Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዋጋ ንረቱና የትንሳዔ በዓል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት አንስቶ በተለይም ዘንድሮ በበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች ውስጥ እያሳለፈች የምትገኝ አገር መሆኗ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡ ከሁሉ ችግሮች ይልቅ የአገሬውን ሕዝብ ሰቅዞ የያዘው ጉዳይ ቢኖር ከድጡ ወደ ማጡ እየተንደረደረ የሚገኘው የዋጋ ንረትና ያንን ተከትሎ የተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ነው፡፡

‹‹የዳቦ ቅርጫት›› የሚል ስያሜ ሲሰጣት በቆየችው አገር የምግብ ነክ ምርቶች ዋጋ ንረት ማየል ከጀመረ ሰነባብቷል ብቻ ሳይሆን የከረመ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የብዙኃኑ ነዋሪ የአብሮነትና የጋራ ማኅበራዊ ዕሴት ማንፀባረቂያ የሆነው የትንሳዔ  በዓል በመጪው እሑድ ይከበራል፡፡ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት የሸማቾች የመግዛት አቅም በተፈተነበት በዚህ ወቅት የሚከበረው የትንሳዔ በዓል ምን መልክ ይኖረዋል? የሚለውን ጉዳይ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ሪፖርተር ባደረገው የከተማዋ ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ቅኝት እንዲሁም ካነጋገራቸው የተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት እንደተረዳው፣ በተለይም የዘንድሮው የትንሳዔ በዓል በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ቀውሶች ሳቢያ በተፈጠረው የምግብ ዋጋ ንረት ውስጥ የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡ ተካፍሎ መብላት አንዱ የበዓሉ ልዩ ገፅታ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ካላቸው ላይ ሲያካፍሉ የቆዩ ዜጎች ዛሬ እነሱም በተራቸው የሰውን ድርጎ የሚሹ ሆነው እንደተገኙ ያነጋገርናቸው ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ የገበያው ዋጋ በራሱ ቀደም ካሉት ጋር ሲነፃፀር ያለምንም አስረጅ ይህንኑ ፍንተው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

በቀላል ንፅፅር ለመመልከት ያህል ዓምና በተከበረው የትንሳዔ በዓል ላይ ሪፖርተር ባደረገው የገበያ ቅኝት፣ ለአብነት ያህል በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ እስከ 390 ብር ይሸጥ የነበረው አምስት ሊትር ዘይት በ2014 ዓ.ም. የትንሳዔ በዓል መዳረሻ ገበያ 900 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ የምግብ ዓይነት ላይ የ510 ብልጫ ያለው ዋጋ ሲቆረጥ ሸማቹ ምን ዓይነት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ መረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በመስከረም ወር ሪፖርተር ባደረገው የገበያ ቅኝት ዘይት ከ550 እስከ 620 ብር ሲሸጥ እንደነበር መገለጹ የቅርብ ጊዜ ማስረጃ ነው፡፡

የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ የሸማቾች የመግዛት አቅም እንዳደከመውና ከዚህ በፊት ወደ የተለያዩ የግብይት ሥፍራዎች ለሸመታ የሚሄዱ ሰዎች ከሚጠይቁት የመግዛት መጠን በግማሽ ቀንሰው መገበያየት እንደጀመሩ ቸርቻሪዎችና ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡

