በወርኃ መጋቢት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ወራት ከፍተኛ የአኃዝ ብልጫ ያለው የምግብ ዋጋ ግሽበት እንደተመዘገበ፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው ሪፖርት አመላከተ፡፡
የመጋቢት ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ43.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በየካቲት ወር ከተመዘገበው የ41.9 በመቶ አኃዝ ጋር ሲነፃፀር በ1.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በአብዛኛው የእህሎች ዋጋ በተጠናቀቀው ወር ጭማሪ ማሳየቱን ያመለከተው የስታትስቲክስ አገልግሎት በተለይም ሩዝ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሽንብራ፣ ምስር፣ እንዲሁም ሌሎች መሰል የእህል ዓይነቶች በአብዛኛው የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል ብሏል፡፡
የምርቴችና የኮንቴይነሮች እጥረት፣ የመርከብ ዋጋ ማሻቀብ፣ ምዕራባውያን የገቡበት የዩክሬይንና የሩሲያ ጦርነት፣ ይህንንም ተከትሎ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ፣ ምግብ ነክ የሆኑት የስንዴና የዘይት ምርቶች አቅርቦት ችግሮች ከዓለም አቀፍ እስከ አገር ቤት ድረስ በመዝለቅ፣ በተለይም የምግብ ነክ የዋጋ ንረትን እያባባሱት መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የሩስያና የዩክሬን ጦርነት በጀርመን በመጋቢት ወር 7.3 በመቶ፣ በቤልጂየም 8.31 በመቶ፣ እንዲሁም በስፔን 9.8 በመቶ የዋጋ ግሽበት እንዲመዘገብ ምክንያት መሆኑ ተገልጾ፣ ይህም በአገሮቹ ላይ ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ የተመዘገበ ከፍተኛ አኃዝ እንደሆነ የዓለም ኢኮኖሚን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ በመጋቢት ወር የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ34.7 ከመቶ ጭማሪ እንዳሳየ፣ የስታትስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከየካቲት ወር ጋር ሲነፃፀር በ4.0 ነጥብ በመቶና የምግብ የኢንዴክሱ ክፍሎች በ4.3 ነጥብ በመቶ ጭማሪ እንዳሳዩ የተገለጸ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት ምግብ ነክ ያልሆነው የዋጋ ግሽበት በ3.4 ነጥብ ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የበጀት ጉድለቱ እየሰፋ በሄደበት፣ ውስብስብ የገበያ አሻጥርና ፈጣን የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ መዳከም እየደረሰበት ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በየወሩ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት በቀጣዮቹ ወራትም በምግብ ነክም ሆነ ምግብ ነክ ባልሆኑ የኢንዴክስ ክፍሎች ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚመዘገብበት ሪፖርተር ያናገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አገሪቱ እየደረሰባት ከሚገኘው ችግር አንፃር በዋጋ ግሽበቱ ላይ የታየው አኃዝ ከዚህም በላይ ይሆን እንደነበር ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ያስረዱት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ፣ ሆኖም መንግሥት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ሸቀጦችን መደጎሙ፣ የነዳጅ ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉ፣ በአጠቃላይ ድጎማው የዋጋ ግሽበቱን አርባ በመቶዎቹ ውስጥ እንዲቆይ ዕድል ሰጥቶታል ብለው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በሌላ በኩል ይፋ ባደረገው የመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበት መረጃ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ23.5 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ከነበረው የካቲት ወር ጋር ሲነፃፀሩ ደግሞ 0.6 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
በዳቦና በተለያዩ እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ሁለት ትልልቅ በዓላት በሚከበሩበት ሚያዚያ ወር እየተስተዋለ ነው፡፡ በተለይ የሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የቅቤ፣ የቅመማ ቅመም፣ የበርበሬና የቡና ዋጋ ጭማሪዎች በተያዘው ወር ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ምጣኔ አስተዋጽኦቸው ቀላል እንደማይሆን ታምኗል፡፡