በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ቅሬታ ከሚያስነሱ ተጠቃሽ ከሆኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሌብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎንም ደንታ ቢስነት፣ የብቃት ማነስና በፍጥነት እየተለወጠ ካለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር እኩል መራመድ እንዲሁ፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን በማመን እነሱን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም፣ ብዙ ጊዜያት ወስደውበታል፡፡ ቀልጠፍና ቆፍጠን ያለ ዕርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ብሶቶችና ምሬቶች ይሰማሉ፡፡ አሁን ጊዜው የሥራ ነው፡፡ ሹመት የተሰጣቸው ግለሰቦች ራሳቸውን ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለውጤታማ ሥራ ይትጉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላትና ተሿሚዎች፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሱ ያሉትን በደሎች ማስቆም አለባቸው፡፡ ቢሮክራሲው ካለበት አረንቋ ውስጥ ወጥቶ በአገልጋይነት መንፈስ እንዲሠራ አመራር የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለመደው መንገድ እየተጓዙ ለውጥ መጠበቅ ስለማይቻል፣ መንግሥት ቢሮክራሲውን ካለበት አስፈሪ ድባብ ውስጥ የማውጣት ግዴታ አለበት፡፡ ሕዝብን ለአምስት ዓመት አገለግላለሁ ብሎ ቃል የገባ አስፈጻሚ ሥራውን መሥራት ካቃተው መወገድ አለበት፡፡ ከዘመኑ ጋር የማይመጥን ኋላቀር አመራርን ለመቀበል ማንም ትዕግሥት የለውም፡፡
የመንግሥት ውጤታማነት ከሚገለጽባቸው መሠረታዊ ከሚባሉ አገልግሎቶች መካከል የትምህርት ሥርዓቱና ጥራቱ፣ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተደራሽነትና ጥራት፣ የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦትና ጥራት፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ጥራት፣ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት አቅርቦትና የአገልግሎት ጥራት፣ የበጋና የክረምት መንገዶች ብዛትና ጥራት፣ የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ አገልግሎት ጥራት፣ የበጀትና የፋይናንስ አስተዳደር የጥራት ደረጃ፣ የገቢ አሰባሰብ ብቃት፣ ውጤታማ የሆነ የሕዝብ አስተዳደርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከላይ በተጠቀሱት የተለያዩ መስኮች ውስጥ የሕዝብ እርካታ ምን ይመስላል? እንዴትስ ይለካል? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ በተቋማት ደረጃ ሕዝብ በጣም የሚማረርባቸው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመገናኛና ትራንስፖርት፣ የመሬት አስተዳደር፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣ የወረዳና የክፍላተ ከተሞች፣ ወዘተ. ተቋማዊ ጥንካሬያቸውና የአመራሮቻቸው ብቃት ምን ይመስላል? ከዘመኑ ቴክኖሎጂና ዕውቀት ጋር የሚመጣጠን ቅልጥፍና ለምን የላቸውም? ተብሎ በፅኑ መገምገም አለበት፡፡
የመንግሥት ተቋማትና አመራሮች ድክመት ጉዳይ ችላ በተባለ ቁጥር አደጋው ለራሱ ለመንግሥት ነው፡፡ ሕዝቡ በየደረሰበት አስተዳደራዊ በደሎች ሲፈጸሙበትና የአገልግሎቶች መስተጓጎል ሲደርስበት፣ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ይጠፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለአመፅ፣ ለብጥብጥና ለሁከት በር ይከፍታል፡፡ ችግር ሲፈጠር ሕግ ለማስከበር አዳጋች ይሆናል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ይከሰትና ለሞትና ለንብረት ውድመት በር ይከፍታል፡፡ ዜጎች መሠረታዊ የሆኑ የፍጆታ ምርቶች ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ከባድ ነው፡፡ የመጠለያና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን አለማግኘትም እንዲሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አመራሮች ፈጣን ምላሽ ሲጠፋ ደግሞ ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡ የብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማትና አመራሮች ዘገምተኝነት፣ ድንገተኛ የሆኑ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱም ይስተዋላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕገወጥ ነጋዴዎች ምክንያት በሕዝብ ላይ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሲፈጠር ፈጣን ምላሽ ሲሰጥ አይታይም፡፡ ገበያውን ሥርዓተ አልበኞች እንደፈለጉ ሲፈነጩበትና ሕዝቡን ግራ ሲያጋቡት፣ የሚመለከታቸው ተቋማት የሚባንኑት በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች ከተከናወኑ በኋላ ነው፡፡
በብዙዎቹ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ መረን የተለቀቀው ዘረፋ ጉዳይ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ነገር ግን ዝርፊያ ገንፍሎ በተዝረከረከበት በዚህ ወቅት፣ ተቋማቱና አመራሮቹ ካልታደሱ በስተቀር ለአገር መከራ ነው፡፡ ከትንሹ የጉቦ መደራደሪያ እስከ ትልቁ ግዥና ጨረታ ድረስ በየቦታው የሚታየው ዓይን ያወጣ ዝርፊያ፣ የመንግሥትን ውጤታማነት ችግር ውስጥ እየከተተው ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት ሳይቀሩ የሙስና መናኸሪያዎች ሆነዋል፡፡ ሕዝብ አገልግሎት ፍለጋ የሚሄድባቸው ብዙዎቹ ተቋማት ‘ጉዳይ ገዳይ’ በሚባሉ የሌባ አቀባባዮች ተወረዋል፡፡ ዘራፊዎች ከንፁኃን በላይ እየተንጎራደዱ አገር ሲያጠፉ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል? ሁኔታው አስፈሪ ነው፡፡ መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገር ለማስተዳደር ቆርጬ ተነስቻለሁ ሲል፣ የተቋማቱንና የአመራሩን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል፡፡ የዘረፋው ደን ጥቅጥቅ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች መሽገውበታል፡፡ አቅም የሌላቸውና ደንታ ቢሶች ደግሞ በየቦታው ተሰግስገዋል፡፡ በስመ የድርጅት አባልነትና በብሔር ተዋፅኦ ዕውቀትም ሆነ የረባ ልምድ ሳይኖራቸው፣ ተቋማትን እየመሩ ያሉ ሰዎች ብቃት ባላቸው ካልተተኩ መዘዙ የከፋ ነው፡፡
ተቋማት በዕውቀትና በክህሎት እየተመሩ በሕግ የተሰጡዋቸውን ኃላፊነቶች መወጣት ሳይችሉ ሲቀሩ፣ ሕገወጥ ድርጊቶች ይንሰራፉባቸዋል፡፡ በኔትወርክ የተሳሰሩ ዘራፊዎች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ከብቃት ይልቅ የብሔርና የጥቅም ግንኙነት ይነግሣል፡፡ በቅጥር፣ በምደባ፣ በሹመት፣ በዝውውር፣ በትምህርት ዕድልና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች አድሎአዊነት ይንሰራፋል፡፡ በሕግ የተሰጠ ሥልጣን ያላግባብ የጥቅም ማጋበሻ ይሆናል፡፡ የአገልጋይነትን መንፈስ በማዳፈን ሥርዓተ አልበኝነት እንዲንሠራፋ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ለእንዲህ ዓይነቱ መራር ችግር መፍትሔ ለመፈለግ በቁርጠኝነት የሚነሳ ከሆነ፣ ከአስመሳይነትና ከአድርባይነት የፀዱ ወገኖችን ነው ከጎኑ ማሠለፍ ያለበት፡፡ በኔትወርክ የተቧደኑ ኃይሎች የዘረፋ ይዞታቸውን ላለማስነጠቅ በሚያደርጉት ትንቅንቅ፣ ጠንክሮ የሚፋለማቸው በራሱ የሚተማመን ኩሩ ዜጋ እንጂ አስመሳይና አድርባይ አይደለም፡፡ ሥራ ፈቶ ስብሰባ ማብዛት ዋነኛው የአስመሳዮችና የአድርባዮች መደበቂያ ነው፡፡ ከሥራ ይልቅ ለወሬ ቅርብ የሆኑት እነዚህ ኃይሎች በስብሰባ ወቅት በተግባር የማይተረጎሙ ንድፈ ሐሳቦችን በመተንተን፣ የማይፈልጓቸውን ወገኖች በማመናጨቅና በማስፈራራት፣ የሕዝብ ቅሬታዎችን በማዳፈንና ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማይዛመዱ ጉዳዮችን በማመንዥክ በአገርና በሕዝብ ጊዜና ሀብት ላይ ይቀልዳሉ፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን በማስወገድና ሥርዓተ አልበኞችን ሕግ ፊት በማቅረብ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል፡፡ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የተጠናከረና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር መስፈን አለበት፡፡ በዘገምተኛነትና በችላ ባይነት ምክንያት አጣዳፊ ጉዳዮች ሲጓተቱ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስከፍላሉ፡፡ በተለይ እጅግ ዘገምተኛ የሆነው የመንግሥት አሠራር መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ካልተደረገበት አደጋው ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ችግሮችን መሸፋፈንና ራስን ማታለል አገሪቱን የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ይከታታል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳሳቢ ችግሮች ሲያጋጥሙ ዝግጁነቱና የመከላከሉ ብቃት በተቻለ መጠን በአሳማኝ ሁኔታ ለሕዝቡ ጭምር ይታይ፡፡ ለሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮች የሚሰጠው ምላሽና ዝግጁነት በሕዝብ ሲመዘን ነው ተስፋ የሚኖረው፡፡ መንግሥት ለሕዝብ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ሲሰጥና ፀጥታ የማስከበር ዝግጁነቱን ሲያሳይ፣ ያሉ ችግሮችን ከሥራቸው ነቅሎ ለመጣል የሚያስችል ተጨማሪ ጉልበት ያገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት በሕዝብ ትብብር እንጂ፣ በመንግሥት ወይም በሚያሰማራቸው የፀጥታ ኃይሎች ብቻ እንዳልሆነ ግንዛቤ ይኑር፡፡ ዘመናዊ ሠራዊትም ሆነ የፀጥታ መዋቅር የሚገነባው በሕዝብ ድጋፍ ነውና፡፡ ከሕዝብ ጋር ለመግባባት ደግሞ መምራት የማይችሉ ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ ገለል ይደረጉ!