የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከግብፅ (ፈርኦኖቹ) ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በሜዳው እንዳያደርግ መከልከሉን ተከትሎ፣ በገለልተኛ ስታዲየም የሚያደርግበትን ቀን እንዲያሳወቅ ካፍ ለግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባው ብሔራዊ ቡድኑ ከግብፅ ጋር የሚያደርገውን የምድቡን የመጀመርያ ጨዋታ በማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ በሚገኘው ቢንጉ ስታዲየም ለማከናወን ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በይፋዊ ገጹ ላይ እንደገለጸው፣ ከማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ፌዴሬሽኑና የአገሪቱ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠታቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የኢትዮጵያን ምርጫ አፅድቆ የማረጋገጫ ደብዳቤ ልኳል፡፡
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ መክፈቻ ጨዋታ ማላዊን ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲገጥም፣ በዚያው በማላዊ ቆይታ በማድረግ ግንቦት 29 ቀን ግብፅን የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ አንድም የካፍን መሥፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ስለሌላት፣ ማንኛውንም ጨዋታ እንዳታስተናግድ መታገዷ ይታወሳል፡፡ ካፍም በኢትዮጵያ ያሉትን ስታዲየሞች ጥራታቸውን የጠበቁና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ ሆነው እንዲገነቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የባህር ዳር ስታዲየምም ዕገዳውን ተከትሎ ዕድሳት ቢያደርግም፣ ካፍ ያስቀመጠውን መሥፈርት ማሟላት አለመቻሉ ተገልጾ ዳግም ሊታገድ ችሏል፡፡ የካፍ የስታዲየም ጥራት ገምጋሚ ቡድን በባህር ዳር ባደረገው ግምገማ መሠረት ማሟላት ያልቻላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
የመጫወቻ ሜዳው አዲስ የተፈጥሮ ሳርና አውቶማቲክ የውኃ ማጠጫ እንደሚያስፈልገው፣ የተጠባባቂና የጨዋታ አመራሮች መቀመጫና የኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባለማሟላቱ እንዲቀየር፣ ከአሠልጣኞች መቆሚያ ቢያንስ አምስት ሜትር የራቀ፣ በአግባቡ የተዘጋጀ፣ የተጠባባቂና የጨዋታ አመራር መቀመጫ እንዲሠራ፣ የካፍን መመዘኛ የሚያሟላ የስታዲየም ፓውዛ እንዲኖርና ተለዋጭ የኃይል አቅርቦትም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ተመልክቷል፡፡
የመልበሻ ክፍሎች ያሉባቸው ደረጃም የካፍን መመዘኛ ባለማሟላታቸው ሙሉ በሙሉ በአዲስ መልክ መሠራት እንዳለባቸው፣ የክፍሎቹ ምንጣፎች፣ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት መቀመጫዎች፣ ሎከሮች፣ የማሳጅ ጠረጴዛ፣ የታክቲክ ቦርድ፣ ሙቅና ቀዝቃዛ ውኃ፣ አየር ማቀዝቀዣና የመሳሰሉትን ከማሟላት በተጨማሪ የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የማሟሟቂያ ቦታዎች በሰው ሠራሽ ሳር መሸፈን እንዳለባቸው፣ የኳስ አቀባዮች ክፍሎች፣ የዶፒንግ መቆጣጠሪያ ክፍሎች ላልተፈቀደላቸው ሰዎች ዝግ መሆን እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡
የስታዲየሙ በሮች ዕድሳትና ለአንድ ሰው ደረጃውን የጠበቀ አንድ ወንበር፣ ለመቀመጫዎቹ የጣሪያ ሽፋን፣ ምግብና የመዝናኛ አገልግሎት፣ ለስታዲየሙ ደኅንነት ደረጃውን የጠበቀ የእሳት አደጋ መከላከያ ሰርተፊኬት፣ ለአደጋ ጊዜ ጠቋሚ ምልክቶች፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና በአግባቡ የተለየ የፓርኪንግ አገልግሎት፣ ግዙፍ ስክሪን፣ የኤሌክትሪክ ሲስተም፣ ለተመልካቾች የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና መስጫ አቅርቦት፣ ለአካል ጉዳተኞች አመቺ መቀመጫዎች መኖር አለባቸው ብሏል፡፡
ለቪአይፒና ቪቪአይፒ መቀመጫዎችና ከፍ ያለ ደረጃውን የጠበቀ ላውንጅ፣ የመስተዋት መለያ በቪአይፒና በሚዲያ ክፍል መካከል፣ የሚዲያ ትሪቢዩን፣ የፕሬስ ኮንፈረንስ ክፍሎች እስከ 50 የሚደርሱ ዘመናዊ መቀመጫዎች ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ የቴሌቪዥንና ብሮድካስት የጨዋታ አስተላላፊዎች ሳጥኖች መሻሻል እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡
የልምምድ ቦታ መብራቶች ቢያንስ አንድ ቡድን የሚያስተናግድበት መልበሻ ክፍል ያለው የመታጠቢያና መፀዳጃ ቤት፣ የአምቡላንስ አቅርቦትና ሌሎችም በርካታ መሟላት የሚገባቸው መሥፈርቶች ያልተሟሉለት ስለመሆኑ ጭምር ካፍ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በመሆኑም ካፍ ኢትዮጵያ ለመጪው ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ በሜዳዋ የምታደርገው ጨዋታ እንደማይኖርም አሳውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ረብጣ ገንዘብ የፈሰሰባቸው ስታዲየሞች ቢገነቡም፣ የሃይማኖታዊ በዓላትና ፖለቲካዊ ስብሰባዎች ሲከናወንባቸው ብቻ ይስተዋላል፡፡ በክልል ከተሞች የተገነቡ ስታዲየሞች ጥራታቸውና አሠራራቸው አመቺ ያለመሆናቸውን ተከትሎ፣ ዘመናዊውን የስታዲየም መሥፈርት ሟሟላት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አለመኖራቸው ይነሳል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ስታዲየሞቹ ግዙፍ መሆናቸው፣ አስፈላጊውን ግንባታ ለማድረግ አመቺ አለመሆናቸው ይተቻል፡፡ በዚህም በርካታ አነስተኛ ስታዲየሞች መገንባት የሚያስችለውን የገንዘብ መጠን እንዲባክን ማድረጋቸው ይነሳል፡፡
ከክልል ስታዲየሞች ባሻገር ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የአደይ አበባ ስታዲየም ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ መጀመሩን ይፋ ቢደረግም የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መጨመራቸውን ተከትሎ ዳግም ግንባታው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣይ ለምታደርጋቸውን ጨዋታዎች ‹‹የትኞቹን ከተሞች ደጅ ትጠናለች?›› የሚለው የብዙኃኑ ጥያቄ ነው፡፡