በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል፣ በአፍሪካ ኅብረት ተዘጋጅቶ፣ ኢትዮጵያ የካቲት 2012 ዓ.ም. ያፀደቀችውን የካምፓላ ኮንቬንሽን በአገር ውስጥ ለመተግበር ሚያስችል የማስፈጸሚያ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚመለከተው የካምፓላ ኮንቬንሽን፣ በአገር ውስጥ የሕግ ማዕቀፍ ከተዘጋጀለት በኋላ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎችን በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሥራ ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት፣ በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የመብቶች ጥሰትን አስመልክቶ ባወጡት ሪፖርት መነሻነት የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል፣ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ አራት ዘርፎችን የሚይዙ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ኮሚቴዎቹ የምርመራና ክስ ኮሚቴ፣ የስደተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ኮሚቴ፣ የፆታን መሠረት ያደረግ ጥቃት ኮሚቴና የሀብት ማሰባሰብ ኮሚቴ ናቸው፡፡
የስደተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዎች ጉዳይ ኮሚቴ የአገር ውስጥ ተፈናቃዎችን በተመለከተ ቀጣይ የሆነ የሰብዓዊ ዕርዳታ ያለ ምንም አድልኦ መዳረሱን የማረጋገጥና ለተፈናቃዎቹ ዘላቂ መፍትሔ የማበጀት ኃላፊነት እንዳለበት የገለጹት የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር)፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ የማቅረቡ ሥራ ከግብረ ኃይሉ ወጥቶ በመደበኛው መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ታደሰ (ዶ/ር)፣ ለተፈናቃዎች ዘላቂ መፍትሔ ማዘጋጀትን በተመለከተ በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ ስደተኛና ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር፣ እንዲሁም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን የያዘ ቡድን የዘላቂ መፍትሔ አተገባበር ስትራቴጂ እንደሚያዘጋጅ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ አካላት ባሻገር ፍትሕ ሚኒስቴርን ያካተተና በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የቴክኒክ ድጋፍ የሚደረግለት ቡድን፣ የካምፓላ ኮንቬንሽን ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮንቬንሽኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያሏቸውን መብቶችና መንግሥት የሚኖሩበትን ግዴታዎች በዝርዝር እንደሚያብራራ የተናገሩት ታደሰ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ብታፀድቀውም እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ሁሉ በአገር ውስጥ ለመተግበር አስቻይ ሕግ እንደሌለው አስተረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኮንቬንሽኑ ቢፀድቅም ፍርድ ቤቶች እንደማይጠቅሱት፣ በታችኛው መዋቅር ላይ ያሉ የመንግሥት ተቋማት እንደማይጠቀሙበትና ተፈናቃዮችም ቢሆን መብት አድርገው ለማስፈጸም እንደሚቸገሩ አስረድተዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት ሥራውን ከዚህ ችግር ለማፅዳት መታሰቡን የሚገልጹት ኃላፊው፣ የተፈናቃዎችን መብትና ግዴታዎችን በተመለከተ ተጨማሪ ሕግ መውጣቱ መንግሥት ተፈናቃዎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ፣ የማደራጀትና አዳዲስ መሠረት የማስያዙ ሥራዎችን የሚያከናውንበት ግልጽ የሆነ የሕግ መሠረት እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡
በጦርነቱ ሳቢያ ነዋሪዎች በተፈናቀሉባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተፈናቃዮቹን የመመለስ ሥራው ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ተናግረው፣ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ ግን መንግሥት ሥራውን ለማከናወን መተማመን እንደሚፈጥርለት አስረድተዋል፡፡
‹‹አሁን ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የመብትና የግዴታ ማዕቀፍን ለይተን በሕግ በማስቀመጥ፣ የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ያላቸውን መብትና ግዴታ አስረግጠን አስረድተን የምንሠራው ሥራ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው ቡድን የሕግ ማዕቀፉን በምን ዓይነት መንገድ ይውጣ የሚለውን በማጥናት ላይ እንደሆነ የገለጹት ታደሰ (ዶ/ር) ጥናቱን ሲጨርስ በአዋጅ፣ በመመርያ ወይም በሌላ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ይውጣ የሚለውን ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ይኼንን በተመለከተ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሕጉን ማርቀቅ አስቸጋሪ እንደማይሆን አክለዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በ1999 ዓ.ም. ያወጣው የካምፓላ ኮንቬንሽን በዓለም ላይ ቀዳሚው የአገር ውስጥ ተፈናቃዎችን ጥበቃና ድጋፍ ሕጋዊ መሣሪያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ኮንቬንሽኑን ያፀደቀች 31ኛዋ አገር ነች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዮናስ ቢርመታ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ኮንቬንሽኑ በዋነኛነት መፈናቀል እንዳይኖር መከላከል፣ ይኼ ሳይሳካ ሲቀር ለተፈናቃዮች የጥበቃ ሥራ ማከናወንና ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበት መንገድ መፍጠር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ አገር አቀፍ ኃላፊነት መሆኑን የሚናገሩት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ከአደጋ ሥጋት ፖሊሲ ውጪ የአገር ውስጥ መፈናቀልን መከላከል ዓላማው ያደረገ ማዕቀፍ አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዮናስ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ጉዳዩ አገር አቀፍ ኃላፊነት በመሆኑ በመንግሥት ትክሻ ላይ የሚወድቅ ቢሆንም መርሆዎቹ ላይ ብዥታ አለ፡፡ በመጀመሪያ መፈናቀል እንዳይኖር መከላከል የመንግሥት ሥራ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ቦታዎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ጭምር በመፈናቀሉ ላይ እጃቸውን ሲያስገቡ እንደሚታይ አብራርተዋል፡፡ አሁን የሕግ ማዕቀፍ መውጣቱ ይኼ ሲፈጸም በወንጀል ለመፈረጅና ተሳትፈዋል የሚባሉ ግለሰቦችን ለመቅጣት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ መንግሥት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ ሲያበጅ የውሳኔው አካል እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው የሕግ መምህሩ አስረድተዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ ተፈናቃዮች ያለ ፍላጎታቸው ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ እንደሚደረግ የገለጹት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ተፈናቃዎቹ እንዲመለሱ የሚደረግበት ቦታ የደኅንነት ሥጋት ያለበት ከሆነ መፈናቀሉ በድጋሚ እንደሚከሰት፣ የካምፓላ ኮንቬንሽንን መሠረት የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ሲዘጋጅ ግን በቅድሚያ ተፈናቃዮቹ ፍላጎታቸው እንዲጠየቅ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ ንብረታቸውና ይዞታቸው በሌሎች ተይዞ የሚጠብቃቸው ተፈናቃዮች፣ ንብረትና ይዞታቸውን መልሰው ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለማዘጋጀት እንደሚረዳም አክለዋል፡፡
የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎችን በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ተፈናቃዮቹ ወደ መደበኛ ቦታቸው መመለስ ወይም ባሉበት ቦታ እንዲቋቋሙ ማድረግ ነው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መውሰድም ሆነ ባሉበት ቦታ ሕይወት እንዲመሠርቱ ማድረግ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲሚጠይቅ የተናገሩት ታደሰ (ዶ/ር)፣ ይኼንን ተግባራዊ ማድረግ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን ሰብዓዊ ዕርዳታ የማቅረብ እንጂ፣ ተፈናቃዎችን የማቋቋም ሥራ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት የለውም ብለዋል፡፡