Tuesday, March 28, 2023

እንደገና ሥጋት የፈጠረው የሰሜኑ ጦርነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሳምንቱ መጀመርያ ከወደ ትግራይ ሚዲያዎች ባሠራጩት ዘገባዎች፣ የሕወሓት አመራሮች እንደገና ወደ ጦርነት ለመግባት ያላቸውን ፍላጎት የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በአንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ከሰሞኑ ተናግረውታል የተባለ በቪዲዮ ተደግፎ የወጣ መረጃ፣ ስለጦርነት እንደገና መቀስቀስ ብዙ መረጃዎችን የሚሰጥ ይመስላል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ተናገሩት ተብሎ በቪዲዮ ተደግፎ ከወጣው መረጃ መካከል ደግሞ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

‹‹የተኩስ አቁሙን የተስማማነው እየተራበ ላለው ሕዝባችን ዕርዳታ እንዲገባለት ብለን ነበር። ለጊዜው ዕድል እንስጠው ብለን ያደረግነው ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከበባውን ቀጥሎበታል። በዚህ ሁኔታ ልንቀጥል አንችልም። የራሳችንን ዕድል በራሳችን እንወስናለን ካልን፣ ሪፈረንደም እናደርጋለን ብለን የምናወራ ከሆነ የኃይል የበላይነት ሊኖረን ይገባል፤›› የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ የደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ንግግር መነጋገሪያ ሆኖ በሰነበተበት ባለፈው ሳምንት የትግራይ ሚዲያ ሐውስ፣ ‹‹ሰላምና ጦርነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ፕሮግራም የጦርነቱን እንደገና መቀስቀስ የሚያስረግጡ ሁኔታዎችን አመላክቷል፡፡ ‹‹የትግራይ ሕዝብ እየተራበና መተላለፊያ ኮሪዶር እየተከለከለ ከጦርነት ውጪ ምን እንዲፈጠር ነው የሚጠበቀው?›› በማለት አንዱ አቅራቢ ለጦርነቱ ገፊ ምክንያት የፌዴራል መንግሥቱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ከሰሞኑ ከትግራይ አካባቢ ወይም ለሕወሓት ቅርብ ከሆኑ የሚዲያ ምንጮች የሚደመጡ መረጃዎች ሌላ ዙር ጦርነት ሊከፈት እንደሚችል የሚያስጠነቅቁና ፍንጭ የሚሰጡ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይህንኑ የሕወሓት የጦር ዝግጅት ለመስተንተን የሞከረው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ረዕቡና ቅዳሜ ምሽት የሚቀርበው ‹‹ስለ አገር›› የተባለ የውይይት ፕሮግራም፣ የሕወሓትን የጦር ዝግጅት  የሚያረጋግጡ የጦር ጄኔራሎችን ንግግሮች አካቶ አቅርቧል፡፡ ‹‹የሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ) ኢትዮጵያን የማተራመስ ምክረ ሐሳብና የሕወሓት ሦስተኛ ዙር የዕልቂት ዕቅድ›› በሚል ርዕስ በሳምንቱ አጋማሽ የቀረበው የዚህ ፕሮግራም ክፍል፣ የሕወሓት ቁንጮ ጄኔራሎች የጦር ድግሱን ተናግረዋል ሲል ከንግግሮቻቸው ጋር ያቀርባል፡፡

የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከሆኑት አንዷ ጋዜጠኛ አበበች ካህሳይ የሕወሓት  አመራሮች በማይጨው፣ በመቀሌና በሌሎችም አካባቢዎች ሰፊ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡ የትግራይን ጉዳይ በቅርበት የምትከታተለዋ ጋዜጠኛ አበበች ለሪፖርተር እንዳረጋገጠችው ከሆነ፣ የሕወሓት አመራሮች ሕዝቡን ከመቀስቀስ አልፈው በማስታጠቅ ጭምር ለጦር ድግስ እያዘጋጁት ይገኛል፡፡ ‹‹ከ50 ዓመት አዛውንት እስከ ታዳጊ ሕፃናት መተኮስ ይችላል ብለው ያመኑትን በሙሉ እያሠለጠኑ ነው፡፡ ባለፈው ዘመቻ ሕይወቱን አትርፎ ወደ ቤተሰቦቹ የተመለሰውን ወጣትም ዳግም ታጠቅ ብለውታል፡፡ በቅፅል ስማቸው ጆቤ የሚባሉት ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት ከሁለት ሳምንት በፊት ‹‹ኢትዮጵያን የማተራመስ ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን›› ብለው ተናግረዋል፡፡ ዓለም ገብረ ዋህድም ይህንኑ ተልዕኮ ከሰሞኑ በወጣና በሚስጥር በተያዘ ቪዲዮ ሲናገሩት ተደምጠዋል፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የደገሙት ይህንኑ የጦር ዝግጅት ነው፤›› በማለት ጋዜጠኛዋ በትግራይ ክልል ያለውን የጦር ዝግጅት ሒደት ተናግራለች፡፡

ከወራት በፊት በመንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ሲደረግና በትግራይ ክልል ድንበር ላይ ሠራዊቱ በተጠንቀቅ እንዲቆም ሲታዘዝ፣ ዳግመኛ አደጋ በማይፈጥርበት ደረጃ ላይ አድርሰነዋል የተባለው ሕወሓት እንደገና ሠራዊት አሠልጥኖ ለጦር እየተዘጋጀ መሆኑ መሰማቱ ያነጋግራል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም ሊጀመር ነው የሚለው ሥጋት ከሰሞኑ አየል ብሎ ቢሰማም፣ ነገር ግን ከአፋር ግንባር ሲሰሙ የቆዩ መረጃዎች ጦርነቱ ጋብ ቢል እንጂ ቆሞ እንደማያውቅ የሚያረጋግጡ ነበሩ፡፡ የአፋርን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ የሪፖርተር መረጃ ምንጮች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች ሲካሄዱ እንደከረሙ ይናገራሉ፡፡ ሕወሓት የአፋር ክልልን ከሁለት ሳምንት በፊት ሙሉ ለሙሉ ለቆ መውጣቱንና ይህንንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በበጎ እንደተቀበለው ሲዘገብ ቢቆይም፣ ነገር ግን በአንፃሩ በአንዳንድ የድንበር አካባቢዎች መለስተኛ የሚባሉ ግጭቶች ሲካሄዱ እንደቆዩ ነው የአፋር ምንጮች ያረጋገጡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በበኩሉ ከሰሞኑ ባሠራጨው አንድ ዘገባ፣ ‹‹የስኩፕ ኢንዲፔንደንት ዜና›› ዋና ኤዲተር አሊስተር ቶምሶን የተባለ ጋዜጠኛ ሕወሓት እንደገና ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን መናገሩን ዘግቦ ነበር፡፡ ጋዜጠኛው በሕወሓት ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መመልከቱንና ብዙ ጉዳት መድረሱን ጠቅሶ፣ ቡድኑ ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን እንደተረዳ መናገሩን በዚህ ዘገባ ተጠቅሷል፡፡

በሌላም በኩል ሕወሓትን በመቃወምና በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በግልጽ በመተቸት የሚጠቀሱት አን ፊዝጄራልድ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ሕወሓት ሕዝቡን ለዳግም ጦርነት እያዘጋጀ ነው ማለታቸውም በብዙ መገናኛ ብዙኃን እየተጠቀሰ ሲዘገብ ነው የከረመው፡፡ ፕሮፌሰሯ የመረጃ ምንጭ ተብራርቶ ባይጠቀስም ነገር ግን፣ ‹‹ሕወሓት የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት መመልመል መቀጠሉን የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊዝጄራልድ ገለጹ›› እየተባለ በዋና ዋና መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ገጾች ሲሠራጭ ነበር፡፡  

ፕሮፌሰሯ ቡድኑ አሁንም በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን እንደያዘና ከሁለቱ ክልሎች ሙሉ ለሙሉ ለቆ አለመውጣቱን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የተናጠል ሰብዓዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈው የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ ሕወሓት አይደለም ያሉት ፕሮፌሰሯ፣ ተኩስ አቁሙ በሁለቱም ወገኖች ሊከበር ይገባል ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡

እነዚህን መሰል መረጃዎች እየተሠራጩ ባሉበት ወቅት ደግሞ ከሕወሓት ቁንጮ አመራሮች አንዷ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ)፣ አቶ ዓለም ገብረዋህድና አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ነዋሪዎችን አወያዩ ብለው የትግራይ መገናኛ ብዙኃን አውታሮች፣ ‹‹ሕዝቡ ለመጨረሻው ምዕራፍ ትግል እንዲዘጋጅ አመራሮቹ ጠይቀዋል›› ሲሉ በተለያዩ መንገዶች ዘግበዋል፡፡

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ባለመሳካቱና የሰላም መንገድ በመዘጋቱ፣ የትግራይን ሕዝብ ነፃነት ለማረጋገጥ የክልሉ ሕዝብ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቀረቡ የሚል የጦርነቱን መቃረብ የሚጠቁሙ ዘገባዎች ተከታትለው ወጥተዋል። ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በመቀሌ፣ ሌሎች የሕወሓት አመራሮች ደግሞ በተለያዩ የትግራይ ዞኖች ከነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የትግራይ ሕዝብ አሁን ያለበት የከፋ ሥቃይ እንዲቀለበስና የትግራይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል እየተባለም፣ በተለያዩ መገናኛ አውታሮች እየተዘገበ ነው።

በርካታ የመረጃ ምንጮች ይህንኑ የሕወሓት ባለሥልጣናትን መረጃ ተጨባጭ ለማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያለፈው ሳምንት የምዕራብ ዕዝ ጉብኝትን አስረጂ አድርገው አቅርበውታል፡፡ በሕወሓት በኩል ያለውን የጦር ድግስ ተረድቶ የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ቅድመ ዝግጅት ለጦርነቱ እያደረገ ነው ሲሉም በርካቶች ሁለቱን መረጃ አቆራኝተው አቅርበዋል፡፡ ሌላው በተለይ የሕወሓት ደጋፊ በሆኑ ሚዲያዎች በሚቀርቡ መረጃዎች፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦና ልማት ድርጅት (ዩኤስኤድ) ዋና ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ሰጡት የተባለው ሪፖርት ለጦርነቱ እንደ አንድ ገፊ ምክንያት ሆኖ ሲቀርብ ነው የሰነበተው፡፡ በሳምንት 500 የዕርዳታ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች እንዲገቡ ቢፈለግም ሆነ መጋዘኖችን በዕርዳታ እህል የሞሉ ቢሆኑም፣ መንግሥት ግን መንገዶችን ዝግ አድርጎብናል ብለው ሳማንታ ፓወር ተናግረዋል ይላሉ እነዚህ ወገኖች፡፡ የዕርዳታ አቅርቦትን መንግሥት በመዝጋቱም የትግራይ ክልልን የተቆጣጠረው ሕወሓት ኮሪዶር ለማስከፈት እንደገና ወደ ጦርነት ለመግባት እንዲገፋፋ እያደረገው ነው በማለት፣ ዳግም ጦርነቱን ፍትሐዊ አድርገው ለማቅረብ ሲጠቀሙበት መታየታቸው እየተነገረ ነው፡፡