በሳሪስ አካባቢ ለሚኖሩት አቶ ሰማኸኝ አለነ ይህ የሰሞነ ሕማማት ወቅት በየዓመቱ የሰፈራቸው አድባርም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ያስለመዱትን የቅርጫ መቃረጥ ተግባር ለመከወን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው ለዕርድ የሚሆነውን መሳሪያ የሚያዘጋጁበት ነበር፡፡ ስድስት መደብ በሚከፋፈለው ቅርጫ ግማሽ መደብ የሚገቡ አቅማቸው ደከም ያሉ ነዋሪዎችን ጨምሮ ለአንድ የቅርጫ መደብ እስካለፈው የገና በዓል ድረስ ስድስት ሺሕ ብር ያስከፍሉ ነበር፡፡ ይህ ክፍያ የዕርድ ባለሙያ ክፍያን ጨምሮ እስከ ዕርድ ማድመቂያ የሆነው የአበሻ አረቄ ወጪ የሚሸፍን ነው፡፡ ብዙም ባልራቀ ጊዜ በወርኃ መስከረም አቶ ሰማኸኝ በመደብ አምስት ሺሕ ብር ያስከፍሉ ነበር፡፡ የመስከረም ወር በምሳሌነት የተነሳው የቅርብ ጊዜ ዋጋን ለማሳየት እንጂ ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት የነበረውን የቅርጫ ዋጋ ማንሳት በራሱ አስፈሪ ስለሆነ መተው የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አቶ ሰማኸኝ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሰማኸኝ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት በቀጥታ የቅርጫ ገንዘቡን ከመሰብሰባቸው በፊት፣ በተለያየ መንገድ የሰሙትን የከብት ዋጋ ማሻቀብ ለማረጋገጥ ከሁለት ባልንጀራዎቻቸው ጋር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ካራ የሠንጋ ገበያ አቅንተው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አቶ ሰማኸኝ በካራ ገበያ ከዚህ ቀደም ይገዙት የነበረውን መካከለኛ መጠን ያለው ሠንጋ ተከራክሮ መግዛት የሚችል ሰው ከ50 ሺሕ ብር በታች ማግኘት እንደማይችል ይናገራሉ፡፡ ይህንን ገንዘብ ሌሎች ወጪዎች ሳይደመሩ በቀጥታ ለአንድ ሰው ቢሰላ የሚደርስበት ወጪ በመደብ ከ8,300 ብር በላይ ነው፡፡ ይህንን ዋጋ መቋቋም የሚችል ተቃራጭ እንደሌለ ቅድሚያ መረዳታቸውን የሚገልጹት አቶ ሰማኸኝ፣ በዚህም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት በቋሚነት ሲከውኑ የቆዩትን የኅብረት ዕርድ በዘንድሮ ትንሳዔ በዓል ላለማድረግ ከውሳኔ ላይ እንደደረሱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኑሮ ውድነት የዋጋ መጨመርና የሸማች የገቢ መጠን መዳከም በአንድ ላይ ሲፈጠሩ የሚመጣ ችግር እንደሆነ የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ ለአብነትም ለበዓል ወቅት ሽንኩርት በገፍና በርካሽ ቢቀርብ የሽንኩርትን ዋጋ መጨመር እንዳይከሰት ያግዛል እንጂ ዓመታዊ የምግብ ነክ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ የሚረዳ እንዳልሆነ ያሰምሩበታል። ምክንያቱም ይህ የሽንኩርት አቅርቦትና ዋጋ ቢያንስ ለረዥም ወራት በተመሳሳይ ሆኖ መቀጠል ስላለበት ነው።

መጪውን የፋሲካና የዒድ አልፈጥር በዓላትን ታሳቢ በማድረግ ለበዓላቱ የሚያስፈልጉ የፍጆታ ምርቶች በሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መቅረብ መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር፡፡ በእነዚህ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የፍጆታ ዕቃዎች መቅረባቸው ይነስም ይብዛ በድህነት ወለል ውስጥ ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል አንድ አማራጭ ቢሆንም፣ ነገር ግን በሸማቾች ሱቅ በኩል የሚቀርቡትን ግብዓቶች መግዛት የማይችሉ ነዋሪዎች ቁጥር አጅግ በጣም በርካታ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በሾላ ገበያ የበዓል ግርግሩ ከመፋፋሙ በፊት የአቅማቸውን ሸምተው ለመመለስ የወጡትን በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቸሬ ሰፈር ነዋሪ የሆኑትን ወ/ሮ ተናኘ ሪፖርተር አናግሯቸው ነበር፡፡ በጡረታ የሚያገኙት ወርኃዊ ገቢ ከ3,200 ብር እንደማይበልጥ የተናገሩት ወይዘሮዋ፣ ከዚህ ቀደም በዓል ሲደርስ ይደጉሟቸው የነበሩት ልጆቻቸው ዘንድሮ እጆቻቸው እንዳጠረባቸው ገልጸዋል፡፡ በቅርጫ ሥጋ አሊያም መለስተኛ በሆነ የፍየል ሙክት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲያከብሩ የኖሩትን የትንሳዔ በዓል፣ ዘንድሮ በለስ ከቀናቸው ዶሮ ብቻ አርደው በዓሉን ለማሳለፍ ወደ ገበያ እንደወጡ አስረድተዋል፡፡ ከእርሳቸው አቅም ትንሽም ቢሆን የተሻለ ገቢ ያላቸው ጎረቤታቸው ያገኙትን ዘይት እንዳካፈሏቸው የተናገሩት ወ/ሮ ተናኘ፣ ቂቤ ከ900 እስከ 1,000 ብር መግባቱን በሰሙ ጊዜ ላለመግዛት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ወ/ሮ ተናኘ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ በዓላት ከእርሳቸው አነስ ያለ ገቢ ያላቸውን ጎረቤቶቻቸውን ካላቸው ወይም ልጆቻቸው ከደጎሟቸው የበዓል መዋያ ጥሪት ላይ ያካፍሉ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ግን ራሳቸው በሰው ድጎማ ማደር መጀማራቸው እንደሚያብሰከስካቸው ይገልጻሉ፡፡ 

ዶሮ በአዲስ አበባ የተለያዩ ገበያዎች ከ800 እስከ 950 ብር፣ የሐበሻ ቀይ ሽንኩርት ከ70 እስከ 75 ብር፣ ቂቤ እንደየሚመጣበት አካባቢ ልዩነት ከ800 እስከ 1,000 ብር፣ በግ ከ5,000 ብር እስከ 13 ሺሕና ከዚያ በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ሪፖርተር በገበያ ቅኝቱ ለመታዘብ ችሏል፡፡

ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወ/ሮ ታደሉ ገብሬ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጎፋ ገብርኤል አካባቢ አንድ ደሳሳ ጎጆ በ2,000 ብር ተከራይታ ያለ አባት ከምታሳድገው የስምንት ዓመት ወንድ ልጇ ጋር ትኖራለች፡፡ በየሰው ቤት በመሄድ ተመላላሽ የልብስ ማጠብ ሥራ የዕለት ጉርሷን ለምትደጉመው እንስት፣ ሸምታ መብላት የተራራ ያህል አቀበት ሆኖባታል። የዕለት ጉርሷን በግዢ ካደረገች ውላ ማደሯን ትናገራለች፡፡ እንኳንስ የበዓል ቀን ደርሶ የዘወትር ኑሮዋ ጉልበቷን አፍሳ ለማደር እንኳ እንዳላስቻላት ትናገራለች፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩትን የገና እና የአዲስ ዓመት በዓላት በአካባቢዋ የሚኖሩ በጎ አድራጊ ወጣቶች ተባብረው ለእሷና መሰል ነዋሪዎች ባደረጉት የዶሮ፣ ዘይትና ሌሎች የበዓል መዋያ ድጋፎች እንዳከበረችው የተናገረችው ወ/ሮ ታደሉ፣ መሰል ደጋግ እጆች ካልተዘረጉላት የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ፉርኖ ዱቄት እንኳን ገዝታና ዳቦ ጋግራ የምትውልበት ዕለት እንደማይሆን ተናግራለች፡፡

ሸማቾች እንደተናገሩት ከሆነ ከዚህ ቀደም ከአንዱ ገበያ ሌላኛው ይሻላል በማለት መርካቶና ሌሎች ገበያዎችን ይቃኙ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት ሁሉም ገበያዎች በሚባል መልኩ የሚቆረጠው የሸቀጦች ዋጋ ተመሳሳይ ነው፡፡

ወርኃዊ ደመወዝተኛው ምንም ዓይነት የደመወዝ ጭማሪ ወይም ማሻሻያ ባልተደረገለት፣ የግል ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የዕለት ጉርሳቸውን የሚገፉ ዜጎች  በሥራ መቀዛቀዝ ሳቢያ በተጋረጠባቸው ከሥራ የመቀነስ ሥጋት፣ የሸቀጦች ዋጋ በቅርብ ወራት ውስጥ ዕጥፍና ከዚያ በላይ በጨመረበት ወርኃ ሚያዚያ የሚከበረው የዘንድሮ የትንሳዔ በዓል ገበያ የሸማቹን ዘንቢል ጎዶሎውን የሚመልስ እንደሆነ ሪፖርተር ካዳረገው የገበያና ሸማቾች ቅኝት ለመታዘብ ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች