Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዋጋ ንረት የተሸበበው የፋሲካ በዓል ገበያ

በዋጋ ንረት የተሸበበው የፋሲካ በዓል ገበያ

ቀን:

በሔለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው

ረዥሙን ሠልፍ የያዙ እናቶች በብስጭት ያጉረመርማሉ፡፡ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደተሠለፉ፣ እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት ወረፋው እንዳልደረሳቸው በመከፋት ይናገራሉ፡፡

ልጅ ያዘሉ፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካሞችና ሌሎችም ተሠልፈው ተራቸውን የሚጠባበቁ ሲሆን፣ የሸማቾች ሱቁ በሰዓት ባለመከፈቱና ለምሳ ሰዓት ረዥም ጊዜ በመውሰዳቸው ሠልፉ ሊጓተት እንደቻለ ይጠቁማሉ፡፡

የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት በሚገኘው የሸማቾች ኅብረት ሱቅ የተሠለፉት ከመቶ ያላነሱ እናቶች ናቸው፡፡ ሦስት ሊትር የሚረጋ ዘይት በ298 ብር ለመግዛት ተራቸውን የሚጠብቁ ሲሆን፣ በየሱቆች የሚገኘውን ፈሳሽ ዘይት ገዝቶ የመጠቀም አቅም እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡

ሪፖርተር በሥፍራው ያጋጠመውን ችግር ለመጠየቅ ጥረት ቢያደርግም፣ ‹‹በሥራ ምክንያት›› በሚል ሰበብ የሸማቾች ሱቅ ሠራተኞች ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም፡፡

የፋሲካ በዓል የገበያ ቅኝት በሾላ፣ በሳሪስ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በቄራ በወፍ በረር የቃኘው የዝግጅት ክፍላችን በአንዳንድ ሸማቾች በር ላይ እንደተመለከተው ወረፋ ዓይነት በገበያ ሥፍራዎች አልገጠመውም፡፡ ይልቁንም፣ ከዓምናው አንፃር በአሁኑ በዓል ሸማቹ እምብዛም ገበያ ውስጥ እየተጋፋ እንዳልሆነ ታዝቧል፡፡

የዘንድሮው የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳዔ በዓል ገበያ፣ አገሪቷ ከገጠሟት ችግሮች ጋር ተዳምሮ ዋጋቸው ሰማይ የነኩ ግብዓቶች መኖራቸውን ተመልክቷል፡፡ ለበዓል ከሚሸመቱ ግብዓቶች መካከል ዋጋው የናረው ቅቤ ተጠቃሽ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ ሾላ ገበያ ቅቤ በመሸጥ አሥራ አራት ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ፣ ሥለ በዓል ገበያው እንዲህ ይላሉ፡፡ የሸኖ ቅቤ በኪሎ 850 ብር፣ የጎጃም ለጋ ቅቤ በ700 ብር፣ መካከለኛው 650 ብር እና በሳል የሚባለው በ600 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

አቶ ቴዎድሮስ እንደተናገሩት፣ የበዓል ገበያው ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር በአንድ ኪሎ ላይ የ270 እና ከዚያ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህም አምስት ኪሎና ከዚያ በላይ ቅቤ ይሸምቱ የነበሩት ደንበኞች ሁለትና አንድ ኪሎ እየገዙ ነው፡፡

በተለይም አንድና ግማሽ ኪሎ ገዝተው ይጠቀሙ የነበሩ ደንበኞቹ ከእነ አካቴው መግዛት እንዳልቻሉ ያስረዱት አቶ ቴዎድሮስ፣ ማኅበረሰቡ የመግዛት አቅሙ በእጅጉ የተፈተነበት ወቅት እንደሆነ መታዘባቸውን ይገልጻሉ፡፡

በንግድ ሥራ ውስጥ ረዥም ዓመታት ያስቆጠሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከዓመት ዓመት ዋጋቸው የሚጨምር እንጂ የሚቀንሱ ነገሮች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡ በሾላ ገበያ በዶሮ ንግድ አራት ዓመታት የሆነው ወጣት ይታገሱ ተስፋዬ እንደተናገረው፣ ከወላይታና ከሌሎች አካባቢዎች ከ200 በላይ ዶሮዎችን ገዝቷል፡፡

