግሡ መቆየታቸውም ይወሳል፡፡

የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ፍሥሐ ደስታ ላበረከቱት ከፍ ያለ ተግባር፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ‹‹የዳግማዊ ምኒልክ የአገልግሎት ሜዳይ›› እንዲሁም በዘመነ ደርግ ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ታላቁ የክብር ኮከብ ኒሻን አንደኛ ደረጃ›› እና ‹‹የየካቲት 66 አብዮት ኒሻን አንደኛ ደረጃ›› ተሸልመዋል፡፡

ነፍስ ኄር ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በመጽሐፋቸው ማጠቃለያ ገጽ ላይ የታዋቂውን ገጣሚ ከበደ ሚካኤል ግጥምን አንጓ አስፍረዋል፡፡ እንዲህም ይነበባል፡-

ሀብታም ይደኸያል፤ ሐኪምም ይሞታል፣

ጎበዝ ይሸነፋል፣ ብልህ ይሳሳታል፣

የበራውም ጠፍቶ የሠሩት ይፈርሳል፣

የቆመውም ወድቆ የሳቀ ያለቅሳል፡፡

ጌጥም ሆነ ጥበብ ውበትም ሆነ ክብርም፣

ያማረበት ነገር ማስቀየሙ አይቀርም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...