Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የጤና መረጃ አስተዳደር የት ያደርሳል?

አወቀ ምሥጋናው (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ ጤና በሦስተኛ ዲግሪ፣ በመቀጠልም ወደ አሜሪካ አቅንተው ሲያትል ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን በበሽታዎች ጫናና ምጣኔ ጥናት በድህረ ፒኤችዲ ተመርቀዋል፡፡ በሥራ ዓለምም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርቶች በሕክምና፣ በመምህርነትና የጤና ፕሮግራሞችን በመሥራትና በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፣ ቅመራና ትንተና ማዕከል አማካሪ ናቸው፡፡ በማዕከሉና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጤና ነክ መረጃዎች ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ዶ/ር አወቀ፡- በተለያዩ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ውስጥ ለተለያዩ ዓላማ የሚሰበሰቡ ጤናና ጤና ነክ መረጃዎች በአግባቡ አይያዙም፡፡ ላለፉት ዓመታት የተሰበሰቡት መረጃዎቸ የት ነው የሚገኙት? ቢባል መልሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደሚታወቀው መረጃ ከነዳጅ እኩል የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለሆነም ባለፈው ዓመት የተሰበሰቡ መረጃዎች ዘመኑን በዋጀ የሳይንስ ጥበብና ሥልት ተመሳክረውና ተተንትነው ባለፉት ዘመናት ከየት ተነስተን የት ደረስን? የሚለውን እንዲነግሩን የዛሬን እንዲያሳዩን፣ የነገን ደግሞ እንዲተነብዩልን በሚያስችል መልኩ ተደራጅተው መቀመጥ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ መሠረተ ሐሳብ በመነሳት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፣ ቅመራና ትንተና ማዕከል ተቋቁሟል፡፡ ማዕከሉ ከተቋቋመ አምስት ዓመታት ሆኖታል፡፡

ሪፖርተር፡- የማዕከሉን አደረጃጀትና አወቃቀር በተመለከተ አጠር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ዶ/ር አወቀ፡- ማዕከሉ አራት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው ዘመናዊ የመረጃ ማከማቻና ማደራጃ ክፍል ሲሆን፣ ይህም ክፍል በሰው ኃይል የተደራጀና የሥራ ዝርዝር አውጥቶ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ሁለተኛው ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡ መረጃዎችን የማጠናከርና የመተንተን ሥራ የሚያከናውን ክፍል ነው፡፡ ይህም በጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉትን ማስረጃዎች ተንትኖና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማስረጃን ከማቅረቡም ባሻገር በሰው ኃይል በጣም የተደራጀና ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የሚሠራ ነው፡፡ ሦስተኛው ክፍል የጤና ሚኒስቴርና የአጋር ድርጅቶችን የመረጃ ፍላጎትና ዓይነት ያጠናል፡፡ የጥናትና የትንተና ውጤቶች ሥራ ላይ መዋላቸውን ያረገግጣል፡፡ አራተኛው ክፍል የሥራ ድርሻ የበሽታዎችን ጫናና ምጣኔ ያጠናል፡፡ በጤና አትላስ ዝግጅት ላይም ተሳትፏል፡፡ ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፣ ቅመራና ትንተና ማዕከል በአፍሪካ ብቸኛና በዓይነቱ የመጀመርያ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ማዕከል በቀሩት የአፍሪካ አገሮች እንዲዳረስ ጠንክረን እንሠራለን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በመተባበር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ጋር በቅርበት እየተጋገዝን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው የጤና አትላስ አስመርቃችኋል፡፡ ጤና አትላስ ምንድነው? በውስጡ ምን ነጥቦችን ያካትታል?

ዶ/ር አወቀ፡- ጤና አትላስ ሰፊና ጥልቅ ከሆነ ትንታኔ ለጤና ዘርፍ ቀለል ባለ መንገድ ለውሳኔ እንዲያግዝና በዋናነትም ለማስተማሪያነት እንዲጠቅም ተብሎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በውስጡም አምስት ምዕራፎችን አካቷል፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ በማኅበረሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ትምህርትንና ኢኮኖሚን ከጤና መለኪያዎች ጋር በማጣመር የተሠራውን ትንታኔ፣ የሞትና የውልደት ምጣኔን የያዘ ነው፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2019 ያሉትን የሞትና የአካል ጉዳት መንስዔዎች፣ በአገርና በክልል ደረጃ በፆታና በዕድሜ አካቷል፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ የጤና እክል አጋላጭ መንስዔዎች የሚያደርሱትን የአካል ጉዳትም ሆነ የሞት ምጣኔ ያመላክታል፡፡ አራኛው ምዕራፍ አማካይ በሕይወት የመኖር ዘመን በአገርና በክልል ደረጃ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ቁልፍ መለኪያ ተብለው የተቀመጡትን ጥናትና ውጤት በተደራጀ መልክ አካቷል፡፡ አምስተኛው ምዕራፍ ጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ሁለተኛውን የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕላን መለኪያዎች እስከ ውጤታቸው በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰዎች በተለያዩ  በሽታዎች ወይም አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ከሚጻፉ ቃላቶች መካከል በተወለደ በዘህ ዓመቱ/ዓመቷ በሕክምና ሲረዳ/ስትረዳ ከቆየ/ከቆየች በኋላ አርፏል/አርፋለች የሚል ነው እንጂ ለሞት የዳረገው በሽታ ሲገለጽ አይስተዋልም፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ዶ/ር አወቀ፡- ሰዎች በተለያየ የዕድሜ ደረጃ፣ በተለያየ በሽታ ወይም አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፣  ይሞታሉ፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የሞተበት ምክንያት በበሽታም ከሆነ የበሽታው ወይም የአደጋው ዓይነት በሐኪሞች ተረጋግጦ ሠርተፊኬት አይሰጥም፡፡ በሌሎች ያደጉ አገሮች ለእያንዳንዱ ሰው የሞተበት ምክንያት ይሠራለታል፣ ሠርተፊኬትም ይሰጣል፡፡ ሰርተፊኬት ካልተያዘ መቅበር ሁሉ አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመጀመርያው አካባቢ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ተጀምሮ ነበር፡፡ ወደፊት ግን ይህ አሠራር በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ ኩነቶች ምዝገባ ጋር ተያይዞ የሞት መንስዔም ይመዘገባል የሚል እምነት አሳድሮብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሰዎችን የሞት መንስዔ እንዴት ይገልጹታል?

ዶ/ር አወቀ፡- ጥናቶች እንደሚሳዩት ከሆነ ተላላፊ በሽታዎች፣ ከእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ከምግብ ዕጥረት ጋር የተያያዙ በሽታዎች የሕመም መንስዔ ቢሆኑም፣ የሞት መንስዔ ከመሆን ቀንሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አማካይ ዕድሜ እንዲጨምር ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ አንደኛው ተላላፊ በሽታ ኤችአይቪ/ኤድስ ነው፡፡ በዚህ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነስ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልል አማካይ ዕድሜ እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ቲቢ በሽታ አልሚና የኃይል ሰጪ ምግብ እጥረት፣ ተቅማጥ፣ የሳንባ ኢንፌክሽን፣ ከእናቶች ምግብና ጨቅላ ሕፃናት ጋር ያሉ በሽታዎችና ሌሎችም የወረርሽኝ በሽታዎች በ60 በመቶና በ80 በመቶ የሞት መንስዔ ከመሆን በመቀነሳቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አማካይ የመኖር ዕድሜ እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከጨቅላ ሕፃናት ጋር የተያያዙ በሽታዎች ግን የታሰበውን ያህል አልቀነሱም፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና አደጋዎች ካለመቀነሳቸው ጋር ተያይዞም መኖር ያለብንን አማካይ ዕድሜ ቀንሰውብናል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደ አገር የታየው አማካይ የዕድሜ መጨመር በክልሎችስ እንዴት ይታያል?

ዶ/ር አወቀ፡- እንደ አገር ዕድሜ በ22 ዓመታት ጨምሯል፡፡ ለዚህም ጥናት ብዙ የመረጃ ምንጮችን እንጠቀማለን/ተጠቅመናል፡፡ ክልሎችን በተመለከተ ግን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እ.ኤ.አ. በ1980 36 የነበረው፣ በእ.ኤ.አ. 2019 64፣ አፋር ከ37 ወደ 64፣ አማራ ከ46 ወደ 69፣ ድሬዳዋ ከ46 ወደ 70፣ ጋምቤላ ከ44 ወደ 68፣ ኦሮሚያ ከ45 ወደ 70፣ ትግራይ ከ42 ወደ 70፣ ሶማሌ ከ50 ወደ 65፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከ43 ወደ 67፣ ሐረሪ ከ41 ወደ 69 እና አዲስ አበባ ከ56 ወደ 71 ዓመታት ከፍ ብሏል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፣ ቅመራና ትንተና ማዕከልን ለማቋቋም ያነሳሳችሁ ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር አወቀ፡- አሜሪካ ሲያትል አካባቢ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን በሥሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ታዋቂ የሆነ ኢንስቲትዩት ፎር ሔልዝ ሜትሪክ ኤንድ ኢቫሉዌሽን የሚባል ተቋም አለ፡፡ ይህ ግዙፍ ተቋም ከሚያካሂዳቸው ጥናቶች መካከል አንዱና ዋነኛው በዓለም የበሽታዎች ጫናና ምጣኔ ወይም ግሎባል በርደን ኦፍ ዲዚዝ የሚለው ነው፡፡ እኔም በዚህ ጥናት ውስጥ ተሳታፊ እንድሆን ዕድሉ ገጠመኝ፡፡ በጥናቱ ውስጥ የእኔ ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮቸ ስትራቴጂ ማዘጋጀት ነበር፡፡ ስትራቴጂውም በቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ተቀባይነት አገኘ፡፡ ይህም ሆኖ ግን በቅድሚያ ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመር አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት፡፡ በዚህም የተነሳ ከስትራቴጂው ተነስቼ ለኢትዮጵያ ይስማማል ብዬ ያመንኩበትን ፕሮጀክት ቀረፅኩ፡፡ ፕሮጀክቱም በኢትዮጵያ ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፣ ቅመራና ትንተና ማዕከልን በማቋቋም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይህንንም ፕሮጀክት በተለያዩ ወቅቶች ለነበሩት የጤና ሚኒስትሮች አቅርቤ እንዲጠናና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ የሚሆኑበት ውይይት እንዲካሄድበት ተደረገ፡፡ በዚህም የተነሳ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና በኢትዮጵያ የቢል ኤንድ ቢልንዳ ጌት ፋውንዴሽን ተጠሪ ያሉበትና እኔም የኢንስቲትዩት ፎር ሔልዝ ሜትሪክ ኤንድ ኢቫሉዌሽን በመወከል ስብሰባ ተካሄዶ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ውይይትና የሐሳብ ልውውጥ ተደረገበት፡፡ በመጨረሻም ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ዕውን እንዲሆነ ተቀባይነትን አገኘ፡፡  

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱ አተገባበር በምን መልክ ነው?

ዶ/ር አወቀ፡- በመጀመርያ በኢትዮጵያ የኅብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በጤና ሚኒስቴርና በኢንስቲትዩት ፎር ሔልዝ ሜትሪክ ኤንድ ኢቫሉዌሽን መካከል የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ለሥራውም መከናወን ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ፋውንዴሽን የ12 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገልን፡፡ ከዚህም ገንዘብ ውስጥ 6.2 ሚሊዮን ዶላር ለኢንስቲትዩት ፎር ሔልዝ ሜትሪክ ኤንድ ኢቫሉዌሽን፣ የቀረው 5.8 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተሰጠ፡፡ ለሁለቱም ተቋማት የተሰጠው ገንዘብ ለፕሮጀክቱ ትግበራና ለማዕከሉ ማቋቋሚያ እንዲውል ለማድረግ ነው፡፡ እኔም የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ በመምራት ሥራውን ተያያዝነው፡፡ በዚህም ከሚቋቋመው ማዕከል ጋር የተያያዘ የአሥር ዓመታት የሥራ መመርያ አዘጋጀን፡፡ ፕሮጀክቱን የመገምገም አቅም ያላቸው ስምንት ባለሙያዎች የተሳተፉበት ግብረ ኃይል ተቋቋመ፡፡ ግምገማው ከተጠናቀቀ በኋላ ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፣ ቅመራና ትንተና ማዕከል ተቋቋመ፡፡ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችና በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች ያበረከቱት ዕገዛና ትብብር ለማዕከሉ በፍጥነት መቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ብልጽግና ፈተና ሆነውብኛል ያላቸውን አምስት ተግዳሮቶች ይፋ አድርጎ የአግዙኝ ጥሪ አቀረበ

ብልፅግና በነፃነት ስም በሚፈጸም ወንጀል ምክንያት በትግሉ ያገኘውን ነፃነት...

ዋሊያዎቹ ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸለሙ

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 11 ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት ተበረከተለት፡፡

መንግሥት ከጦርነቱ ለማገገም በመጭዎቹ አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል አለ

በጦርነቱ የተሳተፉ 250 ሺሕ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ ኅብረተሰቡ...

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...