Tuesday, March 28, 2023

ለአፋርና አማራ ክልሎች ተጎጂዎች በአንድ ማዕከል ድጋፍ አለመሰጠቱ ያስነሳው ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የቁጥጥር ዳሰሳ ሪፖርት ብዙ አዳዲስ ግኝቶችን ይዞ መጥቷል፡፡ በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነት የወደሙ አካባቢዎች ላይ የሚካሄዱ የረድዔት አቅርቦት ሥራዎችን የገመገመው የቁጥጥር ሪፖርቱ፣ በሁለቱ ክልሎች ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በአንድ ማዕከል ማስተባበር አለመቻሉና በተበጣጠሰ መንገድ መሆኑ እንደሚያሳስበው ነው ያስታወቀው፡፡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም በዚህ የቁጥጥር ዳሰሳ ሪፖርቱ በአፋርና በአማራ ክልሎች ከሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት ሥራዎች በተጨማሪ፣ የደረሱ ውድመቶችንና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችንም በሰፊው ይፋ አድርጓል፡፡ ከአስገድዶ መድፈር እስከ ንብረት ውድመትና የሥነ ልቦና ጉዳቶች ድረስ በአኃዝ የተደገፈ መረጃን ይፋ ያደረገው ተቋሙ፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳቱ ተገቢ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ምክረ ሐሳብ ለግሷል፡፡

በሌላም በኩል በአማራ ክልል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች ተጠልለው ይገኛሉ የሚለው ሪፖርቱ፣ የፌዴራል መንግሥት ለእነዚህ ወገኖች በቂና ተገቢ ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑም እንደሚያሳስበው ነው ያስታወቀው፡፡ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች ወጥነት ያለው የረድዔት አቅርቦት ለማካሄድ የሚያስችል ሥርዓትም ሆነ አንድ ማዕከል አለመገንባቱ ችግር መሆኑን ያመለከተው የተቋሙ ሪፖርት፣ በዚህ ላይ ደግሞ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮሚያ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ለተጠለሉ ዜጎች በፌዴራል ደረጃ ድጋፍ አለመደረጉ ትልቅ ክፍተት ሆኖ እንዳገኘው ያስረዳል፡፡

በአማራና በአፋር ክልሎች የሚታየውን የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት አንደኛ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው የሚለው ሪፖርቱ በአግባቡ፣ በዕቅድና በበጀት የተደገፈ ሥራ እየተሠራ አለመሆኑንም ይፋ አድርጓል፡፡ በጦርነትና በግጭቶች የተፈናቀሉ የሁለቱ ክልሎች ዜጎች በተለይ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለማግኘት እንኳ እየተቸገሩ ይገኛሉ የሚለው ሪፖርቱ፣ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል ሲል ነው ያስቀመጠው፡፡  ‹‹የፍትሕ አካላት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡ ባንኮችና የፋይናንስ አገልግሎቶች በቅጡ ሥራ አልጀመሩም፡፡ ስልክና ትራንስፖርት የመሳሰሉ አገልግሎቶችም ተቋርጠዋል፤›› የሚለው ሪፖርቱ፣ መሠረታዊ አገልግሎት መስጫዎች በአብዛኛው ተዘግተዋል በማለት የሁለቱ ክልሎች የጦርነት ተጎጂ የሆኑ ሕዝቦች የተጋፈጡትን በእጅጉ ፈታኝ ያለውን ሁኔታ በዝርዝር ያትታል፡፡

የሪፖርቱ ጥቅል ይዘቶች

የዳሰሳ ቁጥጥሩ አጠቃላይ ዓላማ በአማራና በአፋር ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች በግጭት ለተጎዱ ወገኖች እየቀረበ ያለውን መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥና በመልሶ ግንባታ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን መለየት መሆኑን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ አፋጣኝ የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መፍትሔ ማመላከት፣  ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች እየቀረበ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍና የመሠረተ ልማት አገልግሎትም ተመልክቻለሁ የሚለው ሪፖርቱ፣ በዚህ በኩል አሉ የሚላቸውን በጎና ጎጂ ጎኖች ዘርዝሮ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

