Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ድርጅቶች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በዱቤ እንዲያስገቡ ተፈቀደላቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

እየከፋ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለማርገብና ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ለመቀነስ መንግሥት መሠረታዊ ፍጆታዎች በዱቤ ከውጭ እንዲገቡ መፍቀዱን አስታወቀ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ስኳር፣ ዘይትና ስንዴን በዱቤ ወይም ዲፈርድ ሌተር ኦፍ ክሬዲት አሠራርን በመጠቀም ማስገባት ተፈቅዷል፡፡

ፈቃዱ የተሰጠው ለልማት ድርጅቶች ብቻ ሲሆን ባለፈው ወር 43 በመቶ የደረሰውን የምግብ ዋጋ ግሽበት ለማርገብ ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መንግሥት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን አቅርቦት ለመጨመር በማሰብ የፍራንኮ ቫሉታ አሠራርን ከመፍቀድ ባለፈ ያለ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ እንዲገቡ ፍቃድ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የተደረጉት ማስተካከያዎች ዋጋ ግሽበት ከመቀነስ አኳያ ያመጡት ለውጥ እምብዛም ነው፡፡

ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ ከ400 ብር በላይ ጭማሪ በማሳየት ከ1000 ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ አቅርቦቱም አነስተኛ መሆኑን ሸማቾች ያነሳሉ፡፡ በተመሳሳይ የስንዴና ስኳር አቅርቦት አነስተኛ ሲሆን በዋጋቸውም ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስቴር ዓብይ አህመድ የሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እንዲገቡ የፈቀደ ሲሆን፣ ይህንን እንዲያከናውኑ ለጊዜው የተመረጡት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅትና የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንደሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢና ቺፍ ኢኮኖሚስት የሆኑት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ እንደተናገሩት፣ አሠራሩ ለእያንዳንዱ ምርቶች የተለያየ ሲሆን ለስኳር ምርት ዱቤው የሚከፈልበት ጊዜ ሁለት ዓመት ሲሆን ለስንዴና ዘይት በአንድ ዓመት ውስጥ ሊከፈል ይገባል፡፡

ይህን መሰል አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ አገር ውስጥ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር አይገናኝም ብለዋል፡፡ አሠራሩም የሚመራው የአቅርቦት ብድር (ሳፕላይ ክሬዲት) መመርያ ሲሆን አሠራሩ ተግባራዊ እንዲደረግ ብሔራዊ ባንክ አቅጣጫ መስጠቱት ተናግረዋል፡፡

ተግባራዊ የተደረገው የዱቤ ሥርዓት የደገፉት ሰውአለ አባተ (ዶ/ር) ይህን ሒደት በመከተል ዕቃዎች ለማስመጣት ሲሞክሩ የነበሩ አስመጪዎች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ በዱቤ ዕቃ ማስመጣት መፈቀዱ ትክክለኛ ዕርምጃ ነው ያሉት ባለሙያው፣ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ በተመሳሳይ አሠራር ዕቃ ለማስገባት ለሚሹ የግል ድርጅቶች ሊፈቀድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ግብዓት ማስመጣት ባለመቻላቸው መዘጋታቸው ይታወሳል፡፡ ለአብነትም ከ20 በላይ የታሸገ ውኃ ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ተዘግተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የውጭ ንግድ ለአገሪቷ ባለፈው ዘጠኝ ወራት ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ አስገኝቷል፡፡ የተገኘው ገቢ ከታቀደው አኳያ አነስተኛ መሆኑን የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ ይፋ ያደረገ ሲሆን ካጋጠሙ ዓለም አቀፍ ችግሮች አኳያ ከአምናው የተሻለ ገቢ ተገኝቷል ሲል አስታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች