የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሠራተኞች፣ በምርት ሽያጭና ሥርጭት ምክንያት፣ ካለፈው ሳምንት ሚያዝያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የተጠረጠሩበት ወንጀል ግልጽ ያልሆነው የሐበሻ ሲሚንቶ ሠራተኞች ፍርድ ቤት ቀርበው የምርመራ ጊዜ እንደተሰጠባቸውና ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በድጋሚ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡
የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋሀሳን ብሮማና የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች መታሰርን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
በተጨማሪም ማብራሪያ የተጠየቁት የፋብሪካው የሕግ ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ እሌኒ ከበደ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ማብራሪያ የመስጠት ሥልጣን እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ከመስከረም ወር ጀምሮ ባዋቀረው ግብረ ኃይል፣ የተለያዩ ሕጋዊ ዕርምጃዎች እየወሰደ ነው፡፡ ይህ ግብረ ኃይል የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ጨምሮ 17 ተቋማት በጋራ የሚሳተፉበት ነው፡፡
የንግድና የቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሐሰን መሀመድ እንደተናገሩት በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካይነት፣ ሕግን አክብረው በማይሠሩ ድርጅቶች ላይ የተለያዩ ሕጋዊ ዕርምጃዎችና ማስተካከያዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዲስ ባወጣው መመርያ መሠረት፣ ኢንዱስትሪዎች ከአጠቃላይ ፍላጎቱ ከ80 በመቶ የማያንስ የሲሚንቶ ምርት መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
በዚህ በተቋቋመው ግብረ ኃይል ከተደረጉ ማስተካከያዎች መካከል የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አንደኛው ነው፡፡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላለፉት ሁለት ወራት ያህል የሚጠበቅበትን ያህል አላመረተም ሲሉ አቶ ሐሰን ተናግረዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ ከዳንጎቴ ጋር ባደረገው ንግግር በዚህ ሳምንት በቀን 85 ሺሕ ኩንታል በማምረት አቅሙን እንዲያሳድግ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
የሐበሻ ሲሚንቶ ሠራተኞች መታሰራቸውን በተመለከተ ሚኒስቴር ደኤታው ከመናገር የተቆጠቡ ሲሆን፣ ግብረ ኃይሉ ውስጥ በተካተቱ የፀጥታ አካላት አማካይነት የታሰሩ መኖራቸውን ግን ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የሸቀጦች አቅርቦትና ፍላጎት የተመጣጠነ ባለመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት እየታየ ነው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከመስመር የወጡ አሠራሮችን ሥርዓት ለማስያዝና ለመመለስ በርካታ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ይናገራል፡፡
የሲሚንቶ እጥረትን በተመለከተ ያለውን ችግርና አሻጥሮችን የመለየት ሥራ በግብረ ኃይሉ እየተሠራና ችግሮቹ እየተለዩ መሆናቸውን አቶ ሐሰን ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማወቅም ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ያሉ ችግሮች በሚዳሰሱበት ወቅትም የተለያዩ ምክንያቶች እንደሚሰጡ የጠቆሙት ሚኒስትር ደኤታው፣ ሁሉም ምክንያቶች አሳማኝ ባለመሆናቸው የዘርፉ ዋነኛ ችግር ምን እንደሆነ በአራት የተለያዩ መንገዶች ለማወቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለው ኃላፊነት፣ ሸማቾች እንዳይጎዱ፣ አምራቾች ትርፋማ እንዲሆኑ፣ ነጋዴዎችን ማበረታት፣ የጅምላ ቸርቻሪዎች ያለአግባብ ሀብት እንዳያካብቱና እንዳይከስሩ፣ እንዲሁም የተመጣጠነ ገበያ እንዲካሄድ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
አከፋፋዮች፣ አምራቾች፣ የማዕድን ሚኒስቴርና የንግድ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የተለያዩ ውይይቶች ማካሄዳቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ውይይት ወቅትም አምራቾች ከሚያነሱዋቸው ዋና ዋና ችግሮች መካከል የግብዓት እጥረት፣ የፀጥታ ችግር፣ የካፒታል እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ መኖራቸው ታውቋል፡፡
የግብይት ሰንሰለቱን በመሀል እየገቡ የሚያራዝሙ ደላላዎች በመኖራቸው፣ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ችግሮቹን ለመፍታት እየሠራ ነው ተብሏል፡፡
ይህ ግብረ ኃይል በዋናነት የዋጋ ማረጋጋት ሥራ እንደሚያከናውን፣ እንዲሁም ሕገወጥ ነጋዴዎችን የሚከላከል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የሲሚንቶ ጉዳይ አገራዊ ጉዳይ እንደ መሆኑ መጠን፣ በአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን ሁሉም አካላት በጋራ ሆነው የሚያከናውኑት ተግባር መሆኑም ተገልጿል፡፡ የሲሚንቶ ምርት እንደ መሠረታዊ ሸቀጥ ታይቶ የዋጋ ተመን እንዲወጣለት እየተደረገ መሆኑም ተብራርቷል፡፡
በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ አለመረጋጋት፣ የልማት መጓተት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠር፣ የሥራ ዕድል መቀነስና የመሳሰሉ ችግሮችን ይፈጥራል ሲሉ አቶ ሐሰን ተናግረዋል፡፡ ይህም ችግር እንዳይፈጠር ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ዕርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑን፣ በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ባከናወነው ሥራ በሕገወጥ መንገድ የተከማቸ ምንም ዓይነት ምርት አለመገኘቱን፣ ይልቁንም በተደረገው የኦፕሬሽን ሥራ በቂ የሆነ ምርት አለመኖሩን ለማወቅ መቻሉ ተገልጿል፡፡
በሕገወጥ መንገድ የሲሚንቶ ክምችት ቢኖር ኖሮ በግብረ ኃይሉ አማካይነት ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርስ ይደረግ ነበር፡፡ ግን ምንም ‹‹ክምችት አለመገኘቱን፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ማንኛውም ድርጅት ለኅብረተሰብም ለአገርም ጉዳት ስለሚሆን እስከ እስርና የንግድ ፈቃድ እስከመሰረዝ ደረጃ ይደርሳል፤›› ሲሉ አቶ ሐሰን ተናግረዋል፡፡
የነጋዴዎች በደረሰኝ ያለመገበያየት በዋናነት የሲሚንቶ ዋጋ ለመጨመር ምክንያቶች ከሆኑ መካከል ይጠቀሳል፡፡ የወንጀል ተግባራት ካሉ የሚመለከተው የፀጥታ አካላትን የሚመለከት በመሆኑ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮዎችና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሥራዎች እየተሠሩ ነው ሲሉ አቶ ሐሰን ተናግረዋል፡፡ ሲሚንቶ በዋናነት ከተመረተ በኋላ የንግድና ትስስር ሚኒስቴር የሚቆጣጠረው እንደሆነ፣ ከመመረቱ በፊት ደግሞ የማዕድን ሚኒስቴር እንደሚቆጣጠረው ይታወቃል፡፡