ከዓመታት በፊት በናይሮቢ፣ ኬንያ ተካሂዶ በነበረው የፋሽን ትርዒት የባለ ካሜራውን ቀልብ የገዙት እንስትና ቀንደ መለከት ነፊው ሙዚቀኛ ናቸው፡፡
ፎቶ ቢቢሲ
****
ቱ! በል
ቱፍ – በል! ማሙሽ ቱ!
አለችው እናቱ
እሷው ናት አባቱ
ወንድምና እህቱ
ነፍስና አካላቱ፡፡
ማሙሽ ብቻ – ብቻውን
እያዩ መምጫ – መምጫውን
ያለምንም ከልካይ
ከጐጆው በራፍ ላይ
አፈር አድበልብሎ
ሲቅም እንደቆሎ….
እናት በችኮላ
እንስራዋን አዝላ
ልጄ! … ልጄን! … ብላ
አሳብራ መንገዷን
ዘንግታ ድካሟን
ስትደርስ ከደጃፉ
ሆኖ ስታገኘው አፈር ቅሞ ባፉ
ብድግ አ‘ረገችው
ቱፍ – በል!!! እያለችው፡፡
ጭቃ ባፉ ሞልቶ …
መላ – አካሉ ቦክቶ … ሆኖ ስላየችው፤
መታ አ‘ረገችው
ቱፍ – በል! እያለችው፡፡
እንባውን ስታየው
ቱ – በል! እያለችው
እየዳበሰችው
እያባበለችው
አቅፋ እየሳመችው
አዝላ እያስተኛችው
እሷም እንደማሙሽ ጭቃውን ቃመችው፡፡
- አሰፋ ጉያ ‹‹የከንፈር ወዳጅ››(1984)
******
የስንዴን በቆልት በእርጎ
ጥራጥሬን በቆልት አድርጎ መመገቡ ጤናን ለመጠበቅ ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ በተለይም የጥቁር ሽምብራ በቆልት ለሰውነት ኃይልን ከመለገስ ባሻገር በውስጡ የሚያካብታቸው፤ አያል ቫይታሚኖች የተስተካከለ ጤናን ያጎናጽፋሉ፡፡ ገብስ ባቄላና አተርን የመሳሰሉት ጥራጥሬዎች በበቆልት መልክ ተዘጋጀተው ለምግብነት ሲውሉ ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል እሸት ስንዴን ወቅጦና በውኃ በጥብጦ መጠጣቱም ጤናን ያደራጃል፡፡
ለጋው የስንዴ ጭማቂ አያሌ ሻይታሚኖች አሉት፡፡ በተለይም እርጉዘ ሴት ይህን ጨማቂ አዘውትራ ከተመገበች ጤናማ ቆንጆና ብልህ ልጅ ለመውለድ እንደሚያስችላት ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ስንዴን በቆልት አድርጎ በእርጎ ወይም ከወተት ጋር ደባልቆ መጠጣቱም ሰውነትን እንደሚያጠናክር ጠበብቱ ያስረዳሉ፡፡ ከሌሎች በቆልት ጥራጥሬዎች የስንዴው ብቅል ወደር የለሽ ጠቀሜታ አለው፡፡ እርጅናን የሚከላከለው ቫይታሚን ‹‹ኤ›› በስንዴ ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡
- አባይነህ አበራ ‹‹ዶክተር ለራሴ››
******
በሩ ግን አልተዘጋም
በአንድ መንደር ውስጥ አግብታ ብዙም ሳትቆይ ባሏን በሞት የተነጠቀች አንዲት ሴት ትኖር ነበር፡፡ አጠገቧ ዓይኗን የምታሳርፍባትና የምታጽናናት ብቸኛ ልጅ ነበረቻት፡፡ አንድ ልጇንም በርኅራኄና በፍቅር አሳደገቻት፡፡ ይሁን እንጂ በጥንቃቄ ብታሳድጋትም ልጇ ካደገች በኋላ የበለጠ ወደ ዓለም አዘነበለችና መንደሯን ለቅቃ ወደ ዋናው ከተማ ጥላት ኮበለለች፡፡ የልጅቷ እናት በሐዘን ተሰብራ ልጄ ከዛሬ ነገ ትመለስ ይሆናል ብላ ብትጠብቃትም እሷን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡
የኮበለለችው ልጇ እንድትመለስ ሌትና ቀን እየጸለየች ዓመታት አለፉ፡፡ አንድ ምሽት አንድ የእግር ዱካ ድምፅ ወደ ቤቷ በሚወስደው ጠባብ መተላለፊያ እየተቃረበ ሲመጣና ወደ በሩም ተጠግቶ የበሩን እጀታ እየፈራ እየተባ ሲነካ ሰማች፣ እጀታውም ድምፅ አሰማ፡፡ በእንቅልፍ ሰመመን እንዳለች አንድ ሰው ወደ ውስጥ መዝለቁን እናት ትሰማና ካልጋዋ ተፈናጥራ በመነሳት ወደ በሩ ታመራለች፡፡ የኮበለለችው ልጇ ናት፡፡ ልቧ በደስታ እየዘለለ ልጇን በፍቅር በእቅፏ ውስጥ ወሸቀቻት፡፡ እንደተቃቀፉም፣ ልጇ፣ ‹‹እማዬ፣ በዚህ በእኩለ ሌሊት ለምን በሩን አልቆለፍሺውም?›› ብትላት፣ እናት የልጇን ጸጉር እየደባበሰች፣
‹‹ልጄ ሆይ፣ አንቺ ከኮበለልሽበት ቀን ጀምሮ ምናልባት አንድ ቀን ስትመለሺ ልትቀበልሽ ሁሌ ዝግጁ የሆነች እናት እንዳለሽ እንድታውቂና ሳታመነቺ እንድትገቢ በማሰብ በሩ በቀንም ሆነ በሌሊት ተቆልፎ አያውቅም›› ስትል መለሰችላት፡፡
- ኃይሌ ከበደ ‹‹ምስካይ›› (2004)