የአዋሽ ባንክ ጠቅላላ ሀብት በ2014 የሒሳብ ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ በ50 ቢሊዮን ብር በመጨመር ከ165 ቢሊዮን ብር በላይ ማደጉ ተገለጸ።
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም በተገለጸው የዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከ126 ቢሊዮን ብር በላይ ማደጉ ታውቋል።
የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን በተመለከተ ከባንኩ የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በሒሳብ ዓመቱ በዘጠኝ ወራት የደረሰበት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀደሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ነው፡፡
ባንኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሰጠው የብድር መጠንም በ33 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የሚያመላክተው የባንኩ መረጃ፣ ይህም የባንኩን አጠቃላይ የብድር ክምችት ከ112 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሶታል፡፡
ይህ አፈጻጸሙ አሁንም ባንኩ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል ባንኮች ቀዳሚውን ደረጃ ይዞ መቀጠሉን የሚያመላክት መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡ የባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት (ኤልሲ ማርጅንን ጨምሮ) 107.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡
እንደ ባንኩ መረጃ በተከፈለ ካፒታል መጠንም ከግል ባንኮች ከፍተኛ የሚባለውን የካፒታል መጠን የያዘ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ የሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተከፈለ የካፒታል መጠኑ 10.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመላክቷል፡፡
አጠቃላይ የባንኩ ቅርንጫፎች ብዛት 710 መድረሱን የሚገለጸው የባንኩ መረጃ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 177 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈታቸውን ያመለክታል። ባንኩ ለተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበው ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ተቋማት ዕውቅና እያስገኘለት መሆኑም ተገልጿል፡፡ መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው ግሎባል ፋይናንስ የተባለ መጽሔት አዋሽ ባንክን ‹‹ከኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ›› ብሎ ሰሞኑን መሰየሙም በማሳያነት ቀርቧል።
አዋሽ ባንክ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ ለውጦች እየተከሰቱ በመሆኑ ወደፊት የሚጠበቀውን ከፍተኛ ፉክክር ለመወጣት ለቀጣይ አምስት ዓመት አዲስ ስትራቴጂ በመቅረፅ ለመተግበር መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ይህንንም ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ትግበራ ለማስገባት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ማኬንዚ የተባለውን የአሜሪካ ኩባንያ መርጧል፡፡ ማኬንዚ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሪፎርም ለማድረግና በአዲስ አሠራር እንዲጓዝ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ለመቅረፅ የወጣውን ጨረታ አሸናፊ ሆኖ ውል በመግባት የማመከር ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ተጨማሪ መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የሚታየው ለውጥ አዋሽ ባንክን አዲስ ስትራቴጂ እንዲቀርፅ አነሳስቶታል ብለዋል። ባንኩ እየተከሰቱ ላሉ ለውጦች ዝግጁት ማድረግ እንደሚገባው በባንኩ ቦርድ ታምኖበት ጭምር ዓለም አቀፍ ኩባንያ እንዲመረጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መንግሥት ሊፈቅድ እንደሚችል መገለጹ፣ እንዲሁም የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ላይ የውጭ ኩባንያዎች መግባት፣ ፊንቴኮች የባንክ ሥራ እንዲሠሩ መፈቀዱና የመሳሰሉ አዳዲስ ክስተቶች መታየት በፋይናንስ ዘርፉ ብርቱ ፉክክር የሚፈጥር በመሆኑ አዋሽ ባንክ በዚህ ልዩ ክስተት ውስጥ ብቁ ሆኖ ለማለፍ የሚያስችለውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ መቅረፅ እንዳስፈለገው የባንከ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።
ቀጣዩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ባንኩ በኢትዮጵያ ሳይወሰን በምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ውስጥ እንዲገባና በአጠቃላይ አገልግሎቱ በቀጣናው የተሻለ ባንክ ሆኖ ነጥሮ እንዲወጣ የሚያስችል እንደሚሆን አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡
ከ15 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት አዋሽ ባንክ ከማኬንዚ ጋር የሚደረገው የሥራ ስምምነት በቅርቡ የሚፈረም መሆኑም ታውቋል፡፡