የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እያሠለጠናቸው ላሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች 20 ቢሊዮን ብር ብድር ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
ባንኩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ብድር ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ከግንቦት 1 እስከ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚቆይ ሥልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን፣ በሥልጠናውም 34,000 ሠልጣኞች እንደሚሳተፉ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል። ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ሥልጠና በ20 ከተሞችና በ32 ማዕከላት በመላ አገሪቱ ለሦስተኛ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን አክለዋል።
ከዚህ በፊት በተሰጡ ሁለት ሥልጠናዎች በአጠቃላይ 5,100 ሠልጣኞች መሳተፋቸውን፣ ሥልጠናውን አጠናቀው ወደ ሥራ ለመግባት መሥፈርቱን ያሟሉት 1,200 መሆናቸውን ጠቁመው፣ ለእነዚህ ኢንተርፕራይዞች የሚሆን 14 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
በሦስተኛ ዙር እየሠለጠኑ ለሚገኙት ሠልጣኞች ደግሞ በአጠቃላይ 20 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱን የገለጹት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በዚህ ዙር ከሚሠለጥኑት ውስጥ ቢያንስ እስከ 30 በመቶ ያህሉ ወደ ሥራ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ግምት መኖሩን ተናግረዋል።
ሥልጠናው በዋናነት በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና ሜካናይዜሽንና በቱሪዝም ዘርፎች ትኩረት እንደሚያደርግና ኢንተርፕራይዞቹ ስለቢዝነስ አመራር ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድጉበት መሆኑን ገልጸዋል።
ብድሩን ለማግኘት ሥልጠናውን መውሰድ ግዴታ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ተበዳሪዎች ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉና በጊዜው እንዲመልሱ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። ከተበዳሪዎቹ የሚሰበስበው የገንዘብ መጠን ጭማሪ እያሳየ መሆኑንና ባለፈው ዓመት ብቻ የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 26 በመቶ መድረሱን፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተበላሸ ብድር መጠኑን ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ለማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ጠቅሰዋል።
በ2013 ዓ.ም. ብቻ ደግሞ ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ ስምንት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን፣ ከዚህም ውስት 3.6 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተበላሸ ብድር መሆኑን አብራርተዋል።
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከዚህ በፊት ከነበረው የማበደር ሒደት በተለየ መንገድ ተበዳሪዎች ይጠየቁ ከነበረው የ20 በመቶ ማስያዣ በተጨማሪ ተደራጅተው መበደር የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱን አብራርተዋል። ይህም የመመለስ ሒደቱን ከማሻሻል ባለፈ ተበዳሪዎች የሚጠበቅባቸው ማስያዣ ከፍተኛ እንዳይሆንባቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል።