ለኢንቨስትመንት በሚቀርቡ መሬቶች ላይ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶችን ይፈታል የተባለ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን፣ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ስትራቴጂው በዋናነት የግብርና ኢንቨስትመንት መሬቶች ለባለሀብቶች በሚቀርቡበት ወቅት መሟላት የሚገባቸውን መሥፈርቶች ያካተተ መሆኑንና በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር እንደታቀደ፣ በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት በተለይም ለኢንቨስትመንት መተላለፍ ያለባቸውና የሌለባቸው መሬቶች የትኞቹ ናቸው የሚሉትን በግልጽ ያስቀመጠ፣ በኅብረተሰቡና በአልሚዎች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። ለግብርና ኢንቨስትመንት መሬቶች ሲሰጡም የሃይማኖት ቦታዎች አለመሆናቸውን ማጣራትና ቅሬታዎች እንዳይፈጠሩ ማድረግ እንደሚገባ በስትራቴጂው ተመላክቷል ብለዋል።
መሬቶቹ የግል ወይም የጋራ ይዞታዎች ሲሆኑ የባለይዞታዎቹን ፈቃደኝነት መሠረት እንዲያደርጉና ግጭት እንዳይፈጥሩ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቅሷል። በተጨማሪም ኢንቨስትመንቱ በአካባቢው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግና የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠበቅ የኢንቨስተሩ ኃላፊነት እንደሚሆንም አቶ ዓለማየሁ አክለዋል። ይህም ዘርፉ በተሻለ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣትና የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትልቅ ሚና እንዲኖረው የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚሆኑ መሬቶችን የመስጠት ኃላፊነት የክልሎች ቢሆንም እንኳን፣ በተለይም የፌዴራል መንግሥት ከሚያስቀምጣቸው መሥፈርቶችና አሠራሮች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በስትራቴጂው መካተቱ ተጠቁሟል፡፡
ይህም በተለይም ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ፣ ወደ መሬት ባንክ መመለስ ያለባቸው መሬቶችም በወቅቱ እንዲመለሱ ለማድረግና በክልሎችና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል የሚኖሩ የአሠራር ልዩነቶችን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ አቶ ዓለማየሁ አክለዋል።
ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚቀርቡ ብድሮችም ተገቢውን ሒደት ጠብቀው እንዲቀርቡ፣ የሀብት ብክነትን ከመከላከል አንፃር እንዲህ ዓይነት ወጥነት ያለው አሠራር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ከእዚህ በፊት የግብርናው ኢንቨስትመንት የሚመራበት ግልጽ ስትራቴጂና አሠራር እንዳልነበረ የገለጹት አቶ ዓለማየሁ፣ ግጭት ውስጥ ሲያስገቡና ልዩነቶችን ሲፈጥሩ የቆዩ ጉዳዮችን ለመፍታት በቀጣዮቹ ወራት ወደ ሥራ የሚገባው ይህ ስትራቴጂ ጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል። የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና በግብርና ዘርፍ የሚገኙ ባለድርሻዎችን በማካተት የተዘጋጀው ስትራቴጂ አንድ ዓመት ተኩል ያህል እንደፈጀ አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል።
ስትራቴጂውን መነሻ በማድረም በቀጣይ ለግብርና ኢንቨስትመንት በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት ሌሎች መመርያዎች እንደሚያዘጋጁም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የግብርና ኢንቨስትመንት አቅም ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ መሬት ስድስት ሺሕ ለሚሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በሊዝ ውል ማስተላለፍ መቻሉን፣ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።