የኢትዮጵያና የቻይና መንግሥታት፣ የቻይና ባለሀብቶች በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት ሊፈራረሙ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ነገ ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በሁለቱ መንግሥታት መካከል ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ስምምነት፣ የቻይና መንግሥት ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚገፋና ኢትዮጵያም ለእነዚህ ባለሀብቶች አማራጮችን እንድታቀርብ የሚያስገድድ ነው፡፡
የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ እንደ ኬብልና ብረት ብረት ምርት እንዲሁም ግብርና ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ ሰሎሞን፣ ኢትዮጵያ ከአገሮች ጋር ‹‹ልዩ የሆነ›› የመግባቢያ ሰነድ ሲፈረም የመጀመሪያው ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ የገባቻቸው እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች ጥቂት ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ከሚገኝባቸው ቀዳሚ አገሮች መካከል ቻይና በመሆኗ በስምምነት የታገዘ የኢንቨስትመንት ሥራ መኖሩ በቻይና በኩል ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
አክለውም፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ተሳትፎ ካላት አገር ጋር እንደዚህ ዓይነት ሰነድ መፈረሙ መዋለ ንዋያቸውን በሰፊው የሚያፈሱ የቻይና ባለሀብቶችን ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይታሰባል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ ከዘህ ቀደም በዕቅድ የተያዘና በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተተ መሆኑን የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ በኢትዮጵያ የቻይና ኤንባሲና በኮሚሽኑ መካከል ተደጋጋሚ ንግግሮች መካሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ከስምምነቱ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቻይና ባለሀብቶች በተለየ ሁኔታ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመሬት ማዘጋጀት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ይሁንና የቻይና ባለሀብቶች ዘንድ የራሳቸውን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመገንባት ልምዱ ስላለ ይኼኛው አማራጭ እንደሚበረታታ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 118 ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ፈቃድ ማግኘታቸውን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት የቻይና ባለሀብቶች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ፍቃድ ካገኙት ባለሀብቶች ውስጥ 65 ያህሉ ማኑፋክቸሪንግ፣ 50 በአገልግሎት፣ ሦስቱ ደግሞ በግብርና ዘርፍ መሰማራታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ የተሳበው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 2.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህ መጠን ካለፈው ዓመት አንፃር በ18.8 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ይሁንና ኮሚሽኑ በዕቅድ ከያዘው 3.6 ቢሊዮን ዶላር በ1.2 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው፡፡