ቁጥጥሩ ዳሰሳው የተካሄደባቸውን ቦታዎች ሲያመላክት ደግሞ በባለሙያዎች የተደራጀ አራት የዳሰሳ ቡድኖችን በማደራጀት አንዱ ቡድን ወደ አፋር ክልል በሐውሲና ፈንቲ ዞኖች ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡ ቀሪዎቹን ሦስት ቡድኖች ደግሞ ወደ አማራ ክልል በመላክ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ ሰሜን ጎንደርና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ እንዲሁም ሰሜን ወሎና ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞኖች ተሰማርተው ዳሰሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከመጋቢት 14 እስከ ሚያዝያ 3 ቀን በ2014 ዓ.ም. በተካሄደው ዳሰሳ፣ በአጠቃላይ በሁለቱ ክልሎች ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ የባህር ዳርና የሰመራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንዲሳተፉ ተደርጓል ተብሏል፡፡

የክልልና ፌዴራል ቢሮዎች፣ በየዕርከኑ ያሉ ሠራተኞችና ተገልጋዮች ጋር ቃለ መጠይቅና የቡድን ውይይት በዳሰሳው ተካሂዷል ይላል አዲሱ የዕንባ ጠባቂ ተቋም የቁጥጥር ሪፖርት ጉዳት በደረሰባቸው ተቋማት፣ እንዲሁም የመልሶ ማቋቋሙ ሒደት በተጀመረባቸው ቦታዎችና ተቋማት ላይ ምልከታ ተካሂዷል ሲልም ያስታውቃል፡፡ ከተጎጂዎች ማለትም በጦርነቱ ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ካሉ ተፈናቃይ ዜጎች ጋር ውይይትና ያሉበት ሁኔታ ምልከታ መደረጉንና የሰነዶች፣ የፎቶግራፍና የኦዲዮ ቪዡዋል መረጃዎች ተሰብስበዋል ይላል፡፡

የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና  ተቋማት፣ የአደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያዎች፣ የሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤቶች፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤቶች፣ የግብርና ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ተቋማት፣ ውኃና መብራት አቅራቢ ድርጅቶች፣ ባንኮችና ሆቴሎች፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ልማት መሥሪያ ቤቶች፣ የባህልና ቱሪዝም መሥሪያ ቤቶች በየዘርፉ ተፈትሸዋል በማለትም መረጃው የተጠናቀረበትን መንገድ ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

በአማራ ክልል የደረሱ ጉዳቶች

በተለያዩ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና ቋሚ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች በአጠቃላይ 1,855,823 መሆናቸውን ሪፖርቱ ያስቀምጣል፡፡ በተለይ የመደፈርና የፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች ሲያስቀምጥ፣ በሰሜን ጎንደር 56፣ ደቡብ ጎንደር 89፣ ሰሜን ወሎ 548፣ ዋግ ኽምራ 111፣ ደቡብ ወሎ 342፣ ሰሜን ሸዋ 119፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ስምንት ሰዎች መደፈራቸውን ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡ በድምሩ ከ1,217 በላይ ሴቶች፣ እናቶች፣ ልጃገረዶችና አረጋዊያን ጭምር ተደፍረዋል ይላል፡፡ የመደፈር ወንጀሉ የተፈጸመባቸው ወገኖች ከስምንት ዓመት ልጃገረድ ጀምሮ እስከ አረጋዊ የዕድሜ ክልል ያሉ፣ እንዲሁም ፆታቸው ወንዶች ጭምር የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ሪፖርቱ ያትታል፡፡  

ወላጆቻቸውን ያጡ ታዳጊዎችን በሚመለከት በደቡብ ወሎ 700 ሁለቱንም ቤተሰብ፣ 853 አንድ ቤተሰብ አጥተዋል ሲል፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ 52 ከቤተሰብ የተለያዩ ናቸው በማለት ያስቀምጣል፡፡ በሰሜን ሸዋ 113 ሕፃናት፣ ሰሜን ጎንደር 4,587 ወላጆቻቸውን ያጡ ናቸው በማለትም በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታ ያትታል፡፡

በሞት ሕይወታቸውን ያጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አኃዝ ሲዘረዝር ደግሞ ደቡብ ወሎ 548፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር 297፣ በሰሜን ሸዋ 134 ዜጎች ናቸው ይላል፡፡

አካል ጉዳተኛ የሆኑ ዜጎችን በተመለከተ ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን 213 ሕፃናት፣  በሰሜን ጎንደር 784፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ 402፣ በሰሜን ወሎ 75 ሰዎች አካል ጉዳተኞች ሆነዋል በማለት ያስቀምጣል፡፡

ሰብዓዊ ብቻ ሳይሆን ቁሳዊ ውድመቶችንም ለመዘርዘር የሚሞክረው ሪፖርቱ፣ በአማራ ክልል በሚገኙ የመንግሥት፣ የግል፣ የሕዝብ ተቋማትና ንብረቶች፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የከፋ ጥፋት ደርሷል ሲል ያስቀምጣል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆናል በማለት አንዳንድ የውድመት አኃዞችን ተቋሙ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በሰሜን ወሎ በትምህርት ዘርፍ የደረሰውን ጉዳት ለመሸፈን ብቻ 13,729,514,650 ብር ያስፈልጋል በማለት የጉዳቱን ከፍተኛነት ያመላክታል፡፡ በጎንደር ዞኖች በአጠቃላይ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን ለመጠገን 28,056,950 ብር እንደሚያስፈልግ፣ እንዲሁም ሰሜን ወሎ 149,517,620 ውድመት በትምህርት ላይ ደርሷል የሚለው ሪፖርቱ የሰሜን ሸዋ የትምህርት ዘርፍ ኪሳራን ደግሞ 127 ሚሊዮን ብር ይገመታል በማለት ያስረዳል፡፡

በጤና ተቋማት ውድመት በኩል ደግሞ ማሳያ ተደርገው ከተቀመጡ አኃዞች መካከል በሰሜን ጎንደር ዞን 138,206,433 ብር ግምት ያለው ውድመት አጋጥሟል የሚል መረጃ ይገኝበታል፡፡ በሰሜን ወሎ 3,904,629,151 ብር ግምት ያለው የጤና ተቋማት ውድመት ማጋጠሙን ተቋሙ ያስቀምጣል፡፡ በዋግ ኽምራ 126 ጤና ተቋማትና ሦስት ሆስፒታሎች ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል ወይም ተቃጥለዋል፡፡ በደቡብ ወሎ በጥቅሉ 506 ጤና ተቋማት የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ፣ ከዚህ ውስጥ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው 253 ጤና ኬላዎች 70 ጤና ጣቢያዎችና ሰባት ሆስፒታሎች ናቸው የወደሙት ይላል፡፡ ሰሜን ሸዋ 470,805,705 ብር ግምት ያለው ውድመት በጤና ተቋማት ላይ ደርሷል በማትም ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ደግሞ በሁሉም ዘርፍ የደረሰው የጉዳት መጠን ሲጠቃለል ከ47,635,889,425 ብር በላይ እንደሚሆን፣ በተሰበሰቡ ግርድፍ መረጃዎች ማረጋገጥ መቻሉን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው፡፡

በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኩል ደግሞ በአማራ ክልል የቁጥጥር ዳሰሳው በተደረገባቸው ዞኖች የግብርና ተቋማት፣ የፖሊስ ተቋማት፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ባንኮች፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሰጪዎች፣  ፍርድ ቤቶች፣ የውኃ ተቋማት፣ መብራት፣ ስልክ  መስመሮች፣ ድልድዮች፣ የኮሙዩኒኬሽን አውታሮችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በሙሉና በከፊል ወድመዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ ከወደሙት በተጨማሪ አውቶሞቢሎችና ሌሎች መገልገያዎች መዘረፋቸውንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡

አፋር ክልል ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቁጥጥር ዳሰሳው በተለይ በአፋር ክልል ያገኛቸውን የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች ሲያስቀምጥ፣ በአጠቃላይ በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና ተፈናቅለው ወደ መኖርያ ቀዬአቸው የተመለሱ ወገኖች ቁጥር 645,518 ናቸው በማለት ይጠቅሳል፡፡

አሁን ከዞን ሁለት ከስድስት ወረዳዎች ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች 336,582  መሆናቸውን፣ ከእነዚህ መካከል 175 ሺሕ ሕፃናት እንደሆኑ፣ እንዲሁም 16,829 አራሶችና ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው በማለት የችግሩን ክብደት ይዘረዝራል፡፡  

ዳሰሳዊ ቁጥጥር በተካሄደባቸው የዞን አራት ወረዳዎች ውስጥ ደግሞ ከአንድ ወረዳ ተፈናቅለው፣ አሁን ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው የተመለሱ ዜጎች ቁጥር 172,602 መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል በማለት በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በሚመለከት ደግሞ የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ የወረዳ ዘርፍ መሥሪያ ቤት ሕንፃዎች፣ የግለሰብ ቤቶችና የእምነት ተቋማትን ጥቅል የውድመት ግምት ነው ሪፖርቱ በየዞኑ በመከፋፈል የሚያቀርበው፡፡ በዞን አንድ 220,165,698 ብር ደርሷል ያለው ሪፖርቱ፣ በዞን ሁለት ደግሞ 118,193,255 ብር ኪሳራ አጋጥሟል ይላል፡፡ በዞን አራት ደግሞ  304,339,920 ብር ውድመት ማጋጠሙን ሪፖርቱ ሲጠቅስ፣ በዞን አምስት ደግሞ 191,219,659 ብር ኪሳራ መድረሱን ነው ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው፡፡

በአጠቃላይ በአፋር ክልል በመሠረተ ልማትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት ሲያስቀምጥ፣ በድምሩ 833,918,532.8 ብር ኪሳራ በጦርነቱ መድረሱን ነው የዕንባ ጠባቂ ተቋም የቁጥጥር ዳሰሳ የሚያመላክተው ፡፡

በሪፖርቱ ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎች

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አዲስ ሪፖርት በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥና መልሶ ማቋቋም ጉዳይን የተመለከተ መሆኑን ተቋሙ በግልጽ አመላክቷል፡፡ ተቋሙ የዜጎች ፍላጎትን በጥቂቱም ቢሆን ያሟላ አገልግሎት ለጦርነቱ ሰለባዎች እየቀረበ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ፣ በሁለቱ ክልሎች በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የቁጥጥር ዳሰሳ በማድረግ ሪፖርቱን ማዘጋጀቱንም ይፋ አድርጓል፡፡

የዚህን ሪፖርት አንኳር ይዘት ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በኤልያና ሆቴል በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ ያደረጉት የተቋሙ አመራሮችም፣ የዳሰሳ ቁጥጥሩ ሪፖርት ከመደበኛ ጥናት ሪፖርት የሚለይበትን ምክንያት ተጠይቀው ነበር፡፡ ስለዚሁ ምላሽ የሰጡት በተቋሙ የአስተዳደር በደል ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ፣ ቁጥጥር ከመደበኛ ጥናት እንደሚለይ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህ ቁጥጥር ነው፣ የመደበኛ ጥናት ሳይንሳዊ ዘዴዎችን አይከተልም፡፡ ተቋሙ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በፈለገው ዘዴ፣ በፈለገው ተቋምና ቦታ ተገኝቶ በባለሙያዎች ቁጥጥር ያደርጋል፤›› በማለት ነው የሁለቱን ልዩነት ያስረዱት፡፡

አቶ አዳነ ተቋማቸው የቁጥጥር ዳሰሳውን በመደበኛነት በባለሙያዎች ማካሄዱን ሲያስረዱ ከኢኮኖሚ፣ ከሕግ፣ ከአስተዳደርና ከሶሺዮሎጂ ጀምሮ በቂ የትምህርት ዝግጅትና የሙያ ልምድ ባላቸው ሰዎች ቁጥጥሩን ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡ በሁለቱ ክልሎች ደርሰዋል ካሏቸው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች በተጨማሪ፣ በርካታ የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል ሲሉ በአኃዝ አስደግፈው ያቀረቡት አቶ አዳነ፣ ‹‹ጉዳቱን የማከምና መልሶ የማቋቋሙ ሥራ በመንግሥት ብቻ ተሠርቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በየዘርፉ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል፤›› ሲሉ ነው የችግሩን አሳሳቢነት የጠቆሙት፡፡

በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ በተለይ በአማራ ክልል ዞኖች የደረሱ ጉዳቶችን በሰፊው ያቀረቡት በተቋሙ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ ታሪኳ፣ እስካሁን የሰብዓዊ ረድኤት ሥራውን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስተባብር ማዕከል መፍጠር አለመቻሉን ትልቅ ክፍተት የፈጠረ ችግር ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ብዙ አካባቢዎች ነፃ ከወጡ ቆይተዋል፡፡ በአንፃራዊነት የሰላም ሁኔታው መሻሻል አሳይቷል፡፡ ነገር ግን የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦቱን ለማስተባበር ወጥ የሆነ ማዕከልም ሆነ አሠራር መዘርጋት አለመቻሉ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ፍትሐዊ የረድዔት አቅርቦት ማዳረስም ሆነ የረድዔት አቅርቦቱን ተገቢነት በቅጡ መከታተል አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲሉ ነው ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ ያስረዱት፡፡