ዋጋቸው የወላይታ ከ800 ብር እስከ 850 ብርና ከዚያ በላይ፣ የሐበሻ የሚባሉትን ደግሞ ከ700 ብር ጀምሮ እየሸጣቸው እንደሚገኝ ከዓምና የትንሳዔ ገበያ የገበያ ሁኔታው ብዙም የዋጋ ጭማሪ እንደሌለ ጠቁሟል፡፡

የሐበሻ ቀይ ሽንኩርት ከ70 ብር፣ እስከ 75 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት የተፈለፈለው በ60 ብር፣ ድፍኑ ደግሞ በኪሎ 65 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የ2013 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት የሐበሻ ሽንኩርት ገበያ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ የ35 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ለመታዘብ ችለናል፡፡

በዚሁ ገበያ ኮረሪማ በኪሎ ከ120 ብር እስከ 150 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ፣ ጥቁር ቅመምና ሌሎች የቅመም ዓይነቶች የዋጋ ጭማሪ አንደሌላቸው ተመልክተናል፡፡ ሾላ ገበያ በርበሬ በረንዳ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያመጧቸውን በርበሬ ለገበያ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ፀዳሌና ጎጃሞ ይገኙበታል፡፡

የፀዳሌ በርበሬ በኪሎ ከ270 ብር ጀምሮ ከጎጃም የመጣውን ደግሞ ከ250 ብር ጀምሮ እንደሚሸጥ ዓይተናል፡፡ በትንሳዔ በዓል በብዙ ኢትዮጵያውያን ቤት የሚፈለጉ ግብዓቶች ዶሮና ዕንቁላል ናቸው፡፡ በዚሁ ገበያ ዕንቁላል ከዓምናው የበዓል ገበያ ብዙም ጭማሪ አላሳየም፡፡ የሐበሻው ስምንት ብርና የፈረንጁ ዕንቁላል ደግሞ ሰባት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተሸጠ እንደሆነ ዓይተናል፡፡

ከወላይታ፣ ጊንጪ፣ ወሊሶና ዱበር አካባቢዎች በጎችን እያመጣ የሚሸጠው አቶ አስቻለው ታደለ፣ የትራንስፖርት፣ የመኖና ሌሎች ወጪዎች ጋር ተዳምሮ ዋጋቸው ከፍ እንዳለ ተናግሯል፡፡

በጎቹን ከሚያመጣባቸው አካባቢዎች ሲገዛም ዋጋቸው ከፍ ያሉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አስቻለው፣ ትልቁ የሚባለው 13 ሺሕና ከዚያ በላይ፣ መካከለኛ 7,000 እና ከዚያ በላይ ትንሽ የሚባለው በግ ደግሞ 5,000 ብር እንደሚሸጡ ገልጸዋል፡፡ የፍየል ዋጋ  ከአምስት ሺሕ ብር ጀምሮ እየተሸጠ እንደሚገኝ በገበያው ለማየት ችለናል፡፡

ሪፖርተር በሳሪስና በንፋስ ስልክ ላፍቶ አካባቢ ባደረገው የገበያ ቅኝት አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ36 ብር እስከ 40 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ የሐበሻ ሽንኩርት የሚባለው ደግሞ አንድ ኪሎ ከ70 ብር እስከ 80 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ነጭ ሽንኩርት አንድ ኪሎ ከ50 ብር እስከ 60 ብር ሸኖ ቅቤ አንድ ኪሎ ከ800 ብር ጀምሮ እየተሸጠ እንደሆነ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አብዛኛው ሸማች የአቅሙን ያህል እየተገበያየ ቢሆንም፣ በፊት ከነበረው በዓል ጋር ሲነፃፀር ብዙዎቹ ሸማቾች ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ የገበያው ሁኔታ መቀዛቀዝ ታይቶበታል፡፡ የቅቤ ነጋዴም ወ/ሮ ብርሌ ደግፈውም ገበያ መቀዛቀዙን ነግረውናል፡፡

ወ/ሮ ብርሌ በቅቤ ንግድ ከተሰማሩ ሰባት ዓመታት ማስቆጠራቸውን ከተለያዩ ቦታዎች ቅቤ እያመጡ እንደሚሸጡ ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮ የትንሳዔ በዓል አብዛኛው ማኅበረሰብ የመግዛት ፍላጎት እንደሌለውና የቅቤ ዋጋም ከዓምናው በዓል ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አለው ብለዋል፡፡

አምስት ሊትር ዘይት ከ950 ብር እስከ 1,000 ሺሕ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ሪፖርተር ቦታው ላይ ተገኝቶ ማየት ችሏል፡፡ ከሸማቾች የሚወጣው አምስት ሊትር ዘይት ከ450 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የሐበሻ ዶሮ ከ650 እስከ 900 ብር፣ ክልስ ወይም በተለምዶ የፈረንጅ ዶሮ የሚባለው ከ500 እስከ 800 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

የሐበሻ ዕንቁላል በዘጠኝ ብር ከሃምሳ ሳንቲ እየተሸጠ ሲሆን፣ ፈረንጅ ዕንቁላል ደግሞ በዘጠኝ ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

መካከለኛ በግ ከአምስት ሺሕ ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑን የሚናገረው አቶ አሳምነው ፀጋዬ ነው፡፡ በንግድ ሥራው ከአሥር ዓመት በላይ ያስቆጠረው አቶ አሳምነው፣ የበግም ሆነ የፍየል ዋጋ ከዓምናው በዓል ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ጨምሯል፡፡ አቅሙ ያለው ሰው አንደ አቅሙ እየገዛ መሆኑንና አብዛኛው ሸማች ግን እያማረረ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡ ፍየል ከ6,500 ጀምሮ እየተሸጠ እንደሆነ ሪፖርተር በቦታው ሆኖ ተመልክቷል፡፡

የበገሬ ገበያ

በቄራ አካባቢ በሬ ውድ መሆኑን አይተናል፡፡ ለአብነትም አንድ በሬ ከ35 ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር እየተሸጠ ነው፡፡

የበሬ ዋጋ ለምን ናረ? ብለን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቁም እንስሳት የሚመጡባቸው አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱ የቁም እንስሳት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ በአንድ የቁም እንስሳት ላይ 10 ሺሕ ብር ድረስ መጨመሩን፣ አንዳንድ የልኳንዳ ቤት ነጋዴዎችም ወደ ተለያዩ ክልሎች ሄደው ከብት ለመግዛት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

የቁም እንስሳት ዋጋ ጭማሪ መታየት የጀመረው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዓብይ ፆምን ሲቀበሉ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ2005 ዓ.ም. ያወጣውና የተሻሻለው መመርያ የልኳንዳ ነጋዴዎች የታክስ መጠንና ተጨማሪ እሴት ታክስ አሰባሰብ በሌላ በኩል ነጋዴዎችን እያማረረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የወጣው መመርያ ልኳንዳ ቤቶች በሚሸጡት ወይም በሚሰጡት አገልግሎት ሳይሆን፣ ልኳንዳ ቤቱ በመንገድ ዳር ወይም ወደ ውስጥ ገብቶ ይገኛልን በሚልና በግምት መሆኑ፣ ይህም አብዛኛውን የልኳንዳ ቤት ነጋዴ ከሥራ የሚያወጣ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የልኳንዳ ቤት ችግሮችን በተመለከተ ማኅበሩ ለአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ማኅራት ምክር ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ ማቅረቡንም፣ ይሁን እንጂ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ አቶ አየለ አክለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ሸማቾች የበዓል ግብይታቸው መቀዛቀዙን፣ በተለይም የተለያዩ ግብዓቶች ላይ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ብዙም እየሸማመቱ እንዳልሆኑ ታዝበናል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...