Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአብን የፓርቲውን አመራር በአቋራጭ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረትን እንደማይታገስ አስታወቀ

አብን የፓርቲውን አመራር በአቋራጭ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረትን እንደማይታገስ አስታወቀ

ቀን:

ፓርቲው ለአቶ ክርስቲያን ታደለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ አሥር አመራሮቹን አግዷል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በፓርቲው በ13 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ላይ ከመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እስከ ማገድ የደረሰ ዕርምጃ ከወሰደ በኋላ፣ የፓርቲውን አመራር በአቋራጭ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረትን እንደማይታገስ አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ዘላቂ ድርጅታዊ ማሻሻያ /ሪፎርም/ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጾ፣ አመራሩን የመቆጣጠር ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አባላት እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራርና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን፣ በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ አሥር አመራሮቹን ድግሞ ከአባልነት አግዷል፡፡ ፓርቲው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በፓርቲው መዋቅር ውስጥ እየታዩ ያሉ ‹‹የዲሲፕሊንና ድርጅታዊ መርህ ጥሰቶችን›› በተመለከተ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ‹‹የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በተለያዩ አፍራሽ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ›› በመሆኑ እንደሆነ ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የወጣው የፓርቲው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ አቶ ክርስቲያን ‹‹አፍራሽ›› የተባሉትን ድርጊቶች አስመልክቶ ሁለት ጊዜ የቃል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ያብራራው የአብን መግለጫ፣ ይሁንና የሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው በጋራ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ተገዥ አለመሆናቸውን በመግለጫው ላይ ተካቷል፡፡

መግለጫው አክሎም፣ ‹‹ንቅናቄውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አንጃዎች ጋር ኅብረት በመፍጠርና፣ ንቅናቄው የሐሳብና የተግባር አንድነት እንዳይኖረው በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ስለተገኙ፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፤›› ብሏል፡፡

የአብን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው በተወሰነበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ስለመሳተፋቸው የተባለ ነገር ባይኖርም፣ በፌስ ቡክ ገጻቸው በጻፉት መልዕክት ውሳኔውን ተቃውመዋል፡፡ የፓርቲውን መግለጫ ‹‹በአብን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስም የወጣው›› ያሉት አቶ ክርስቲያን፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይህ ዓይነቱን ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ክርስቲያን፣ ስለ ጉዳዩ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ይህ የውስጠ ፓርቲ ጉዳይ ስለሆነ ለጋዜጣ የሚቀርብ አይደለም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አክለውም ተቃውሟቸውን በፌስቡክ ገጽ ያስቀመጡት የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ተደራሽ የሚሆኑበት የተሻለ አማራጭ ስለሌለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአብን የታገዱት አሥር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ የፓርቲው መካከለኛ አመራሮች፣ ውሳኔው የተላለፈባቸው ‹‹በድርጅት አመራርነት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው በሚከተሉት ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ ተሳታፊና መሪ ሆነው ተገኝተዋል፤›› በሚል ነው፡፡ ከታገዱት አባላት መካካል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጌታሁን ሳህሌ (ዶ/ር)፣ አቶ አንተነህ ስለሺ፣ አቶ እሱባለው ሙላት ዘለቀና አቶ ንጉሥ ይልቃል ይገኙበታል፡፡

ሕገ ወጥ ተብለው ከተጠቀሱት አብዛኛው ድርጊቶች የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ የተመለከቱ ናቸው፡፡ በፓርቲው የተሰጣቸው ውክልና ሳይኖር ‹‹የጠቅላላ ጉባኤ ተወካይ ነን በማለት ሕገወጥ ቅስቀሳና አድማ መምራትና በንቅናቄው ውስጥ አንጃ መፍጠር፣ በማደናገርና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ፊርማ ማሰባሰብ፣ ሕገወጥ የጠቅላላ ጉባዔ ውክልና ይገባኛል መጠየቅና ድርጅታዊ ሥልጣን በእጅ አዙር ለመንጠቅ መሞከር›› የታገዱት አመራሮች ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ናቸው፡፡ እንዲሁም ‹‹ጉባዔ ጠርተን ሪፎርም እናካሂዳለን በማለት ከድርጅቱ ዕውቅና ውጪ ገንዘብ ማሰባሰብ›› እና ‹‹በንቅናቄው ላይ መሠረተ ቢስ ክሶች በመሰንዘርና በከፍተኛ አመራሩ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት›› የሚሉትም ለእገዳቸው ምክንያት እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

እነዚህ የፓርቲው አመራሮች ከመታገዳቸውም ባሻገር፣ የፈጸሟቸው ዝርዝር ጥሰቶችን በተመለከቱ ማስረጃዎች መሠረት የዲሲፕሊን ክስ እንዲመሠረትባቸው ለንቅናቄው የዲሲፕሊን ኮሚቴ መመራቱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም አቶ ሀብታሙ በላይነህና አቶ በቀለ ምንባለ የተባሉት የፓርቲው ቋሚ ኮሚቴዎችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ አባላት ደግሞ ‹‹አብረው ውሳኔ ያሳለፉበትን አጀንዳ በእጅ አዙር ለመቀልበስ አባላትን በማሳደም፣ ለንቅናቄው የስብሰባና ሥነ ሥርዓታዊ ሕጎች፣ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ባለመገዛትና የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ረግጦ በመውጣት፤›› የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

በመግለጫው መጨረሻ ላይም ፓርቲው፣ ‹‹የፓርቲውን አመራር በአቋራጭ በመቆጣጠር ለሕዝባችን በጎ ባልሆነ የኃይል አሠላለፍ ውስጥ ለማስገባት የሚደረግ ማናቸውንም ጥረት ፓርቲያችን የማይታገስ መሆኑን እያስገነዘብን፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመሰል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ የምታደርጉ አንዳንድ የፓርቲው አባላት ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

ይህንን የአብን መግለጫን ተከትሎ በፓርቲው የወረዳና የከተማ መዋቅሮች ስም የተከፈቱ የፌስ ቡክ ገጾች የፓርቲው ውሳኔን ያልተወያዩበትና የማይቀበሉበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በእነዚህ ገጾች ላይ ስለሰፈረው አቋምና የፓርቲው ትክክለኛ የመዋቅር ገጾች ስለመሆናቸው ጥያቄ የቀረበላቸው የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሐመድ፣ ‹‹ኖ ኮሜንት›› በማለት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አብን፣ የጉባዔ ተሳታፊዎች የአመራር ለውጥ (ሪፎርም) የማድረግን ጉዳይ በአጀንዳነት አፅድቆ ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ለአብን ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ በርካታ የጉባዔው አባላት የአመራር ለውጡ በጉባዔው ቀን እንዲካሄድ ቢጠይቁም በአጀንዳነት ተይዞ ስላልነበር በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ጉባዔው በድጋሚ ተጠርቶ እንደሚከናወን መገለጹን ጠቅሷል፡፡

በዚህም መሠረት ምርጫ ቦርድ ፓርቲው በደንቡ መሠረት የሚቀርፃቸውን ሌሎች አጀንዳዎች ጨምሮ፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደገና ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድና ከዚህ ቀደም ዕልባት ላላገኘው ‹‹የአመራር ሪፎርም ወይም ለውጥ ማድረግ›› ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...