በአማራ ክልል በጦርነት ከተፈናቀሉ ተጎጂዎች በተጨማሪም፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮሚያ ክልሎች ተፈናቅለው የተጠለሉ መኖራቸውን በመጥቀስም፣ ‹‹ለእነዚህ ዜጎች ግን የፌዴራል መንግሥቱ ሳይሆን ክልሉ ነው ድጋፍ እያቀረበ ያለው፤›› ብለዋል፡፡ በፌዴራል በኩል ለእነዚህ ዜጎች የተመደበ የዕርዳታ ኮታ መኖሩን የጠቀሱት ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ፣ ‹‹እያልን ያለነው ይህ በአግባቡ ይቅረብ ነው፤›› በማለት ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ለዘጠኝና ለአሥር ወራት መብራት ያላዩ ዜጎች በአፋርና በአማራ ክልሎች መኖራቸውን የተቋሙ አመራሮች በቁጥጥር ዳሰሳው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች መብራት፣ ውኃ፣ ስልክ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎት ሊሟላላቸው እንደሚገባ መጠየቃቸውንም አመራሮቹ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል፡፡ ይህ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት አለመሟላት ዜጎችን ለእንግልት ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ፣ ለፖለቲካዊና ለሰብዓዊ መብቶቻቸው ጥሰት እየዳረጋቸው ጭምር መሆኑን ነው የተቋሙ አመራሮች ጉዳዩን ገዘፍ ባለ መንገድ ለማስቀመጥ የሞከሩት፡፡ 

አገሪቱ አሁን ላይ ለተጎዱ ዜጎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለሟሟላት በምትችልበት አቅም ላይ ትገኛለች ወይ? እንዲሁም መንግሥት ለተጎጂዎች አጣዳፊ የመልሶ ግንባታ በማድረግ መሠረታዊ አገልግሎት ለዜጎች የማቅረቡን ሥራ ለመፈጸም ካልቻለ የሚወሰደው አማራጭ ምንድነው? ተብሎ ለቀረቡ ጥያቄዎች የተቋሙ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩልም ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች ሁኔታ፣ እንዲሁም አሁንም ከጦርነት ባልተላቀቁት በአፋርና በአማራ ክልሎች ስላለው ችግር ሪፖርቱ በቂ መረጃዎች አላቀረበም የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ፣ ‹‹ከአራት ወራት በላይ የረድዔት አቅርቦት እየተካሄደ መሆኑ ቢነገርም፣ ነገር ግን አቅርቦቱም ሆነ ፍትሐዊነቱ መሻሻል ያለበት ብዙ ጉድለት አለው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች እንዲሽሩ ለማድረግ ጉዳቱን የሚያስታውሱ የጦርነት ቅሪቶች በየቦታው አሉ፡፡ ጅምላ መቃብሮች፣ የወደሙ ንብረቶችና ጽሑፎች ጭምር በየቦታው ይታያሉ፤›› በማለት የተናገሩት ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ፣ እነዚህን ጉዳቶች ከመቅረፍ በተጨማሪ የጠፉ የቅርስ ሀብቶችን ማስመለስና የግብርና ግብዓቶችን ለተጎጂዎች ማድረስ ላይም ብዙ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ አገሪቱ በርካታ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችና ኃላፊነቶችን የተቀበለች መሆኗን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፣ ‹‹የዜጎች ጥያቄ በዚያ ደረጃ ተሄዶ ጭምር መንግሥት እንዲፈታ የማስገደድ ሥራ ሊሠራ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አዳነ በበኩላቸው፣ ‹‹በጦርነት ላይ ላሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ መሠራት አለበት፤›› ሲሉ ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት ሥራውም ሆነ መልሶ ግንባታው ብዙ ክፍተት እንደሚታይበት የዘረዘሩት አቶ አዳነ፣ ‹‹መልሶ ግንባታውንም ሆነ ዕርዳታና ድጋፉን በፌዴራል ደረጃ በአንድ ማዕከልና ቋት በኩል ቢካሄድ ሀብት አሰባስቦ የማዳረስ ሥራው እጅግ ውጤታማ እንደሚሆን በቁጥጥር ዳሰሳችን አረጋግጠናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህ የዳሰሳ ጥናት ነፃ በወጡና አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ብቻ መካሄዱን የጠቀሱት የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ወንድም በበኩላቸው፣ ነፃ ያልወጡ የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎችም ሆነ የትግራይ ክልል ጉዳይ አለመካተቱን አስረድተዋል፡፡ ‹‹መቀሌ ካለው ቅርንጫፋችን ጋር የነበረው የመጨረሻ ግንኙነታችን ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ የተደረገ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ግንኙነታችን ተቋርጧል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ዘውዱ፣ ሪፖርቱ ነፃ በወጡ የአፋርና የአማራ አካባቢዎች ብቻ የተደረገ የቁጥጥር ዳሰሳ መሆኑ እንዲወሰድ ነው ያሳሰቡት፡፡v

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -