Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሚዲያው ቀንበር አሁንም እንደ ከበደ ነው!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ በወሰነው መሠረት፣ በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 ቀን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚከበርበት ምክንያትም መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ1948 የፀደቀውን ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት በማድረግ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ለማስገንዘብ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት የሰብዓዊ መብቶች አካል ከሆነው ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ከፍተኛ ዝምድና አለው፡፡ ለዚህም ነው በአምባገነኖች መዳፍ ሥር ከሚገኙ እጅግ በጣም ጥቂት አገሮች በስተቀር በበርካታ አገሮች በከፍተኛ ስሜት የሚዘከረው፡፡ እኛ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለምን እናከብራለን? በአገራችን ከምናውቃቸው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ወይም ፖለቲካዊ ሥነ ሥርዓቶች ምን የተለየ ያደርገዋል? ሌሎቹ በዓላት ወይም ሥነ ሥርዓቶች ዓላማቸው ታውቆ በሚመለከታቸው ወገኖች ከልብ ሲከበሩ፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንስ እንዴት ነው የሚታሰበው? በየሆቴሉ ለታይታ በሚደረጉ ዲስኩሮችና ግርግሮች ነው? ወይስ ከልብ ታምኖበት? ሚዲያዎቻችን ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ በአፅንኦት በማስተዋል፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለምን እንደምናከብር ግልጽ መሆን አለበት፡፡

የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲታሰብ በአገር ደረጃ ምን አገኘን? ምን አጣን? የተሟላው የቱ ነው? የተጓደለውስ? እያልን በቅጡ ካልተነጋገርን ችግር አለ፡፡ በሐሳብ መለያየት ብርቅ ባልሆነበት ዓለም ውስጥ በልዩነቶቻችን ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ዘክዝከን ማየት ካቃተን፣ የፕሬስ ነፃነት ቀን ተዘከረ ማለት አይቻልም፡፡ የሚዲያ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከመንግሥትና ከሕዝቡ ጋር በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ በሚታዩ ሥር የሰደዱ ችግሮች ላይ መነጋገር ካልቻሉ ስለፕሬስ ነፃነት መነጋገር ፋይዳ የለውም፡፡ ለፕሬስ ነፃነት ቀን እንኳን አደረሰን ተብሎ መልካም ምኞት ለመለዋወጥም አይመችም፡፡ በአጠቃላይ የፕሬስ ቀን ምን ማለት ነው? ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ስለሚጽፉት ወይም ስለሚዘግቡት ጉዳይ መነጋገር ብቻ ሳይሆን፣ ከፕሬስ ውጤቶች ሕዝቡ የሚያገኘው ምንድነው? መረጃዎች ትክክለኛና ሚዛናዊ ሆነው ይደርሱታል? ጋዜጠኞች ለአንድ ወገን ጥብቅና ቆመው ነው ወይ ለሕዝቡ የሚያቀርቡት ወይስ ሙያዊ ሥነ ምግባር ተላብሰው? የሚተላለፈው መረጃ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ይመስላል? የሚሉት ዋነኞቹ መሆን አለባቸው፡፡

በአገራችን የሚገኙ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ምን ያህል ናቸው? የጋዜጦቻችን የአንድ ወር ኅትመት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ የሚኖር ሕዝብን ማዳረስ ካልተቻለውና የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ሥርጭት ተደራሽነት ውስን ከሆነ፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንን እንዴት ነው የምናከብረው? የዲጂታል ሚዲያው ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን፣ ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ አለመሥራት ምን እያስከተለ ነው? የሚዲያ ነፃነት አለ ሲባልስ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ ነው ወይ? ስለሚዲያ ነፃነት ስንነጋገር ሚዲያው ሊደርስበት ያልቻለውን የአገሪቱን ሕዝብ ከዘነጋን ትልቅ ችግር አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ልዩነታችን ከፍተኛ የሆነ የሐሳብ ሙግት ያስፈልገዋል፡፡ ሌላው ትልቁ ተግዳሮት ሚዲያው ከዘመኑ የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲዘምን ምን መደረግ ይኖርበታል? አዲሲ የሚዲያ ሕግ በባለሙያዎች ተመክሮበት ቢወጣም በአግባቡ እየተሠራበት ነው ወይ? በዚህ ዘመን ጋዜጠኞችን ወይም ሐሳባቸውን በነፃነት ለማስተላለፍ የሚፈልጉ ሰዎች ማሰር ምን የሚሉት ፋሽን ነው? በሕጉ መሠረት ፍርድ ቤት አለማቅረብና ያሉበትን አለማሳወቅ ጤነኝነት ነው ወይ? ያ ሁሉ ቃል የተገባለት የዴሞክራሲ ጭላንጭል የት ገባ?

ለሚዲያ ነፃነት ፈተና ከሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ ሚስጥራዊነትና ተጠያቂነት አለመኖር ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ይዘው አትዩኝ፣ አትናገሩኝ፣ አትጠይቁኝ… የሚሉ እየበዙ በመሆናቸው ችግሩ እየሰፋ ነው፡፡ ይህ ችግር ከመንግሥት ጀምሮ እስከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድረስ በጉልህ የሚታይ ነው፡፡ የሕዝብ የማወቅ መብትን እየተጋፋ መረጃ ከሚከለክል የመንግሥት ሹም አንስቶ፣ በአገሪቱ የሚታየው የሚስጥረኝነትና ተጠያቂ ያለ መሆን ችግር የሚዲያ ነፃነትን እየፈተነ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ከባቢ ውስጥ ለሐሳብ ልዩነት ዕውቅና መስጠት ይቅርና እስከ መፈጠሩም ማወቅ የማይፈልጉ አሉ፡፡ መንግሥት እያንዳንዱን ፖሊሲ ሲቀርፅ የንግግር ነፃነትን ለማክበርና ለማስፋፋት ጥረት ያደርጋል ወይ? ካላደረገስ መፍትሔው ምን ሊሆን ነው? በሕገ መንግሥቱ የሠፈረው አንቀጽ 29 በቀጥታ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19 የተቀዳ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ይህንን ነፃነት የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በተግባር ሲታይ መንግሥት ለሚዲያ ነፃነት መከበር ያበረከተው አስተዋጽኦ ከሚፈለገው ጋር ይመጣጠናል? በጭራሽ፡፡ አሁንም እጅግ በጣም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡

የአገሪቱ ሚዲያ ዕድሜ ከ100 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም፣ የግሉ ሚዲያ ደግሞ በዚህች አገር ውስጥ በይፋ መሥራት ከጀመረ 30 ዓመታት አልሞሉትም፡፡ ይህ ጮርቃ የግል ሚዲያ ለሙያው አሁንም አዲስ ከመሆኑም በላይ፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የሙያ ሥነ ምግባርና የልምድ ጉድለቶች አሉበት፡፡ የሙያ ችግሮችን በተመለከተ በሚፈለገው መጠን ጋዜጠኞችን የሚያፈሩ የትምህርት ተቋማት በሚገባ አለመኖራቸው፣ የጋዜጠኞችን ክህሎት ለማሳደግ የግሉ ሚዲያ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ በመንግሥት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ኢንቨስትመንት መሳብ ባለመቻሉና በመሳሰሉት የሙያ ሥነ ምግባሩም እያደር መዝቀጡ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ የአገሪቱ ሚዲያዎች የሙያ ሥነ ምግባር መመርያም ሆነ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የላቸውም፡፡ በዚህ ላይ መሠረታዊ የሆነ የመዋቅር ችግር አለባቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ ገለልተኝነት እየጠፋ ጽንፈኝነት፣ ከዚያም ባለፈ ወደ ፖለቲካ አቀንቃኝነት (Activism) ውስጥ ተገብቷል፡፡ የጋዜጠኛ ማኅበራት በቅጡ አለመደራጀታቸውና ደካማ መሆናቸው ሌላው የችግሩ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ መጠነ ሰፊ ችግር ላይ መንግሥት ለግሉ ሚዲያ ያለው ዕይታ አሁንም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ፣ ማበረታቻ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ጋዜጦችና መጽሔቶች የኅትመት ዋጋ 85 በመቶ ጨምሮባቸው ህልውናቸው አደጋ ላይ ነው፡፡

በሚዲያ ነፃነት ጉዳይ የሕዝብ ሚና ግልጽ ሆኖ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሕዝብ የንግግር ነፃነት እንዲኖር መጠየቅ አለበት፡፡ ለምን ቢባል ይህንን ነፃነት ከጥቃት መከላከል እንዳለበት መተማመን ሲኖር፣ ሕዝብ የሚስማማውን ብቻ አይደለም መስማት ያለበት፡፡ እንዲያውም የማይፈልገው ሐሳብ ጭምር እንዲደመጥ ማበረታታት አለበት፡፡ የማንፈልገውን ጭምር ካልሰማን የንግግር ነፃነት ውበት የለውም፡፡ የምንጠላውን ወይም የማንስማማበትን ጭምር መስማት የንግግር ነፃነትን መደገፍ ነው፡፡ ለማይስማማን ንግግር ጭምር ጥብቅና መቆም ካቃተን የራሳችን ንግግር ጭምር አደጋ ውስጥ መውደቁን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ እየመረረንም ቢሆን ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ያስከብራል እንጂ አያስነቅፍም፡፡ የሐሳብ ልዩነት በነፃነት ካልተስተናገደ ስለሚዲያ ነፃነት የሚደረግ ዲስኩር ትርጉም ያጣል፡፡ ለዚህም ነው በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም የሚባለው፡፡ በመሆኑም የሚዲያው ሸክም እንዲቃለልና የንግግርና የጽሑፍ መብት ተሟልቶ ሥራ ላይ እንዲውል፣ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚዲያው ቀንበር እንደ ከበደ ነው ያለው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...