የሕወሓት ኃይሎች በተለይ የዓብይ (ዶ/ር) የምዕራብ ዕዝ ጉብኝትን ብቻ ሳይሆን፣ ከሰሞኑ በባህር ዳር በተካሄደው በህልውና ዘመቻው ላይ ለተሳተፉ ኃይሎች የሽልማት ሥነ ሥርዓት መድረክ ላይ፣ በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የተደረጉ ንግግሮችን እንደ አንድ የጦር ዝግጅት ማሳያ አድርገው እያቀረቡም ይገኛሉ፡፡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ጠንካራ አፀፋ የሚሰጥ የፀጥታ ኃይል የማደራጀትን አስፈላጊነት መግለጻቸው፣ በአማራ ክልል በኩል ለጦርነት ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚል ማስረጃ ሆኖ ሲቀርብ ተሰምቷል፡፡ በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጠላቶቻችን ከትናንትም ከታሪክም ተምረው ካልታቀቡ የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ ለኢትዮጵያውያን የማይከብድ ሥራ ነው፤›› ማለታቸውን በመጥቀስ ጠላቶች ያሏቸውን ወገኖች በዚሁ መድረክ ማስጠንቀቃቸው፣ የፌዴራል መንግሥቱን የጦር ዝግጅት የሚያሳይ ነው ተብሎ እየቀረበ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን አሁንም መልስ ያላገኙ ብዙ ጥያቄዎች በብዙኃኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ሲስተጋባ ይሰማሉ፡፡ ለዚህ ጦርነት የሰላም መፍትሔ ታጣ ወይ? ከሚለው አንስቶ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ተኮላሽተዋል ወይ? የሚሉ ናቸው፡፡ ጦርነት በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍም አገራዊውም ሁኔታ አስከፊ ገጽታን በያዘበት ወቅት አስፈላጊ ሆኖ ነው ወይ ወደ ሦስተኛ ዙር ጦርነት የሚገባው የሚሉ ወገኖችም ድምፅ ይደመጣል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረ ግጭቱን ጀማሪው ማን ነው? ጥቃቱን የሚከፍተው በየት ግንባር? እንዲሁም ዕልቂቱ አገሪቱን ወዴት ይወስዳታል? የሚሉ ተያያዥ ጥያቄዎች ሲስተጋቡ ይደመጣል፡፡

በአማራ ክልል ዳግም ጦርነት?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ እንደገና ወደ ጦርነት የመግባት ዝንባሌ በሕወሐት በኩል መኖሩን በርካታ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ይናገራሉ፡፡ ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተል ዜጋ አዝማሚያው ወዴት እያመራ እንደሚገኝ ግምታቸውን እንደሚናገሩ ያስረዱት ሲሳይ  (ዶ/ር) በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ለጦርነት የሚጋብዙ ገፊ ምክንያቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹አሁንም ቢሆን ሕወሓት ከአንዳንድ የአፋርና የአማራ ክልሎች ወሰን አካባቢዎች ለቆ አልወጣም፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች መጋጨቱ እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የወሰን አካባቢዎቹ ሁኔታ እንደገና በሦስቱ ክልሎች ከባድ ጦርነት ለመቀስቀስ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤›› በማለት የትግራይ ክልል ከአጎራባቾቹ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ጋር ያለበትን ፍጥጫ ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በወልቃይት ጠገዴና በአካባቢው ወደ ጎረቤት አገሮች መውጫ በር ለማስከፈት የሚደረግ ፍላጎት ሕወሓት ያለው በመሆኑ፣ በዚያ መስመር ጥቃት ሊከፍት እንደሚችልም ሲሳይ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ በሱዳን ድንበር በኩል ከውጭ ያሉ ሕወሓትን ደጋፊ ኃይሎች ጥቃት ያጠናክራሉ የሚል ግምት እንዳላቸውም ይገልጻሉ፡፡  ‹‹የትሕነግ አመራሮች ከሰሞኑ የሚያደርጉት ሕዝባዊ ስብሰባና የሚናገሩት ንግግር ደግሞ የጦርነቱን አይቀሬነት እንድንገምት ያስገድዳል፤›› ሲሉ ከትግራይ በኩል የጦር ዝግጅት መኖሩን የሚደግፉ በርካታ መረጃዎች እንዳሉ ያሰምሩበታል፡፡

በመንግሥት በኩልም ለሕወሓት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነት እንደሚታይ የሕግ ምሁሩ ሲሳይ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በሰቆጣ፣ በራያ ቆቦ ግንባር፣ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ተገኝተው ሕዝቡንና የመከላከያ ሠራዊቱን ማናገራቸው ያውም የጦር ልብስ ለብሰው ከመታየታቸው ጋር ተደማምሮ፣ መንግሥት ለጦርነቱ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን እንደሚያመለክት ነው፤››  በማለት ሲሳይ (ዶ/ር) ግምታቸውን የሚናገሩት፡፡

