Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

[ክቡር ሚኒስትሩ ሊጠይቃቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ከመጣ አንድ ካድሬ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የጀመሩት ጨዋታ አልመች ብሏቸዋል]

 • ለሕግ አስከባሪ ተቋማት የተደረገውን ገለጻ አዳመጡት ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ገለጻ? አልሰማሁም።
 • ስለአገሪቱ ፖለቲካዊ ክስተቶች ከኋላውም ከቅርቡም ተደርጎ ሰሞኑን ጥልቅ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
 • እንዴት አልሰማሁም?
 • ልብ ስላላሉ ይሆናል። በተለይም ከምርጫ በኋላ ስለተከሰቱ ጉዳዮች የተደረገው ገለጻ በጣም ገላጭ ነበር።
 • ስለምርጫ ምን ተባለ?
 • ምርጫ 97ን ተከትሎ ማኅበረሰቡ ድባቴ ውስጥ ገባ፡፡
 • እሺ በ2002 ምርጫስ?
 • ተብሰከሰከ።
 • ማን?
 • ማኅበረሰቡ!
 • ለምን?
 • ኢሕአዴግ ከሁለት የፓርላማ ወንበር በስተቀር ሁሉንም በማሸነፉ፣ ይኼ ነገር ምንድነው? ብሎ ማኅበረሰቡ ተብሰከሰከ፡፡
 • በ2007 ምርጫስ?
 • ተቆጣ!
 • ለምን?
 • ኢሕአዴግ የፓርላማውን ወንበር በሙሉ አሸነፈ ሲባል ማኅበረሰቡ ተቆጣ። ለውጡም ያኔ ነው የጀመረው ተብሏል።
 • በቀጣዩ ምርጫስ?
 • ቀጥሎ ስለነበረው ምርጫ ምንም አልተባለም።
 • ለምን?
 • ለምን እንደሆነ አልገባኝም።
 • ኦ… ገባኝ… ገባኝ!
 • ምኑ?
 • ቀጥሎ ስለነበረው ምርጫ ምንም ያልተባለበት ምክንያት።
 • ለምንድነው?
 • በኮቪድ ምክንያት ተራዝሞ ነበር።
 • እንደዚያ ከሆነ ካቆምንበት መቀጠል እንችላለን፡፡
 • ምን ላይ ነበር ያቆምነው?
 • ማኅበረሰቡ ድባቴ ውስጥ ገባ፣ ተብሰከሰከ፣ ቀጥሎ ተቆጣ ብለን ነበር።
 • እሺ በቀጣዩ ምርጫስ?
 • ማኅበረሰቡ አይምረንም!
 • ምን?
 • እርሶ እንዳሉት ማኅበረሰቡ አይምረንም!
 • ምንድነው የምታወራው? እኔ እንደዚያ ወጣኝ?!
 • ኧረ ለጨዋታ ያህል ነው ክቡር ሚኒስትር! ቀልዴን ነው።
 • ለጨዋታ እያላችሁ ነው የምታናክሱን!
 • የምታናክሱን?
 • አዎ። ለነገሩ ጥፉቱ የኔ ነው።
 • እንዴት?
 • ካድሬዎች ናቸው ማኅበረሰቡን የሚያጋጩት ሲባል እየሰማሁ አለመጠንቀቄ የራሴው ጥፋት ነው።
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ጨዋታውን አከረሩት?
 • አከረርኩት እንዴ?
 • እሺ ይተዉት… ሌላ ጨዋታ ብንጫወት ይሻላል።
 • ምኑን ተጫወትኩት!
 • ቅድም ወደዚህ ስመጣ አንድ ነገር አይቼ እንዴት አዘንኩ መሰሎት ?
 • ምን አይተህ ነው?
 • እዚህ መንገድ ላይ ያለው ኤምባሲ በር ላይ ወጣት የለ ጎልማሳ ተሠልፎ ዓይቼ ምንድነው ብዬ ጠየኩ…
 • እሺ?
 • ለውትድርና ምዝገባ ነው ሲሉኝ አዘንኩ።
 • ኤምባሲ ላይ ለውትድርና ምዝገባ?
 • እሱ እኮ ነው የሚገርመው። አገሩን በውትድርና እንዲያገለግል ጥሪ ሲደረግ እንዳልነበር ዛሬ የሰው አገር ወታደር ለመሆን ተሠልፎ ስመለከት አዘንኩ።
 • እውነት ነው። በጣም ያሳዝናል።
 • ለነገሩ ወጣቱስ ምን ማድረግ ይችላል? አገሩን በውትድርና እንዳያገለግልም እኮ በመንግሥት ኃላፊዎች ንግግር ተደናገረ?
 • እንዴት?
 • ሰሞኑን የተባለውን አልሰሙም?
 • ምን ተባለ?
 • ወታደሩ ሲኖር ጄኔራል ነው፣ ሲወጣ ደሃ ነው፡፡
 • እና ምን አገናኘው?
 • ወጣቱ ይህን እየሰማ እንዴት አድርጎ ሠራዊቱን ሊቀላቀል ይችላል?
 • ድጋሚ ልታስገባኝ? እኔ አላውቅም።
 • ምን አሉኝ?
 • እኔ የማውቀው ነገር የለም አልኩህ!
 • እንዴት?
 • ወንድሜ ከቤት ልትወጣልኝ ትችላለህ?
 • እ…
 • ውጣልኝ አልኩህ! እንዴት ያለ ካድሬ ነው የገጠመኝ?

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን የተፈቀደው ፍራንኮ ቫሉታ የውጭ ንግድ አተገባበር ያስገኘው ውጤት በየጊዜው እየተገመገመ እንዲቀርብ ባዘዙት መሠረት የመጀመሪያውን የግምገማ ሪፖርት እያዳመጡ ነው]

 • የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል በተፈቀደ በሳምንቱ በገበያው እየተስተዋለ ያለው ነገር አሳሳቢ ነው ክቡር ሚኒስትር።
 • ለምን አሳሳቢ ይሆናል? ጠቃሚነቱ ተጠንቶ አይደል እንዴ የተፈቀደው?
 • ቢሆንም ባደረግነው ግምገማ አዝማሚያው አሳሳቢ መሆኑን ነው ያስተዋልነው።
 • እስቲ አዝማሚያውን አቆይና ውጤቱን አቅርብ።
 • ጥሩ። በመጀመሪያ ቅኝታችን ትኩረት ያደረግነው ትይዩ ገበያው ላይ ነው።
 • እንዴ ለገበያውም ትይዩ መሠረቱ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ትይዩ ካቢኔ የመሠረቱት?
 • ኧረ ወዲህ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ወዴት?
 • የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ ማለቴ ነው።
 • ታዲያ ለምን ትይዩ ማለት አስፈለገህ?
 • በፋይናንስ ሙያ የተሰጠው ስያሜ እንደዚያ ስለሆነ ነው።
 • ቢሆንም የሚያደናግር ቃል መጠቀም ተገቢ አይደለም። ለማንኛውም ቀጥል።
 • ጥሩ። እንደገለጽኩት ፍራንኮ ቫሉታ መፈቀዱን ተከትሎ ትይዩ… ማለቴ ጥቁር ገበያው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
 • ከፍራንኮ ቫሉታ በኋላ ስንት ገባ?
 • በአንድ ጊዜ ከ68 ብር ወደ 74 ብር አሻቅቧል።
 • ቢያሻቅብም ማንም ጥቁር ገበያ ሄዶ ዶላሩን ስለማይመነዝር ችግር የለውም።
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ዶላር ያለው ሸቀጦችን እንዲያስመጣበት የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል ስላገኘ ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄድ አይኖርም።
 • ክቡር ሚኒስትር ተቃራኒው ነው እየሆነ ያለው።
 • እንዴት?
 • ዶላር ያለው ሸቀጥ ከማስመጣት ይልቅ ዶላሩን በጥቁር ገበያ እንዲሸጥ ነው የተመቻቸለት። እየሆነ ያለው በተቃራኒው ነው።
 • አልገባኝም?
 • የአገር ውስጥ አስመጪዎች በተፈቀደው የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል ሸቀጥ ለማስመጣት ከአገር ውስጥ ዶላር የማሰባሰብ ሥራ በስፋት ጀምረዋል። ለዚህ ነው የጥቁር ገበያው ዋጋ ባንዴ ያሻቀበው።
 • እኛ የፈቀድነው እኮ ከአገር ውጭ በሚገኝ የዶላር ምንጭ እንዲያስገቡ ነው።
 • ነው። ነገር ግን ሰብስበው ያስወጡታል። ሰሞኑንም የተያዙ አሉ።
 • ምን ሲያደርጉ?
 • በአንድ ጊዜ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ወደ ጅቡቲ ሊያስወጡ የሞከሩ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
 • ዶላር ከጥቁር ገበያ ሰብስበው?
 • በትክክል። ችግሩ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ሌላ ነገር አለ።
 • ምንድነው እሱ?
 • የሚያስመጡትን ሸቀጥ የሚቸረችሩት ደግሞ ዶላሩን ከጥቁር ገበያ በገዙበት ዋጋ ላይ ትርፍ አስልተው ስለሚሆን የታቀደው የዋጋ ማረጋጋት ዕቅድ አይሳካም።
 • ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ሆኗል በለኛ?
 • እንደዚያ ነው። በአንድ ጊዜ ባንክና በጥቁር ገበያው መካከል ከ17 ብር በላይ ነው ልዩነት የተፈጠረው።
 • ነገሩ ግን ጥሩ ዕድል እንዳለው ይታየኛል።
 • ምን ዓይነት ዕድል ሊኖር ይችላል ክቡር ሚኒስትር?
 • በባንክና በጥቅሩ ገበያው መካከል የተፈጠረውን ሰፊ ልዩነት የማጥበብ።
 • እንዴት ተደርጎ?
 • የብር ምንዛሪ ተመንን ዲቫሊዩ በማድረግ!
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎ። እንደውም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ዓይነት ዕድል ነው።
 • ሌላው ዕድል ምንድነው?
 • ከአይኤምኤፍ ለመታረቅ በር ይከፍታል።

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ አመሻሹን መኖሪያ ቤታቸው ሲደርሱ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈው የማዕከላዊ ኮሚቴ ገለጻ እየተከታተሉ አገኟቸውና አጠገባቸው ተቀምጠው የደረሱበትን አብረው መከታተል እንደጀመሩ፣ ባለቤታቸው ቴሌቪዥኑን ትተው መጠየቅ...

እኔ ምለው? እሺ... አንቺ የምትይው? የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አባላት እንዲያወሩ ወይም እንዲጠይቁ አይፈቀድም እንዴ? እንዴት ይከለከላል? ታዲያ ለምንድነው ፕሬዚዳንቱ ብቻ የሚያወሩት? እያወሩ አይደለም፣ ገለጻ እያደረጉ ነው። ቢሆንም አንድም አባል...

[ክቡር ሚኒስትሩ አምሽተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ‹‹ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን›› የሚለውን የቴሌቪዥን ዜና ተመልክተው ለብቻቸው ሲስቁ አገኟቸው]

ስልክ እያወራሽ ነበር እንዴ? ኧረ በጭራሽ... ምነው? ታዲያ ምንድነው ብቻሽን የሚያስቅሽ? አይ... በቴሌቪዥኑ የሚቀርበው ነገር ነዋ። ምንድነው? ድሮ ድሮ ዜና ለመስማት ነበር ቴሌቪዥን የምንከፍተው፡፡ አሁንስ? አሁንማ ቀልዱን ተያይዘውታል... አንተ ግን በደህናህ...

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ስልካቸው ጠራ። ደዋዩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊ እንደሆኑ ሲነገራቸው የስልኩን መነጋገሪያ ተቀበሉ]

ሃሎ፡፡ እንዴት አሉ ክቡር ሚኒስትር። ደህና ነኝ። አንተስ? አስተዳደሩስ? ሕጋዊ ሰውነታችን ተነጥቆ እንዴት ማስተዳደር እንችላለን ክቡር ሚኒስትር? ለዚህ ጉዳይ እንደደወልክ ገምቻለሁ። ደብዳቤም እኮ ልከናል ክቡር ሚኒስትር፡፡ አዎ። ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውኛል።...