የኬንያው ፕሪንስፓል ካታሊስት ኩባንያ በኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ አቅራቢ ከሆነው ከየስ ውኃ በሽርክና የገዛውን የ50 በመቶ ድርሻ ሸጦ ሊወጣ መሆኑ ተነገረ፡፡
ኩባንያው እ.ኤ.አ በ2013 ከየስ ውኃ ጋር በሽርክና ገበያውን ከተቀላቀለ ወዲህ ትርፍ ማግኘት ባለመቻሉ ድርሻውን ሸጦ ለመውጣት ከኢትዮጵያው ባለድርሻ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን፣ የየስ ውኃ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ከበደ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻቸው 50 በመቶ በመሆኑ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ተቸግረው እንደነበርና መገፋፋት እንደሚታይ የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ ከዚህ ባለፈ ሁለቱም ሥራ አስኪያጅ ቀጥረው ያሠሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከውኃ ማምረት በተጨማሪ አንድ የጁስ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊተክሉ ከተስማሙ ዓመታት ያለፋቸው ቢሆንም፣ እስካሁን በዕቅዳቸው መሠረት ፋብሪካውን ማቋቋም አለመቻላቸውን በመጥቀስ የዚህ ሁሉ ችግር የአክሲዮን ድርሻ ተመሳሳይ መሆንና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ጠንካራ አቋም ባለመያዙ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እየተከናወነ ባለው የድርሻ ማስተላለፍ ወይም ሽያጭ ላይ ሁለቱ ባለአክሲዮኖች ሲለያዩ በስምምነታቸው መሠረት እንዴት ሀብት ይከፋፈሉ የሚለውን ለመወሰን፣ የሁለቱም ኩባንያዎች ጠበቆች ውይይት እያደረጉ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለው ተናግረዋል፡፡
ከፕሪንስፓል ካታሊስት ጋር የሚደረገው አክሲዮን የማስተላለፍ ወይም የመሸጥ ሒደት ወደ መጨረሻ ደረጃ እንደደረሰ የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፣ ጉዳዩ በቅርቡ ውሳኔ ይሰጠዋል ተብሎ እንደሚጠበቅና በአቶ ዓለማየሁ ንጉሤ የተያዘው የኢትዮጵያው ኩባንያ አክሲዮን የኬንያውን ድርሻ መጠቅለል ከቻለ፣ በቀጣይ በተጠናከረ አደረጃጀትና ማኔጅመንት ሥራውን ማንቀሳቀስ የሚቻልበት ዕድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡
ሪፖርተር ፕሪንስፓል ካታሊስት ኩባንያን ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠይቅም፣ የደርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምንም ዓይነት አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡
የስ ውኃ በውጭ ምንዛሪና በጥሬ ዕቃ ችግር ውኃ ማምረት ካቆመ ሁለት ወራት እንዳለፈው ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የታሸገ ውኃ አምራች ድርጅቶች በአገሪቱ ባጋጠመ የጥሬ ዕቃና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት፣ ከ20 በላይ ኩባንያዎች ሥራ ማቆማቸውን ማስታወቃቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ከ100 በላይ የታሸገ ውኃ አቅራቢ ድርጅቶች በሥራ ላይ ሲገኙ፣ የታሸገ ውኃ ለማቅረብ የሚረዱ ጥሬ ዕቃዎች ችግር በተደጋጋሚ ሲያነሱ ይሰማሉ፡፡