ይህን ግምት ደግሞ በአማራ ክልል ያሉና የጦር ቀጣና ሊሆኑ ይችላሉ ለሚባሉ አካባቢዎች ቅርብ የሆኑ ምንጮችም ሲደግፉት ይታያል፡፡ በወልቃይት ግንባር ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በቅርበት የሚከታተለው ጸሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን፣ ሕወሓት በቅርቡ ወደ ግጭት መግባቱ ስለማይቀር ለዚያ ዝግጅት መደረጉን ይናገራል፡፡ ‹‹አንዳንዶች ከፋኖ ጋር በተያያዘ ከፋፋይ አጀንዳዎችን በመፍጠር ቢሠሩም፣ እውነተኞቹ ፋኖዎች ግን ግንባር ላይ ምሽግ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ሕወሓት ያለ ጦርነት መተንፈስ አይችልም፡፡ ጦርነቱን ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በተጨባጭ በወልቃይት ግንባር የሚታይ የሕወሓት የዳግም ግጭት እንቅስቃሴ ነው፤›› ሲል በቅርበት ስለሚከታተለው አካባቢ ሁኔታ ገልጿል፡፡

በወልዲያ የማኅበረሰብ አንቂና የፋኖ አደረጃጀት አስተባባሪ የሆነው ቴዎድሮስ አያሌው በበኩሉ ሕወሓት በተጨባጭ ራሱን ለዳግም ጦርነት እያዘጋጀ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹በሕወሓት በኩል የትንኮሳ ሙከራዎች አሉ፡፡ የጦርነት ዝግጅትም አድርገዋል፡፡ ይህን ራሱ መንግሥትም ያወቀ ሲሆን፣ በሁሉም ረገድ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረጉን ነው የማውቀው፤›› በማለትም፣ በወቅቱ ከሕወሓት በኩል ሊቃጣ ስለሚችለው ጥቃትና ይከሰታል ስለሚባለው ጦርነት አስረድቷል፡፡

የሕወሓት ዳግም ጥቃት የሚጨበጥ ሥጋት ነው ከሚሉ ወገኖች በተጨማሪ፣ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዓምደኞች በተለያዩ ግንባሮች ሕወሓት ጦርነት ከፈተ የሚሉ ሰበር ዜናዎች እያቀረቡ ነው፡፡ እስካሁን መጠነ ሰፊ ጦርነት ወይም ግጭት መጀመሩን የሚያስረግጡ ኦፊሴላዊ መረጃዎች ከመንግሥትም ሆነ ከገለልተኛ ወገን ማግኘት ባይቻልም፣ ነገር ግን የሦስቱ ተጎራባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ የግጭት ሥጋት አይሎባቸዋል የሚለው ግምት ሚዛን ደፊ ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚሁ ከሕወሓት ዳግም ጦርነት ሥጋት ጎን ለጎን ደግሞ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ኃይሎች አሠላለፍ ሌላ ዓይነት ውዝግብ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ከሰሞኑ በባህር ዳር ከተማ በተሰናዳው በህልውና ዘመቻው ለተሳተፉ ወገኖች ዕውቅና የመስጠት መርሐ ግብር፣ በተለይ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ አደረጃጀት ለመከፋፈል የተወጠነ ሴራ አድርገው አንዳንዶች ሲያቀርቡት ታይተዋል፡፡ በሌላም በኩል የግጭት ሥጋት ካለባቸው አካባቢዎች የአማራ ልዩ ኃይልና የፋኖ አደረጃጀቶች እንዲለቁ መደረጉን በመጥቀስ፣ አሁን ከሕወሓት ጦርነት እኩል የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ኃይል ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የጠነሰሱት ሴራ ነው በማለት አንዳንድ ወገኖች ግምታቸውን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

‹‹ከራያ ቆቦና ከሰቆጣ ግንባር አካባቢዎች ልዩ ኃይሉንና ፋኖውን አስለቅቆ መከላከያው ቦታውን የያዘበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን መከላከያ ከልዩ ኃይሉና ከፋኖው ጋር ተናቦ እንደሚሠራ አውቃለሁ፡፡ አንዳንድ በፋኖ ስም ከተማ የሚያስጨንቁና መሣሪያ ይዘው ብቻ የሚያውደለድሉ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ መታረም ያለበት ነው፡፡ ፋኖ፣ ልዩ ኃይሉም ሆነ መከላከያ አሁንም ቢሆን ስንቅና ትጥቅ እየተካፈሉ በጋራ እንደሚሠሩ አውቃለሁ፡፡ የጦር ወይም የወታደራዊ ሥራውን ለባለሙያዎቹ መተው ነው የሚሻለው፡፡ መከላከያ ኃይሉም ሆነ ልዩ ኃይሉና ፋኖው አሠላለፋቸውን ተናበው ይወስናሉ ብዬ ነው የማስበው፤›› በማለት ሲሳይ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ በእሳቸው እምነት አሁን ፋኖውን ለማጥቃት ሴራ አለ ወይም የአማራ ክልልን ለማበጣበጥ እየተሠራ ነው የሚለው ወሬ ያልተጨበጠ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከባህር ዳሩ የሽልማት ሥነ ሥርዓት እየተመለሰ መሆኑን በስልክ የተናገረው የወልዲያው ፋኖ ቴዎድሮስ፣ ተመሳሳይ ሐሳብ ያነሳል፡፡ መንግሥት ዕውቅና መስጠቱን ተገቢ ነው ሲል የገለጸው ቴዎድሮስ፣ ዕውቅናውም ሁሉንም ያካተተና ያለ አድልኦ የተካሄደ እንደነበር በአካል ተገኝቶ ጭምር መታዘቡን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ አንዳንዴ ከፊት ተሠለፍ ሲባል እኔን ግንባር አድርገው ሊያስበሉኝ የሚል ይኖራል፡፡ አንዳንዴ ከጀርባ ሲያሠልፉት የእኔን ድልና ጀግንነቴን ሊነጥቁኝ የሚል ስሜት ይፈጠራል፡፡ ይህን ዓይነት ቅሬታ የሚቀርበው ወታደራዊ አሠላለፍና የጦር አደረጃጀትን ካለማወቅ ነው፡፡ አሁን  እከሌ ከግንባር ውጣ ተባለ በሚል የሚቀርበው ወሬ ምንጩ ይህን ካለመረዳት ሊሆን ይችላል ሲል ቴዎድሮስ ያስረዳል፡፡

‹‹እኔ አልተሸለምኩም፣ ነገር ግን መጠራቴና ዝግጅቱን በአካል መካፈሌ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ዕውቅና ይሰጥ እያልኩ ስጮህ ነበር፡፡ ደግሞም ይህን ዕድል በዓይን ያላዩ ብዙ የተሰው ጓዶች አሉ፡፡ ካልተሸለምኩ ብዬ ግን አላኮርፍም፡፡ እኔ የማኮርፈው ሕወሓት አራት ኪሎ ስትገባ ነው፤›› በማለት ቴዎድሮስ ይናገራል፡፡ አሁን በፋኖ፣ በመከላከያም ሆነ በመንግሥት መካከል ክፍፍል የሚፈጥሩ ወገኖች የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንጂ፣ በተጨባጭ በመሬት ላይ ያለውን ሀቅ ተመርኩዘው አለመሆኑን ነው የተናገረው፡፡       

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገመግሙ ወገኖች ብዙኃኑ የሕወሓት ጦርነት አይቀሬ መሆኑን ሚዛን በሚደፋ መንገድ ያስረዳሉ፡፡ በፋኖ አደረጃጀት ዙሪያ የሚነሳው ውዝግብ ተባብሶ አማራ ክልልን ወደ ጦርነት ሊከት ይችላል የሚለውን ሥጋት የሚያወሱ ቢኖሩም፣ ይህ የሚሆንበት ዕድል የጠበበ መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ፡፡

ኅትመት ልንገባ ስንል የአማራ ክልል መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት እንዲሁም የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በተናጠል ባወጡት መግለጫ፣ የአማራ ሕዝብና መላው ኢትዮጵያውያን የሕወሓትን ዳግም ወረራ ለመመከት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -