Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ20 በላይ ዶሮ አርቢ ድርጅቶች መዘጋታቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ20 በላይ የዶሮ አርቢና አቀናባሪ ድርጅቶች መዘጋታቸውን፣ የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር አስታወቀ።

ዶሮ አርቢዎቹ በዋነኝነት የመኖ ዋጋ በመወደዱ ምክንያት እየተፈተኑ መሆናቸውን፣ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሚሊዮን ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ማኅበሩ 115 አባላት እንዳሉት ገልጸው፣ ከአባላቱ መካከልም እስካሁን ከ20 በላይ የሚሆኑት መዘጋታቸውን ተናግረዋል። በመኖ ዋጋ መወደድ ምክንያት ሥራው አዋጭ አለመሆኑን አስረድተው፣ በተለይም እንደ በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ ስንዴ፣ ፍሩሽካና የመሳሰሉት የዶሮ መኖዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል ብለዋል።

በአገር ውስጥ የሚገኙት እንደ አኩሪ አተር ያሉና የቅባት እህል ተረፈ ምርቶች ለዶሮ መኖነት የሚውሉ መሆናቸውን፣ እነዚህም በብዛት ወደ ውጭ በመላካቸው በዶሮ አርቢዎች ላይ ጫና ፈጥሯል ብለዋል። ፋጉሎ የተባለው የዶሮ መኖ ወደ ውጭ እንደሚላክ ገልጸው፣ ይህም ሊቆምና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ሊውል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በዶሮ አርቢዎች ላይ የደርሰው ጫና በቀጥታ በእንቁላልና በዶሮ የገበያ ዋጋ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳለው የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ በአሁኑ ወቅት ከዶሮ አርቢዎች ዘንድ የአንድ እንቁላል ዋጋ እስከ ስድስት ብር ከ50 ሳንቲም እንደሚያወጣ ተናግረዋል። አንድ ኪሎ የዶሮ ሥጋ ደግሞ 230 ብር መድረሱን ገልጸው፣ ይህም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መቶ በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው ብለዋል።

ከ25 ዓመታት በላይ በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ የተሰማራው አለማ ፋርምስ መሥራችና ባለቤት መቶ አለቃ ለማ አስፋው በበኩላቸው፣ የዶሮ መኖ በተለይም አንድ ኩንታል አኩሪ አተር እስከ 5,000 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸው ይህም በጥቂት ወራት ውስጥ እስከ ሦስት እጥፍ ጭማሪ እንደታየበት አስረድተዋል፡፡

በመኖ ላይ ያለው የዋጋ ጭማሪም በዶሮና በእንቁላል ዋጋ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ምርቶቹ ለገበያ የሚቀርቡበትን ዋጋ ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

የቃል ዶሮ ዕርባታ የቁጥጥር ባለሙያ አቶ ዮናስ ማቲዎስ፣ 1,280 ብር የነበረው አንድ ኩንታል የስዴ መኖ በወራት ውስጥ 3,200 ብር ደርሷል ብለዋል። ከመኖ በተጨማሪ የጫጩት ዋጋ ከነበረበት እስከ ሦስት እጥፍ የሚደርስ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል። የአንድ ጫጩት ዋጋ 35 ብር የነበረ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅት ግን 98 ብር ደርሷል ብለዋል። ይህም ለዶሮ አርቢዎች ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች