Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹አይፍረሱ!›› - ያልተቋረጠው የቅርስ ባላደራው ድምፅ

‹‹አይፍረሱ!›› – ያልተቋረጠው የቅርስ ባላደራው ድምፅ

ቀን:

‹‹ሚያዝያ 10 የዓለም የቅርስ ቀን እንደሆነ ያውቃሉ?››

በዓለም የሚኖሩ ሰዎች በየቀኑ ማንነታቸውንና የትመጣቸውን በሚያሳይ መልኩ ሕይወታቸውን በመምራት ባህላዊ ቅርሶቻቸውን ያከብራሉ፡፡ በመሆኑም ዓለም ሁሉ ነው በዓመት አንዷን ቀን በተለየ አገባብ የሰው ልጆችን የጋራ ታሪክና ቅርስ ለማክበር  የሚዘጋጀው፡፡ ለዚህም ነው ሉላዊው የባህል ተቋም ዩኔስኮ የዓለምን የቅርስ ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 10 ቀን (አፕሪል 18) እንዲከበር የደነገገው፡፡

የቀኑን ፋይዳ ዩኔስኮ ሲያብራራ ‹‹የዓለም ቅርስ ቀን ሁሉንም የዓለም ባህሎች እንድናከብርና ጠቃሚ ስለሆኑ ሐውልቶችና ባህላዊ ቦታዎች ግንዛቤን እንድናገኝ፣ እንዲሁም የዓለምን ባህሎች የመጠበቅን አስፈላጊነት እንድንሰንቅ ያበረታታናል፤›› ሲል አስምሮበታል፡፡

በምሕፃሩ ‹‹አይኮሞስ›› ተብሎ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የመታሰቢያ ሐውልቶችና መካነ ቅርሶች ምክር ቤት፣ በቱኒዝያ ሚያዝያ 10 ቀን 1974 ዓ.ም. ባካሄደው ሲምፖዚየም ‹‹ዓለም አቀፍ የሐውልቶችና ቦታዎች ቀን›› በዓለም ዙሪያ እንዲከበር ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ነው፣ ዩኔስኮ በጠቅላላ ጉባዔው በኅዳር 1976 ዓ.ም. ይሁንታ የሰጠው፡፡ በዘልማድም ዕለቱ ‹‹የዓለም ቅርስ ቀን›› ተብሎም በታካይነት ተጠርቷል፡፡

የአይኮሞስ ምክር ቤት የዓለም ቅርስ ቀንን እንዴት ማክበር እንደሚቻልም በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሐውልቶችንና መካነ ቅርሶችን፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን (ሪስቶሬሽን) ያለ ክፍያ መጎብኘት ቀዳሚ ነው፡፡ ቀኑን በተመለከተ መጣጥፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ማውጣት እንዲሁም በቴሌቪዥንና ሬዲዮ ማሠራጨት፣ ኅብረተሰቡ ለባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስገነዝቡ ባነሮችን (የጽሑፍ ሰሌዳዎችን) በከተሞች አደባባዮች ወይም ትራፊክ በሚጨናነቅባቸው አካባቢዎች መስቀል፣ ሌሎቹ ተግባሮች ናቸው፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችን ያካተቱ ውይይቶችን በባህል ማዕከላት፣ በከተማ ማዘጋጃ ቤቶችና በሕዝባዊ አደባባዮች ማደራጀት የበዓሉ ተጠቃሾች ናቸው ያለው ምክር ቤቱ እንዲሁም የፎቶና የሥዕል፣ የቪዲዮ ወዘተ ዓውደ ርዕይ፣ የመጻሕፍት፣ መጽሔት፣ የፖስት ካርድ፣ ፖስተሮች ኅትመት፣ የባህል ቅርሶችን ከመጠበቅና ከማስተዋወቅ አንፃር የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጀቶች ወይም ግለሰቦች ወይም በርዕሰ ጉዳዩ ዙርያ የተዋጣላቸው ጽሑፎችን ያዘጋጁትን መሸለም፣ በቅርብ የታደሰ ሐውልትን መመረቅ ዓይነተኛ የቀኑ መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ በተለይ በትምህርት ቤቶች ለልጆችና ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ልዩ ልዩ ተግባራትን ማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር ዘርፈ ብዙ ትስስር መፍጠርን የዓለም የቅርስ ቀን የሚታሰብባቸው ናቸው፡፡

ቀኑን ያላስታወሰችው ኢትዮጵያ

የዘንድሮው የዓለም ቅርስ ቀን መሪ ቃል ‹‹ቅርስና የአየር ንብረት›› (ሄሪቴጅ ኤንድ ክላይሜት) ሆኖ በተለያዩ አገሮች በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል፡፡  በዓሉ ከተከበረባቸው አገሮች አንዷ በዩኔስኮ ስምንት ቅርሶች ያስመዘገበችው ግብፅ ናት፡፡ የአገሪቱ የቱሪዝምና አንቲካ (ጥንታዊ ቅርስ) ሚኒስቴር ቀኑን ያከበረው በግብፅ ሥልጣኔ ብሔራዊ ሙዚየም 10 ሚኒስትሮችና የ53 አገሮች አምባሳደሮች ከባለቤቶቻቸው ጋር እንዲገኙ በማድረግ ነው፡፡ ታዳሚዎቹ በባህል ሚኒስቴር አማካይነት የቀረበላቸውን የግብፃውያንን ፎክሎር (ባህላዊ ኩነት) ተመልክተዋል፡፡

ዘጠኝ ቅርሶችን ባስመዘገበችው በኢትዮጵያ ግን የሚመለከተው ግንባር ቀደም ተቋም በቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር የተመደበው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቀኑን በአርምሞ ማለፉን ከግቢው ድባብ መረዳት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር ከቅጥር ግቢው ተገኝቶ እንደታዘበው ዕለቱን የሚያስታውሱ ማስታወቂያዎችም ሆኑ ሠሌዳዎች (ባነሮች) አልተሰቀሉም፡፡ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች በስልክ ለማግኘት የተደረገ ጥረትም አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ ዕለቱን አስመልክቶ መንግሥታዊ ያልሆነው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር (ኢቅባማ) በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ‹‹Happy Heritage Day!!!›› (መልካም የቅርስ ቀን) በማለት መልዕክቱን ከመሪው ቃል አንፃር ሲያስተላልፍ፣ ቅርሶች ይጠበቁ በማለትም ጭምር ነው፡፡

ዓምና ይኸው የዓለም የቅርስ ቀን ‹‹የባህል ብዝኃነትና የጋራ ቅርሶችን መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት›› በሚል በዓል ከቅርስ ባለ አደራ ማኅበር ጋር በእግር ጉዞ፣ በጉብኝትና ‹‹መሠረተ ልማትና ቅርስ›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ለሦስት ቀናት ያከበረው የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ዘንድሮ ግን ድምፁ አልተሰማም፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት የቅርስ ባለ አደራ ማኅበር (ኢቅባማ) ‹‹ለቅርሶቻችን ድምፅ በመሆን እንታደጋቸው!›› የሚል በማሳሰቢያ የታጀበ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ በቅርስነት የተዘመገቡ የጥንቱን ኪነ ሕንፃ የሚያስታውሱ ቤቶች ሲፈርሱ፣ ሲደረመሱ ታይተዋል፡፡ ‹‹አንድ ይባል›› እያሉ ድምፃቸውን ያሰሙ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦችን ከቁብ የቆጠረ ባለመኖሩ ደብዛቸው መጥፋታቸው የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡

ኢቅባማ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳመለከተው፡- ‹‹በከተማችን አዲስ አበባ በቅርስነት ከተመዘገቡ በርካታ ቁጥር ካላቸው ቅርሶች መካከል ሰባቱ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ እነዚህም የከተማዪቱን አዲስ አበባ ምሥረታና ጥንታዊነት አጉልተው የሚያሳዩ ታሪክን በጉያቸው የታቀፉ አንበሳ መድኃኒት ቤት፣ የራስ ናደው አባ ወሎ ቤት፣ የተክለ ማርያም ባሻ ቤት፣ የደጃዝማች ሊበን ቤት እንዲሁም የቀድሞ ዓድዋ እና ጣይቱ ሆቴል ተያይዘው የተሠሩ ቤቶች ናቸው፡፡››

ማኅበሩ እነዚህ ቅርሶች ከመፍረሳቸው በፊት የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ‹‹ድምፃችንን በማሰማት የድርሻችንን እንወጣ፤›› ሲል በአፅንዖት አሳስቧል፡፡

የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ እየሠራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር የሦስት አሠርታት ዕድሜን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው በቅርስነት የተመዘገበውን የራስ ከበደ መንገሻ ነባር ቤትን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ1996 ዓ.ም. ተረክቦ ታሪካዊ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ ጥገና በማድረግ በጽሕፈት ቤትነት እየተገለገለበት ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአዲስ አበባ የዘመን አሻራን የያዙ የተወሰኑ ታሪካዊ ቤቶች በየዘመኑ ከመኖር ወደ አለመኖር እየተቀየሩ ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የሻቃ በልሁ ቤት (ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የነበረ)፣ የደጃዝማች ብሩ ኃይለ ማርያም ቤት (ከጣሊያን ትምህርት ቤት ጀርባ የነበረ)፣ ራስ ናደው ከሠሯቸው ቤቶች አንዱ (ከሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ጀርባ የነበረ)፣ የወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ቤት (ልደታ አካባቢ የነበረ) እና ሌሎችም ጥንታዊ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ ጥንታዊ ሕንፃዎች በ‹‹ልማት›› ስም ከመፍረስ የታደጋቸውም የደረሰላቸውም መንግሥታዊ ተቋም የለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...